ኤርምያስ 18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኤርምያስ በሸክላ ሠሪው ቤት 1 ከእግዚአብሔር ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፦ 2 “ተነሥተህ ወደ ሸክላ ሠሪው ቤት ውረድ፤ እዚያም መልእክቴን እነግርሃለሁ።” 3 እኔም እዚያ ሄጄ ሸክላ ሠሪው በመንኰራኲሩ ላይ ሲሠራ አየሁት፤ 4 የሸክላውም ዕቃ በእጁ ላይ በሚበላሽበት ጊዜ እንደገና ለውሶ በሚፈልገው ዐይነት ሌላ ዕቃ አድርጎ ይሠራው ነበር። 5 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 6 “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ሸክላ ሠሪው ሸክላውን በፈለገው ዐይነት እንደሚሠራው፥ እኔስ በእናንተ ላይ የፈለግኹትን ማድረግ አልችልምን? የሸክላው ጭቃ በሸክላ ሠሪው እጅ እንደሚገኝ እናንተም፥ በእኔ እጅ ናችሁ። 7 እኔ አንድን ሕዝብ ወይም መንግሥት፥ ‘እነቅላለሁ ወይም ሰባብሬ አጠፋለሁ’ ብዬ በተናገርኩ ጊዜ፥ 8 ያ ሕዝብ ተጸጽቶ ከክፋቱ የሚመለስ ከሆነ፥ አመጣበታለሁ ብዬ ያቀድኩትን ክፉ ነገር አላደርግበትም። 9 በሌላ በኩል ደግሞ እኔ አንድን ሕዝብ ወይም መንግሥት ‘እተክላለሁ ወይም እገነባለሁ’ በምልበት ጊዜ፥ 10 ያ ሕዝብ ለእኔ የማይታዘዝና ክፋትንም የሚያደርግ ሆኖ ከተገኘ ላደርግለት ያቀድኩትን መልካም ነገር አላደርግለትም። 11 ስለዚህም እኔ እነርሱን ለመቅጣት በእነርሱ ላይ ክፉ ነገር የማደርግ መሆኔን ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ሕዝብ ንገራቸው፤ ኃጢአት መሥራትን እንዲተዉና አካሄዳቸውንና አሠራራቸውን ሁሉ እንዲለውጡ ምከራቸው። 12 እነርሱም ‘ስለምን ብለን ይህን እናደርጋለን? እንዲያውም ያቀድነውን ሁሉ በመፈጸም ከምንጊዜውም ይልቅ እልኸኞችና ዐመፀኞች መሆን እንችላለን’ ብለው ይመልሱልሃል።” የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን መተዉ 13 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ይህን የመሰለ ነገር በሕዝቦች መካከል ተሰምቶ እንደ ሆነ ጠይቁ፤ የተለዩ የእስራኤል ሕዝብ በጣም አጸያፊ የሆነ ነገር አድርገዋል። 14 የሊባኖስ ጭንጫማ ተራራዎች በበረዶ ያልተሸፈኑበት ጊዜ አለን? ከየተራራው ላይ የሚወርዱትስ ቀዝቃዛ ምንጮች ደርቀው ያውቃሉን? 15 ሕዝቤ ግን እኔን ረስተዋል፤ ከንቱ ለሆኑ ጣዖቶችም ዕጣን ያጥናሉ፤ እነርሱም ባልታወቀ መንገድ እንዲሄዱ አድርገዋቸዋል፤ ተሰናክለውም የቀድሞውን መንገድ ትተዋል። 16 ምድራቸው የዘለዓለም መሳለቂያ፥ ባድማ ትሆናለች፤ በአጠገብዋ የሚያልፉ ሁሉ በማፌዝ ራሳቸውን ይነቀንቃሉ፤ 17 ትቢያ በምሥራቅ ነፋስ እንደሚበተን፥ ሕዝቤን በጠላቶቻቸው ፊት እበትናቸዋለሁ። ፊቴን ከእነርሱ መልሼ ጀርባዬን እሰጣቸዋለሁ። ጥፋት በሚመጣባቸውም ጊዜ ፈጽሞ አልረዳቸውም።” በኤርምያስ ላይ የታቀደ ሤራ 18 ከሕዝቡ መካከል አንዳንድ ሰዎች፦ “ኑ በኤርምያስ ላይ ዕቅድ እናውጣ! የእግዚአብሔርን ሕግ የሚያስተምሩ ካህናት፥ ምክር የሚሰጡ ጥበበኞች፥ የእግዚአብሔርን መልእክት የሚናገሩ ነቢያት ሁልጊዜ እናገኛለን፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ ኤርምያስን ከማድመጥ ይልቅ በንግግሩ አጥምደን በወንጀል እንክሰሰው ተባባሉ።” 19 ስለዚህ እንዲህ በማለት ጸለይኩ “እግዚአብሔር ሆይ! ልመናዬን ስማ፤ ጠላቶቼም በእኔ ላይ የሚናገሩትን ክፉ ነገር አድምጥ። 20 ታዲያ የደግ ሥራ ዋጋው ክፉ ነገር ማድረግ ነውን? አንተ በእነርሱ ላይ እንዳትቈጣ እኔ በፊትህ ቆሜ ስለ እነርሱ እንደማለድኩህ አስብ፤ እነርሱ ግን እነሆ እኔ የምወድቅበትን ጒድጓድ ቈፈሩ። 21 አምላክ ሆይ! አሁን ግን ልጆቻቸው በራብ እንዲያልቁ፥ እነርሱም በጦርነት እንዲወድቁ አድርግ፤ ሴቶቻቸው ያለ ባልና ያለ ልጅ ይቅሩ፤ ወንዶቻቸው በበሽታ ወጣቶቻቸውም በጦርነት ይደምሰሱ። 22 ወራሪዎችን በድንገት ላክባቸው፤ ከቤታቸው ጩኸት ይሰማ፤ እነርሱ እኔ የምወድቅበትን ጒድጓድ ቆፍረዋል፤ የምያዝበትንም ወጥመድ አዘጋጅተዋል። 23 አምላክ ሆይ! እነርሱ እኔን ለመግደል የሸረቡትን ሤራ ታውቀዋለህ፤ ስለዚህ ክፋታቸውን ይቅር አትበል፤ ኃጢአታቸውም እንዲሰረይላቸው አታድርግ፤ በፊትህ እንዲሸነፉና በብርቱ ቊጣህ እንዲወድቁ አድርግ።” |