ራእይ 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 አምስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ እነሆ፥ ከሰማይ ወደ ምድር የወደቀ አንድ ኮከብ አየሁ፤ የጥልቁ ጒድጓድ መክፈቻ ተሰጠው። 2 እርሱ የጥልቁን ጒድጓድ ከፈተው፤ ጢስም ከታላቅ ምድጃ እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጥልቁ ጒድጓድ ወጣ፤ ከጒድጓዱ በወጣው ጢስ ምክንያት ፀሐይና አየር ጨለሙ፤ 3 ከጢሱም ውስጥ አንበጣዎች በምድር ላይ ወጡ፤ የምድር ጊንጦችን ኀይል የመሰለ ኀይል ተሰጣቸው፤ 4 የምድርን ሣር ሆነ ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ እንዳይጐዱ ተነገራቸው፤ መጒዳት ያለባቸው ግን በግንባራቸው ላይ የእግዚአብሔር ማኅተም የሌለባቸውን ሰዎች ብቻ ነበር። 5 እነርሱንም ቢሆን አምስት ወር ለማሠቃየት እንጂ ለመግደል ፈቃድ አልተሰጣቸውም፤ አንበጣዎቹ የደረሰባቸው ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ሲነድፍ እንደሚሰማው ዐይነት ያለ ነው። 6 በእነዚያ ቀኖች ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን አያገኙትም፤ ለመሞትም ይመኛሉ፤ ነገር ግን ሞት ከእነርሱ ይሸሻል። 7 አንበጣዎቹ ለጦርነት የተዘጋጁ ፈረሶችን ይመስሉ ነበር፤ በራሳቸው ላይ የወርቅ አክሊል የመሰለ ነገር ነበር፤ ፊታቸውም የሰው ፊት ይመስል ነበር፤ 8 የሴት ጠጒር የመሰለ ጠጒር ነበራቸው፤ ጥርሳቸው የአንበሳ ጥርስ ይመስል ነበር፤ 9 የብረት ጥሩር የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የክንፎቻቸው ድምፅ ወደ ጦርነት የሚጋልቡ ብዙ ፈረሶችና ሠረገላዎች የሚያሰሙትን ድምፅ ይመስል ነበር። 10 እንደ ጊንጥ ጅራትና መንደፊያ ነበራቸው፤ በጅራታቸው ውስጥ ሰዎችን ለአምስት ወር የሚጐዱበት ኀይል ነበራቸው። 11 ንጉሥም ነበራቸው፤ እርሱ የጥልቁ ጒድጓድ መልአክ ነው፤ ስሙም በዕብራይስጥ አባዶን፥ በግሪክ አጶልዮን ይባላል፤ 12 የመጀመሪያው ወዮ አልፎአል፥ እነሆ ከዚህ በኋላ ሌላ ሁለት ወዮ ገና ይመጣል። 13 ስድስተኛው መልአክ እምቢልታውን ነፋ፤ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ካለው በወርቅ ከተሠራው ከመሠዊያው ቀንዶች ድምፅ ሲወጣ ሰማሁ። 14 ድምፁም እምቢልታ የያዘውን ስድስተኛውን መልአክ፥ “በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው!” አለው። 15 ለዚህ ሰዓትና ለዚህ ቀን፥ ለዚህ ወርና ለዚህ ዓመት የተዘጋጁት አራቱ መላእክት የሰውን ዘር አንድ ሦስተኛ እንዲገድሉ ተፈቱ። 16 የፈረሰኞቹ ሠራዊት ብዛት ሁለት መቶ ሚሊዮን መሆኑን ሰማሁ። 17 ፈረሶቹንና በፈረሶቹ ላይ የተቀመጡትን ሰዎች በራእይ ያየኋቸው እንደሚከተለው ነበር፦ በደረታቸው ላይ የነበረው ጥሩር እንደ እሳት ፍም ቀይ፥ እንደ ያክንት ጥቊር ሰማያዊ፥ እንደ ዲን ቢጫ ይመስል ነበር፤ የፈረሶቹም ራስ የአንበሳ ራስ ይመስል ነበር፤ ከአፋቸው እሳትና ጢስ ዲንም ይወጣ ነበር፤ 18 ከአፋቸው ባወጡት እሳት፥ ጢስና ዲን በእነዚህ በሦስቱ መቅሠፍቶች የሰው ዘር አንድ ሦስተኛ ተገደለ። 19 የፈረሶቹ ኀይል በአፋቸውና በጅራታቸው ነበር፤ ጅራታቸው እባብ ይመስላል፤ የእባብ ራስም አለው፤ ሰውንም የሚጐዱት በእርሱ ነበር። 20 በእነዚህ መቅሠፍቶች ከሞት የተረፉት የሰው ዘር ከእጃቸው ሥራ ተመልሰው ንስሓ አልገቡም፤ አጋንንትንና ከወርቅ፥ ከብር፥ ከናስ፥ ከድንጋይና ከእንጨት የተሠሩ ማየት ወይም መስማት ወይም መሄድ የማይችሉትን ጣዖቶች ማምለክንም አልተዉም። 21 እንዲሁም ከነፍሰ ገዳይነታቸው፥ ከሟርታቸው፥ ከሴሰኛነታቸው፥ ከሌብነታቸውም ንስሓ አልገቡም። |