Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሐዋርያት ሥራ 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእስጢፋኖስ ንግግር

1 የካህናት አለቃው እስጢፋኖስን “ይህ የተባለው ነገር ልክ ነውን?” ሲል ጠየቀው።

2 እስጢፋኖስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ወንድሞቼና አባቶቼ ሆይ! እስቲ ስሙኝ! አባታችን አብርሃም በካራን ለመኖር ከመሄዱ በፊት ገና በመስጴጦምያ ሳለ የክብር አምላክ ተገለጠለትና

3 ‘ከአገርህ ወጥተህ፥ ከዘመዶችህ ተለይተህ፥ እኔ ወደማሳይህ አገር ሂድ’ አለው።

4 በዚያን ጊዜ ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ፤ አባቱ ከሞተ በኋላም እግዚአብሔር ከካራን አውጥቶ ዛሬ እናንተ ወደምትኖሩባት አገር አመጣው።

5 ይሁን እንጂ የእግር ማሳረፊያ እንኳ የሚያኽል ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን ይህችን አገር ለእርሱና ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ርስት አድርጎ እንደሚሰጠው ቃል ገብቶለት ነበር፤ ይህን ቃል የገባለትም አብርሃም ገና ልጅ ሳይኖረው ነበር።

6 ዘሩም በባዕድ አገር ስደተኛ ሆኖ እንደሚኖርና በዚያም አገር አራት መቶ ዓመት ባሪያ አድርገው በጭቈና እንደሚገዙት ነግሮት ነበር።

7 ቀጥሎም ‘ባሪያ አድርጎ በሚገዛው ሕዝብ ላይ እፈርድበታለሁ፤ ከዚያም በኋላ ነጻ ወጥተው በዚህ ስፍራ ያመልኩኛል’ ብሎ እግዚአብሔር ተናግሮአል።

8 የመገረዝንም ኪዳን ሰጠው፤ ስለዚህ አብርሃም ይስሐቅን በወለደ ጊዜ በስምንተኛው ቀን ገረዘው፤ እንዲሁም ይስሐቅ ልጁን ያዕቆብን ገረዘው። ያዕቆብም የነገድ አባቶች የሆኑትን ዐሥራ ሁለቱን ልጆቹን ገረዘ።

9 “የያዕቆብ ልጆች በወንድማቸው በዮሴፍ ላይ ቀንተው በግብጽ አገር ባሪያ እንዲሆን ሸጡት፤ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ነበረ፤

10 ከመከራው ሁሉ አወጣው፤ በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ፊትም ሞገስንና ጥበብን ሰጠው። ንጉሡም በግብጽና በቤቱም ሁሉ ላይ አዛዥ አደረገው።

11 በዚያን ጊዜ በግብጽና በከነዓን አገር ሁሉ ላይ ታላቅ ችግር ያስከተለ ራብ ሆነ፤ አባቶቻችንም ምግብ ሊያገኙ አልቻሉም።

12 ያዕቆብም በግብጽ እህል መኖሩን በሰማ ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ አባቶቻችንን ወደዚያ ላከ።

13 ዳግመኛ ወደ ግብጽ ተመልሰው በሄዱ ጊዜ ዮሴፍ ለወንድሞቹ ተገለጠ፤ ቤተ ዘመዱም በፈርዖን ዘንድ ታወቀ።

14 ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አባቱን ያዕቆብንና ዘመዶቹን ሁሉ ወደ እርሱ አስመጣቸው፤ እነርሱም በጠቅላላው ሰባ አምስት ሰዎች ነበሩ።

15 ስለዚህ ያዕቆብ ወደ ግብጽ ሄደ፤ እርሱና አባቶቻችን እዚያ ሞቱ።

16 ዐጽማቸው ወደ ሴኬም ተወስዶ አብርሃም በሴኬም ከኤሞር ልጆች በገንዘቡ በገዛው መቃብር ተቀበረ።

17 “እግዚአብሔር ለአብርሃም በመሐላ የሰጠው ተስፋ የሚፈጸምበት ጊዜ ሲቃረብ በግብጽ የነበረው የሕዝባችን ቊጥር እየበዛ ሄደ።

18 ይህም የሆነው ዮሴፍን የማያውቅ ሌላ ንጉሥ በግብጽ እስከ ነገሠበት ጊዜ ድረስ ነው።

19 አዲሱ ንጉሥ በሕዝባችን ላይ በተንኰል ተነሥቶ አባቶቻችንን ይጨቊናቸው ጀመር፤ ሕፃኖቻቸውም እንዲሞቱና ወደ ውጪ አውጥተው እንዲጥሉአቸው፥ አባቶቻችንን አስገደዳቸው።

20 በዚያን ጊዜ ሙሴ ተወለደ፤ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ያማረ ሕፃን ነበር፤ ሦስት ወር በአባቱ ቤት አደገ፤

21 ወደ ውጪም በተጣለ ጊዜ የፈርዖን ሴት ልጅ አነሣችውና እንደ ልጅዋ አድርጋ አሳደገችው።

22 ሙሴም የግብጻውያንን ጥበብ ሁሉ ተማረ፤ በቃሉና በሥራውም የበረታ ሆነ።

23 “ሙሴ አርባ ዓመት በሞላው ጊዜ ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ለመጐብኘት ተነሣሣ።

24 ከወንድሞቹም አንዱ በአንድ ግብጻዊ ሰው ሲበደልና ሲገፋ አይቶ ረዳው፤ ለተገፋውም በመበቀል ግብጻዊውን መታና ገደለው።

25 እግዚአብሔር በእርሱ አማካይነት ነጻ እንደሚያወጣቸው ወገኖቹ የሚገነዘቡ መስሎት ነበር፤ እነርሱ ግን ይህን አልተገነዘቡም።

26 በማግስቱም ሁለት እስራኤላውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አገኘና ሊገላግላቸው በመፈለግ ‘እናንተ ሰዎች፥ እናንተ ወንድማማች ናችሁ፤ ስለምን ትጣላላችሁ?’ አላቸው።

27 ያ ባልንጀራውን ይደበድብ የነበረው ሰው ሙሴን ወዲያ ገፈተረና ‘አንተን በእኛ ላይ ገዢና ፈራጅ ያደረገህ ማን ነው?

28 ትናንትና ግብጻዊውን እንደ ገደልከው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?’ አለው።

29 ሙሴ ይህን በሰማ ጊዜ ከግብጽ አገር ሸሽቶ ወደ ምድያም አገር ሄደና እዚያ በስደት ኖረ፤ በዚያ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ።

30 “ሙሴ በዚያ አገር አርባ ዓመት ካሳለፈ በኋላ በደብረ ሲና በረሓ በሚነደው የቊጥቋጦ ነበልባል ውስጥ አንድ መልአክ ታየው።

31 ሙሴ ይህን ባየ ጊዜ ተገረመ፤ ቀረብ ብሎም ሲመለከት እንዲህ የሚለውን የጌታ ድምፅ ሰማ፤

32 ‘እኔ የአባቶችህ አምላክ ነኝ፤ የአብርሃም አምላክ፤ የይስሐቅ አምላክ፥ የያዕቆብ አምላክ ነኝ፤’ ሙሴም በፍርሃት ተንቀጠቀጠ፤ ለመመልከትም አልደፈረም።

33 ጌታም እንዲህ አለው፦ ‘የቆምክበት ስፍራ የተቀደሰ ምድር ስለ ሆነ ጫማህን አውልቅ፤

34 በግብጽ ያለውን የሕዝቤን ጽኑ መከራ በእርግጥ አይቼአለሁ፤ የጭንቀት ጩኸታቸውንም ሰምቻለሁ፤ ስለዚህ ላድናቸው ወርጃለሁ፤ አሁንም ና! እኔ አንተን ወደ ግብጽ እልክሃለሁ።’

35 “የእስራኤል ሕዝብ ሙሴን ‘በእኛ ላይ ገዢና ፈራጅ እንድትሆን ያደረገህ ማን ነው?’ በማለት ተቃውመውት ነበር፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ይህንኑ ሙሴን በቊጥቋጦው ውስጥ በተገለጠለት መልአክ አማካይነት ገዢና ነጻ አውጪ አድርጎ ወደ እነርሱ ላከው።

36 በግብጽና በቀይ ባሕር ድንቆችንና ተአምራትን በማድረግ ሕዝቡን አውጥቶ አርባ ዓመት የመራቸው ይህ ሙሴ ነበር።

37 ‘ጌታ አምላካችሁ እኔን እንዳስነሣኝ እንዲሁ ከወንድሞቻችሁ መካከል ነቢይ ያስነሣላችኋል’ ብሎ ለእስራኤላውያን የተናገረው ይኸው ሙሴ ነበር።

38 በበረሓ ተሰብስቦ ከነበረው ሕዝብ ጋርና ከሲና ተራራ ላይ ከተናገረው መልአክ ጋር እንዲሁም ከአባቶቻችን ጋር የነበረው እርሱ ነው። የእግዚአብሔርን የሕይወት ቃል ለእኛ ያስተላለፈልንም ይኸው ሙሴ ነው።

39 “አባቶቻችን ግን ተቃወሙት እንጂ አልታዘዙትም፤ በልባቸውም ወደ ግብጽ ለመመለስ አሰቡ።

40 አሮንንም ‘ይህ ከግብጽ አገር ያወጣን ሙሴ ምን እንደ ደረሰበት አናውቅምና እፊት እፊታችን እየሄዱ የሚመሩንን አማልክት ሥራልን’ አሉት።

41 በዚያን ጊዜ በጥጃ ምስል ጣዖት ሠርተው መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸውም ሥራ ተደሰቱ።

42 እግዚአብሔር ግን ተለያቸው። የሰማይንም ከዋክብት እንዲያመልኩ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም በነቢያት እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው፤ ‘እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ! የታረደውን እንስሳና መሥዋዕትን አርባ ዓመት ሙሉ በበረሓ ያቀረባችሁት ለእኔ ነውን?

43 ይዛችሁ የሄዳችሁት የሞሎክን ድንኳንና ሬፋን የሚባለውን የአምላካችሁን ኮከብ ምስል ነበር፤ እነርሱም በእጃችሁ ሠርታችሁ ትሰግዱላቸው የነበሩ አማልክት ናቸው። እኔም ከባቢሎን ወዲያ እንድትሰደዱ አደርጋለሁ።’

44 “አባቶቻችን በበረሓ የምስክሩ ድንኳን ነበረቻቸው፤ ይህችንም ድንኳን እግዚአብሔር በነገረውና ባሳየው መሠረት የሠራት ሙሴ ነበር።

45 እግዚአብሔር ከፊታቸው ያባረረላቸውን የአሕዛብን አገር በወረሱ ጊዜ አባቶቻችን ይህችን የተቀበሉአትን ድንኳን ከኢያሱ ጋር ወደዚያ አገቡአት፤ እስከ ዳዊት ዘመንም ድረስ እዚያ ኖረች።

46 ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝቶ ለያዕቆብ አምላክ ለእግዚአብሔር ማደሪያ የሚሆን ቤት ለመሥራት በጸሎት ለመነ።

47 ነገር ግን ለእግዚአብሔር ቤት የሠራው ሰሎሞን ነው።

48 “ሆኖም ልዑል እግዚአብሔር በሰው እጅ በተሠራ ቤት ውስጥ አይኖርም፤ ይህም ነቢዩ እንዲህ ሲል እንደ ጻፈው ነው፤

49 ‘ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ ማሳረፊያ ናት፤ ታዲያ ለእኔ ምን ዐይነት ቤት ትሠሩልኛላችሁ? የማርፍበትስ ቦታ ምን ዐይነት ነው? ይላል ጌታ።

50 ይህን ሁሉ እኔ በእጄ የሠራሁት አይደለምን?’ ይላል እግዚአብሔር።

51 “እናንተ እልኸኞች ልባችሁ የተደፈነ! ጆሮአችሁም የማይሰማ! እናንተም ልክ እንዳባቶቻችሁ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን ትቃወማላችሁ።

52 ከነቢያት መካከል አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን አለ? እነርሱ የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ እናንተም አሁን ይህን ጻድቁን አሳልፋችሁ በመስጠት ገደላችሁት።

53 እናንተ በመላእክት አማካይነት ሕግን ተቀብላችሁ ነበር፤ ነገር ግን አልጠበቃችሁትም።”


እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ መሞቱ

54 የሸንጎ አባሎች ይህን በሰሙ ጊዜ ተናደዱ፤ በእስጢፋኖስ ላይም በቊጣ ጥርሳቸውን አፋጩ።

55 እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኲር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር አየ፤ ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየው፤

56 ስለዚህ “እነሆ፥ ሰማይ ተከፍቶ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ።

57 በዚህ ጊዜ እነርሱ በታላቅ ድምፅ ጮኹ፤ ጆሮአቸውንም ደፍነው በአንድነት ወደ እርሱ ሮጡ።

58 ከከተማ አወጡትና በድንጋይ ወገሩት፤ ምስክሮችም ልብሳቸውን ወስደው ሳውል የሚባል አንድ ጐልማሳ እንዲጠብቅላቸው በእግሩ ሥር አስቀመጡ።

59 በድንጋይ ሲወግሩት ሳሉ እስጢፋኖስ፥ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ! ነፍሴን ተቀበል!” ብሎ ጸለየ።

60 ተንበርክኮም “ጌታ ሆይ! ይህን በደል አትቊጠርባቸው!” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ይህንንም ብሎ ሞተ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos