Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የተሰበረው ገንቦ ምሳሌ

1 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ሄደህ ከሸክላ ሠሪው ገንቦ ግዛ፤ ከሕዝቡና ከካህናቱ መካከል ታላላቆቹን መርጠህ ከአንተ ጋር አብረው እንዲሄዱ አድርግ።

2 በሸክላ ስባሪ በር በኩል አድርገህ ወደ ሂኖም ሸለቆ ሂድ፤ በእዚያም እኔ የምነግርህን ቃል እንዲህ ብለህ ዐውጅ፦

3 ‘የይሁዳ ነገሥታትና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁሉ እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የምነግራችሁን አድምጡ፤ እነሆ በጆሮው ለሚሰማው ሰው ሁሉ የሚዘገንን መቅሠፍት አመጣለሁ።

4 ይህንንም የማደርገው ሕዝቡ እኔን ስለ ተዉና ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት በማቅረብ ይህን ስፍራ ስላረከሱ ነው፤ እነርሱም ሆኑ የቀድሞ አባቶቻቸው ከይሁዳ ነገሥታት ጭምር ስለ ነዚህ አማልክት የሚያውቁት ነገር የለም፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ንጹሖች ሰዎችን በመግደል ይህ ስፍራ በደም የተሞላ እንዲሆን አድርገውታል።

5 ልጆቻቸውንም መሥዋዕት አድርገው በእሳት ለማቃጠል ለባዓል መሠዊያዎችን ሠርተዋል፤ ይህን እንዲያደርጉ አላዘዝኳቸውም፤ ከቶም ስለዚህ ነገር አላሰብኩም።

6 ስለዚህ ይህ ስፍራ ቶፌት ወይም የሂኖም ሸለቆ መባሉ ቀርቶ የዕርድ ሸለቆ ተብሎ የሚጠራበት ጊዜ ይመጣል።

7 የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ያቀዱት ነገር ሁሉ በዚህ ስፍራ እንዳይፈጸም አደርጋለሁ፤ ጠላቶቻቸው ድል እንዲነሡአቸውና በጦርነትም እንዲገድሉአቸው አደርጋለሁ፤ ሬሳቸውንም የሰማይ ወፎችና የምድር አራዊት እንዲበሉት አደርጋለሁ።

8 ይህችን ከተማ የፍርስራሽ ክምር አደርጋታለሁ፤ በዚያ በኩል የሚያልፍ ሁሉ ይደነግጣል፤ በደረሰባት ችግርም ይገረማል።

9 ጠላት ከተማይቱን ከቦ ሕዝቡን ለመጨረስ ያስጨንቋቸዋል፤ በዚህ ጊዜ ምግብ ሁሉ አልቆ ሕዝቡ ስለሚራብ እርስ በርሳቸው ይባላሉ፤ እንዲያውም ወላጆች የልጆቻቸውን ሥጋ ይበላሉ።’ ”

10 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አብረውኝ በሄዱት ሰዎች ፊት ያን ገንቦ እንድሰብረው አዘዘኝ፤

11 የሠራዊት አምላክ እንድነግራቸው ያዘዘኝም ቃል ይህ ነው፥ “ይህ የተሰበረ የሸክላ ገንቦ ተመልሶ ሊጠገን እንደማይችል፥ ይህን ሕዝብና ይህችን ከተማ በዚሁ ዐይነት እሰባብራለሁ፤ ሰዎች ሙታናቸውን የሚቀብሩበት ሌላ ስፍራ ስለማይገኝ በቶፌት ይቀብሩአቸዋል።”

12 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በቶፌት ላይ እንዳደረግሁ በዚህ ከተማና በኗሪዎችዋ ላይ አደርጋለሁ፤

13 የኢየሩሳሌም ሕዝብና የይሁዳ ነገሥታት የሚኖሩባቸው ቤቶች፥ እንዲሁም በጣራዎቻቸው ላይ ለሰማይ ሠራዊት ዕጣን የሚታጠንባቸውና ለባዕዳን አማልክትም የወይን ጠጅ የሚፈስባቸው ቤቶች ሁሉ እንደ ቶፌት የረከሱ ይሆናሉ።”

14 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ቃሉን እንድናገርበት ካዘዘኝ ከቶፌት ተመልሼ መጣሁ፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይም ቆሜ እንዲህ ብዬ ነገርኳቸው፤

15 “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነርሱ እልኸኞች ሆነው ለቃሌ ስላልታዘዙ በዚህች ከተማና በዙሪያዋ በሚገኙ ስፍራዎች ሁሉ ይመጣል ብዬ ያስታወቅኹትን መቅሠፍት ሁሉ አመጣባቸዋለሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos