ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስድስተኛ ራእይ 1 ከዚህም ከሰባተኛው ቀን በኋላ በሌሊት ሕልምን አየሁ። 2 እነሆ፥ ጽኑ ነፋስ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ ማዕበሎቹም ሁሉ ታወኩ። 3 ያም ነፋስ በሰው አምሳል ከባሕሩ ሲወጣ አየሁ፤ ከዚህ በኋላ ያ ሰው ከሰማይ ደመናዎች ጋር ወጣ፤ ፊቱንም መልሶ ባየ ጊዜ፥ ሁሉ በጊዜው ጊዜ ወደ እርሱ ይመጣል። 4 ቃሉም በወጣ ጊዜ ከቃሉ የተነሣ ሁሉ ይቀልጣል፤ ቃሉን የሰሙት ሁሉም አደሮ ማር ወደ እሳት በቀረበ ጊዜ እንደሚቀልጥ ይቀልጣሉ። 5 ከዚህ በኋላ ቍጥር የሌላቸው ብዙ ሰዎች ከባሕር የወጣ ይኽን ሰው ይዋጉት ዘንድ ከአራቱ ማዕዘን ሲሰበሰቡ አየሁ። 6 ከዚህ በኋላም ታላቅ ተራራን ሠራ፤ በላዩም ተቀመጠ። 7 ያ ተራራም የተሠራበትን ላውቅ ወደድሁ፤ ነገር ግን አልቻልሁም። 8 ከዚህም በኋላ ይጣሉት ዘንድ የተሰበሰቡት ሁሉ ፈጽመው ፈሩት። ነገር ግን ይዋጉት ዘንድ ደፈሩ። 9 ከዚህም በኋላ በከበቡት ጊዜ፥ ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እጁን በእነርሱ ላይ አላነሣም፤ ጦርን ወይም ማናቸውንም የጦር መሣሪያ አላነሣም። 10 ከአፉ የእሳት ማዕበልን፥ ከከንፈሩም የእሳት ነበልባልን፥ ከአንደበቱም የእሳት ፍምን እንደ ጥቅል ነፋስ አወጣ እንጂ፤ ያ የእሳት ማዕበል፥ ያም የእሳት ነበልባል፥ ያም የእሳት ፍም ሁሉ ተቀላቅሎ እንደ ጥቅል ነፋስ ሆነ። 11 ሊገድሉት በከበቡት በእነዚያ በብዙዎች ላይም ወረደ፤ ከዐመዳቸው ትቢያና ከቃጠሏቸው ጢስ በቀር ከእነርሱ የተረፈ እስከማይኖር ድረስ ሁሉንም አቃጠላቸው። ከዚህም በኋላ ደንግጬ ነቃሁ። 12 ከዚህም በኋላ ያን ሰው ከዚሁ ተራራ ሲወርድ አየሁት፤ ለእርሱ የሚስማሙ ብዙዎች ሌሎችንም ወደ እርሱ ጠራ። 13 ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጡ፤ ከእነርሱም ደስ ያላቸው ነበሩ፤ ከእነርሱም ያዘኑ ነበሩ፤ ከእነርሱም እስረኞች ነበሩ። ከዚህ በኋላ ይህ ሁሉ በደረሰብኝ ጊዜ ደንግጬ ነቃሁ፤ ወደ ልዑልም ጸለይሁ። 14 እንዲህም አልሁ፥ “ቀድሞ አንተ ይህን ጌትነትህን ለባሪያህ አሳየኸው፤ ጸሎቴንም ትሰማ ዘንድ አደረግህልኝ። 15 አሁንም የዚህን የሕልሜን ትርጓሜ ዳግመኛ ንገረኝ። 16 ነገር ግን እኔስ እንደምጠራጠረው በእነዚያ ወራቶች ለሚኖሩ ሰዎች ወዮላቸው! ይልቁንም ላልነበሩት ወዮላቸው! 17 በኋላ ዘመን የሚቈያቸውን ገና ያልደረሰላቸውን ባለማወቅ ያዝናሉና። 18 ላሉት ግን ፈጽመው ስላወቁት ነው። 19 ስለዚህም ወዮላቸው! በዚህ ሕልም እንዳየሁ ታላቅ ጭንቅንና ብዙ ድካምን ያያሉና። 20 ነገር ግን ይህ ሳይደርስ መከራ መቀበል ይሻላል፤ እንደ ደመናም ከዚህ ዓለም ያልፉ ዘንድ ይሻላል፤ በኋላ ዘመን የምታገኛቸውን አያውቁምና።” የራእዩ ትርጓሜ 21 እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “የዚህን የሕልምህን ትርጓሜ እነግርሃለሁ፤ ይህን ያልኸኝንም እተረጕምልሃለሁ። 22 ስለሚቀሩትና ስለሚኖሩት ተናግረሃልና ትርጓሜው እንዲህ ነው። 23 በእነዚያ ወራቶች ያን መከራ የሚያዩት እነዚያ የሚቀሩት ናቸው፤ ያም መከራ የሚያገኛቸውንና በልዑል ዘንድ ሃይማኖትና በጎ ምግባር፥ ጽናትም ያላቸውን እርሱ ራሱ ይጠብቃቸዋል። 24 ነገር ግን ከሞቱት ይልቅ በሕይወት የቀሩት ፈጽመው ብፁዓን እንደ ሆኑ ዕወቅ። 25 የዚህስ የሕልምህ ትርጓሜው እንደዚህ ነው፤ ከባሕር ሲወጣ ያየኸው ይህ ሰው፥ 26 ዓለሙን ሁሉ በእርሱ ያድን ዘንድ ለኋላ ዘመን ልዑል የጠበቀው ይህ ነው። እርሱም የተረፉትን በሥርዐት ያኖራቸዋል። 27 እንደ ጥቅል ነፋስ ከአፉ የእሳት ነበልባል፥ የእሳትም ፍሕም ሲወጣ ያየኸው፥ 28 ጦሩን ወይም የጦር መሣሪያውን ያላነሣ፥ ግን የከበቡትንና ሊገድሉት የመጡትን እነዚያን ብዙዎችን ያጠፋቸው ትርጓሜው እንዲህ ነው። 29 በምድር የሚኖሩትን ልዑል የሚያድንበት ዘመን ይመጣል። 30 ያንጊዜ እርስ በእርሳቸው ይወነጃጀላሉ። 31 ከተማ ከከተማ ጋር፥ ገጠር ከገጠር ጋር፥ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር፥ መንግሥታት ከመንግሥታት ጋር ይዋጋሉ። 32 ይህም በተደረገ ጊዜ፥ ቀድሞ ያሳየሁህ ምልክቱም በደረሰ ጊዜ ያንጊዜ ከባሕር ሲወጣ ያየኸው ያ ሰው ይገለጣል። 33 “አሕዛብም ሁሉ ቃሉን በሰሙ ጊዜ ሀገሮቻቸውና እርስ በርሳቸው የሚጣሉበትን ጠባቸውን ይተዋሉ። 34 ቍጥር የሌላቸው ሰዎች እንዳየሃቸው መጥተው ሊገድሉት ወድደው በአንድነት በዝተው ይሰበሰባሉ። 35 እርሱ ግን በጽዮን ተራራ ራስ ይቆማል። 36 ያለ ሰው እጅ የተፈጠረው ተራራ ሲወጣ እንዳየኸው፥ ጽዮን ትመጣለች፤ ተዘጋጅታና ተሠርታም ለሁሉ ትታያለች፤ 37 እንደ ዓውሎ ነፋስ የሆኑ አሕዛብን በኀጢአታቸው የሚዘልፋቸው እርሱ ወልድ ነው። የሥራቸውንም ክፋት በፊታቸው ይገልጥባቸዋል። እንደ እሳት ነበልባል የሆኑትም በጽኑዕ የሚሠቃዩበትን ይገልጣል። 38 እንደ እሳት ፍም የሆኑትንም ያለ ድካም ከኀጢአታቸው ጋር ያጠፋቸዋል። 39 “ለእርሱ የሚስማሙ ብዙዎች ወደ እርሱ ሲሰበሰቡ ያየኸውም፥ 40 እኒህ በአሦር ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን ካገራቸው የተማረኩ፥ እርሱም በመንግሥቱ የማረካቸው፥ በወንዙ ማዶም ያኖራቸው ዘጠኙ ነገድና የነገድ እኩሌታ ናቸው፤ ተመልሰውም ሌላ ሆኑ። 41 የወገናቸውን ነገድ ይተዉ ዘንድ፥ የሰው ወገን ወደማይኖርበት ሀገርም ይሄዱ ዘንድ እነርሱ ራሳቸው ይህችን ምክር አወጧት። 42 በሀገራቸው ያልጠበቁትን ሕግ ይጠብቁ ዘንድ፥ 43 መግቢያው ጠባብ ወደ ሆነ ወደ ኤፍራጥስም ገቡ። 44 ያንጊዜም ልዑል ተአምር አደረገላቸው፤ የወንዙንም ምንጭ እስኪያልፉ ድረስ አቆመላቸው። 45 ሀገሩ ግን ዓመት ከመንፈቅ ያስሄዳል፤ የሀገሩም ስም አዛፍ ይባላል። 46 “እስከ ኋለኛውም ዘመን ድረስ በዚህ ኖሩ፤ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ ይመለሱ ዘንድ ባላቸው ጊዜ፦ 47 መሻገር ይችሉ ዘንድ የወንዙን ምንጭ ልዑል ዳግመኛ ያቆምላቸዋል። 48 ስለዚህም ስለ አየኸው ነገር ከሕዝቡ አብዛኛዎቹን ይወስዷቸዋል። እነርሱም በከበረው ቦታዬ ይገኛሉ። 49 በእርሱ ላይ የተሰበሰቡ እነዚያን ብዙዎችንም ባጠፋቸው ጊዜ ያንጊዜ የቀሩትን ሕዝብ ያጸናቸዋል። 50 ያንጊዜም ብዙ ምልክቱን ያሳያቸዋል።” 51 እኔም እንዲህ አልሁት፥ “አቤቱ ጌታዬ፥ ይህንም ንገረኝ፤ ከባሕር መካከል ሰው ሲወጣ እኔ ያየሁት ስለ ምንድን ነው?” 52 እንዲህም አለኝ፦ በባሕሩ ጥልቀት ውስጥ ያለውን ማንም ማወቅ እንደማይችል እንደዚሁም በምድር ካሉት ወልድን ማወቅ የሚችል ማንም የለም፤ ሰዓቱና ቀኑ በደረሰ ጊዜ ነው እንጂ፤ ከእርሱም ጋር ያሉት አያውቁትም። 53 ያየኸው የሕልምህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ስለዚህም ለአንተ ብቻ አሳየሁህ። 54 ግዳጅህን ትተህ የእኔን ግዳጅ ተከትለሃልና ሕጌንም ፈልገሃልና። 55 ሕይወትህንም ለዕውቀት አዘጋጅተሃልና፤ ጥበብንም እናት አድርገሃታልና። 56 ስለዚህም ይህን ገለጥሁልህ፤ ዋጋህ በልዑል ዘንድ አለና፥ እንግዲህስ ወዲህ ከጥቂት ቀን በኋላ ና፤ የምነግርህ ሌላ ነገር አለና፥ ድንቅንም እተረጕምልሃለሁና።” 57 በየጊዜው ስለሚያደርገው ስለ ድንቅ ሥራውም እግዚአብሔርን አመሰግነውና አከብረው ዘንድ ወደ ምድረ በዳ አልፌ ሄድሁ። 58 ዘመኖቹን ያዘጋጃቸዋልና፥ ይህንም በየዓመቱ ያደርጋልና። በዚያም ሦስት ቀን ተቀመጥሁ። |