ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ዮዲት 12 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 የራሱ የብር ሳህን ወደሚቀመጥበት ድንኳን እንዲያስገቧት አዘዘ፥ እሱ ከሚመገበው ምግብና እሱ ከሚጠጣው ወይን ጠጅ እንዲሰጧት አዘዛቸው። 2 ዮዲት ግን “እንቅፋት እንዳይሆንብኝ ከእርሱ አልመገብም ነገር ግን ካመጣሁት እህል እመገባለሁ” አለች። 3 ሆሎፎርኒስም “ያመጣሽው ቢያልቅብሽ እንደ እርሱ ያለ ከየት እናመጣልሻለን? ከወገንሽ የሆነ አንድም ከእኛ ጋር የለም” አላት። 4 ዮዲትም “ጌታዬ ሕያው ነፍስህን፤ ጌታ ያቀደውን ነገር በእኔ እጅ ስይፈጽም ይዤው የመጣሁትን ባርያህ አልጨርሰውም” አለችው። 5 የሆሎፎርኒስ አገልጋዮች ወደ ድንኳኑ አስገቧት፥ እስከ እኩለ ሌሊትም ተኛች። በማለዳ ገና ሳይነጋ ተነሣች፤ 6 “እኔ ባርያህ ለጸሎት እንድወጣ እንዲፈቅዱልኝ ጌታዬ ይዘዝ” ብላ ወደ ሆሎፎርኒስ ላከች። 7 ሆሎፎርኒስም እንዳይከለክሏት ዘበኞቹን አዘዛቸው። በሰፈሩ ሦስት ቀን ቆየች፤ በየሌሊቱም ወደ ቤቱሊያ ሸለቆ እየሄደች በሰፈሩ በሚገኘው የምንጭ ውኃ ትታጠብ ነበር። 8 ከወጣችም በኋላ ስለ ሕየዝቡ መዳን መንገድዋን እንዲያቀናላት ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ጌታ ትጸልይ ነበር። 9 ንጹህ ሆና ትመለስ ነበር፥ የማታ ምግብዋ እስኪቀርብላት ድረስ በድንኳንዋ ውስጥ ትቆይ ነበር። ዮዲት በሆሎፎርኒስ ግብዣ ላይ 10 በአራተኛው ቀን ሆሎፎርኒስ ለአሽከሮቹ ብቻ ግብዣ አደረገ፤ ከጦር አለቆቹ ማንንም አልጠራም። 11 የግሉ ጉዳይ አስፈጻሚ የሆነውን ጃንደረባ ባጎስን እንዲህ አለው፦ “ሂድና በአንተ ጥበቃ ሥር ያለችውን ዕብራዊት ሴት ወደ እኛ መጥታ ከእኛ ጋር እንድትበላና እንድትጠጣ አባብልልኝ፤ 12 እንዲህ ያለችውን ሴት ባናነጋግራትና ብንተዋት ለእኛ ውርደት ነው፤ ባንገናኛትም ትስቅብናለች።” 13 ባጎስም ከሆሎፎርኒስ ፊት ወጥቶ ወደ እርሷ ገባ፤ እንዲህም አላት፦ “ወደ ጌታዬ ለመምጣት፥ በፊቱም ለመከበር፥ ከእኛ ጋር ወይን ለመጠጣት፥ ዛሬ በናቡከደነፆር ቤት ከሚያገለግሉ የአሦር ልጆች አንዲቱ ለመሆን ይህች ቆንጆ አታመንታ።” 14 ዮዲትም “ጌታዬን እምቢ እለው ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ለዓይኑ ደስ የሚያሰኘውን ሁሉ ፈጥኜ አደርጋለሁ፤ እስከ ዕለተ ሞቴ ድረስ ይህ ለእኔ ደስታ ነው።” አለችው። 15 ልብስዋን ለመልበስና የሴቶች ጌጣጌጧን ሁሉ ለማድረግ ተነሣች፤ አገልጋይቷም ቀድማ ገባችና በየቀኑ ስትበላ አንጥፋ የምትቀመጥበትን ባጎስ የሰጣትን ምንጣፏን በሆሎፎርኒስ ፊት በምድር ላይ አነጠፈችላት። 16 ዮዲትም ገብታ ተቀመጠች፤ የሆሎፎርኒስ ልብ ተደነቀች፤ ከእርሷም ጋር ለመተኛት ነፍሱ ፈጽማ ታወከች፤ እርሷን ካየበት ቀን ጀምሮ እርሷን ለማሳሳት ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር፤ 17 ሆሎፎርኒስም፦ “ጠጪ፥ ከእኛም ጋር ተደሰቺ” አላት። 18 ዮዲትም፤ “ከተወለድሁ ጀምሮ እስከ ዛሬ ሕይወቴ እንዲህ ከብራ አታውቅምና እጠጣለሁ ጌታዬ” አለችው። 19 አገልጋይዋ ያዘጋጀችላትን ተቀብላ በፊቱ በላች፥ ጠጣችም። 20 ሆሎፎርኒስ በእርሷ ምክንያት ደስ ብሎት ነበርና ከተወለደበት ጀምሮ አንዲት ቀን እንኳ እንደዚህ ያልጠጣውን ብዙ ወይን ጠጅ ጠጣ። |