Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ኤርምያስና የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን

1 ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል የሚከተለው ነው፤

2 “የዚህን ቃል ኪዳን ይዘት አድምጠህ ለይሁዳ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም ከተማ ነዋሪዎች ንገራቸው።

3 ይህን ቃል ኪዳን የማይታዘዝ ሁሉ የተረገመ ይሁን።

4 ይህ ቃል ኪዳን እንደ ጋለ ምድጃ ከሆነችባቸው አገር ከግብጽ ባወጣኋቸው ጊዜ ለቀድሞ አባቶቻችሁ የሰጠሁት ነው፤ ለእኔ እንዲታዘዙና እኔ የምላቸውን ሁሉ እንዲፈጽሙ ነገርኳቸው፤ የሚታዘዙኝም ከሆነ እነርሱ ሕዝቤ እንደሚሆኑና እኔም አምላካቸው እንደምሆን ገለጥኩላቸው።

5 ይህም ከሆነ አሁን ያሉባትን በማርና በወተት የበለጸገችውን ለምለም ምድር የቀድሞ አባቶቻቸው እንዲወርሱ ባደረግሁ ጊዜ የሰጠኋቸውን የተስፋ ቃል እፈጽማለሁ።” እኔም “እሺ ጌታ ሆይ!” አልኩ።

6 ከዚያን በኋላም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ወደ ይሁዳ ከተሞችና ወደ ኢየሩሳሌም መንገዶች ሄደህ ቃል ኪዳኔን እንዲያዳምጡና ትእዛዞቼን እንዲፈጽሙ በማሳሰብ ቃሌን ዐውጅላቸው፤

7 የቀድሞ አባቶቻቸውን ከግብጽ ባወጣኋቸው ጊዜ ለእኔ እንዲታዘዙ ደጋግሜ አስጠነቀቅኋቸው፤ ሕዝቡንም እስከ ዛሬው ቀን ድረስ እንኳ ከማስጠንቀቅ አልተቈጠብኩም።

8 ነገር ግን ሊያዳምጡኝም ሆነ ሊታዘዙኝ አልፈለጉም፤ በዚህ ፈንታ እያንዳንዱ ከምንጊዜውም ይልቅ እልኸኛና ክፉ ሆኖአል፤ ቃል ኪዳኔን እንዲፈጽሙ አዘዝኳቸው፤ እነርሱ ግን እምቢ አሉ፤ ስለዚህ በቃል ኪዳኔ የተጻፈውን መቅሠፍት ሁሉ አመጣሁባቸው።”

9 ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በኔ ላይ ዐድመዋል፤

10 እኔ ያዘዝኳቸውን ለመፈጸም እምቢ ይሉ እንደ ነበሩት እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው ኃጢአት ይሠራሉ፤ ባዕዳን አማልክትን ያመልካሉ፤ እስራኤልና ይሁዳ በአንድነት ከቀድሞ አባቶቻቸው ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል።

11 ስለዚህም እነሆ እኔ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ጥፋት አመጣባቸዋለሁ፤ ከጥፋቱም ማምለጥ አይችሉም፤ የእኔን ርዳታ ለማግኘት ቢጮኹም እንኳ አልሰማቸውም።

12 በዚያን ጊዜ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ መሥዋዕት ወደሚያቀርቡላቸው ባዕዳን አማልክት ሄደው ርዳታ እንዲያደርጉላቸው ይጮኻሉ፤ ነገር ግን እነርሱ ይህ ጥፋት በሚመጣበት ጊዜ ሊያድኑአቸው አይችሉም።

13 የይሁዳ ሕዝብ ሆይ፥ በከተሞቻችሁ ልክ ብዙ አማልክት አሉአችሁ፤ በኢየሩሳሌምም መንገዶች ልክ አጸያፊ ለሆነው በዓል ተብሎ ለሚጠራው ባዕድ አምላክ መሥዋዕት የምታቀርቡበት ብዙ መሠዊያዎችን ሠርታችኋል።

14 ኤርምያስ ሆይ፥ እነርሱ በሚጨነቁበት ጊዜ ወደ እኔ ሲጮኹ ስለማልሰማቸው ለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ስለ እነርሱም ልመናና ምልጃ አታቅርብ።”

15 እግዚአብሔር ለይሁዳ ሕዝብ እንዲህ እንድላቸው ነገረኝ፦ “እናንተ እኔ የምወዳችሁ ሕዝብ ናችሁ፤ ነገር ግን እንደእነዚህ ያሉ ክፉ ነገሮችን እያደረጋችሁ በዚህ በቤተ መቅደሴ ውስጥ ልትገኙ አይገባም፤ የምታቀርቡልኝም የእንስሶች መሥዋዕት ከጥፋት አይጠብቃችሁም፤ ስለዚህ በቤተ መቅደሴ ውስጥ መደሰታችሁን አቁሙ።

16 አንድ ጊዜ እናንተ በፍሬ እንደ ተመላ የወይራ ዛፍ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በቅርብ ጊዜ እንደ ነጐድጓድ የሚያስተጋባ ድምፅ በማሰማት ቅጠሉን በእሳት አቃጥላለሁ ቅርንጫፎችንም እሰባብራለሁ።

17 “እኔ የሠራዊት አምላክ ነኝ፤ እናንተ የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ እኔ እንደ ተከልኩት ዛፍ ናችሁ፤ ነገር ግን በዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት መሥዋዕት በማቅረባችሁ አስቈጣችሁኝ፤ ስለዚህ አሁን ጥፋትን አመጣባችኋለሁ።”


ኤርምያስን ለመግደል የተደረገ ዐድማ

18 በዚያን ጊዜ እነርሱ የሚያደርጉትን ነገር እግዚአብሔር ስላሳየኝ ሤራቸውን ዐወቅሁት።

19 ወደ ዕርድ እንደሚሄድ የበግ ጠቦት ሆኜ ነበር፤ እነርሱ “ስሙ ዳግመኛ እንዳይታወስ ዛፉን ከነፍሬው እናጥፋ፤ ከሕያዋያን ዓለም እናስወግደው” ብለው በእኔ ላይ ማደማቸውን አላወቅሁም ነበር።

20 እኔም እንዲህ በማለት ጸለይኩ፦ “የሠራዊት አምላክ ሆይ! የሰውን ልብና አእምሮ የምትመረምር አንተ ቅን ፈራጅ ነህ፤ እነሆ ችግሬን ለአንተ አስታወቅሁ፤ ስለዚህም በእነዚህ ሕዝብ ላይ የምትፈጽመውን በቀል እንዳይ አድርገኝ።”

21 “በእግዚአብሔር ስም ትንቢት የተናገርክ እንደ ሆነ እንገድልሃለን” ብለው የኤርምያስን ሕይወት ለማጥፋት ስለሚፈልጉት ስለ አናቶት ሰዎች እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦

22 “እኔ ራሴ እቀጣቸዋለሁ፤ ጐልማሶቻቸው በሰይፍ ያልቃሉ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም በራብ ይሞታሉ።

23 በዐናቶት ሕዝብ ላይ መቅሠፍት የማመጣበት ዘመን ሲደርስ ከእነርሱ መካከል አንድ ሰው እንኳ አይተርፍም።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos