የርስቱን ትሩፍ ኀጢአት ይቅር የሚል፣ የሚምር እንደ አንተ ያለ አምላክ ማነው? ለዘላለም አትቈጣም፤ ነገር ግን ምሕረት በማድረግ ደስ ይልሃል።
ተመልሰህ ትራራልናለህ፤ ኀጢአታችንን በእግርህ ትረግጣለህ፤ በደላችንንም ሁሉ ወደ ጥልቁ ባሕር ትጥላለህ።
እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት።
ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው። ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤ ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።
“ዘሩ ጥሩ ሆኖ ይበቅላል፤ ወይኑ ፍሬውን ያፈራል፤ ምድሪቱ አዝመራዋን ታበረክታለች፤ ሰማያትም ጠላቸውን ይሰጣሉ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ለቀሪው ሕዝብ ርስት አድርጌ እሰጣለሁ።
“ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ ዳሩ ግን ምንም አያገኙም፤ ጕረሯቸው በውሃ ጥም ደርቋል። ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር እመልስላቸዋለሁ፤ እኔ የእስራኤል አምላክ አልተዋቸውም።
በተራቈቱ ኰረብቶች ላይ ወንዞችን፣ በሸለቆዎች ውስጥ ምንጮችን አፈልቃለሁ። ምድረ በዳውን የውሃ ኵሬ፣ የተጠማውን ምድር የውሃ ምንጭ አደርጋለሁ።
የሐሤትና የደስታ ድምፅ፣ የሙሽራውና የሙሽራዪቱ ድምፅ፣ እንዲሁም፣ “ ‘ “እግዚአብሔር ቸር ነውና፤ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤” የሚል የምስጋናን መሥዋዕት ይዘው ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጡ ሰዎች ድምፅ ይሰማል፤ የምድሪቱን ምርኮ ቀድሞ እንደ ነበረ እመልሳለሁና፤’ ይላል እግዚአብሔር።
ስለዚህ የዛለውን ክንዳችሁንና የደከመውን ጕልበታችሁን አበርቱ።
ዐንካሳው እንዲፈወስ እንጂ የባሰውኑ እንዳያነክስ “ለእግራችሁ ቀና መንገድ አብጁ።”
እርሱም አለ፤ “የአምላካችሁን እግዚአብሔር ድምፅ በጥንቃቄ ብትሰሙ፣ በፊቱም ትክክል የሆነውን ብትፈጽሙ፣ ትእዛዞቹን ልብ ብትሉና ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቁ፣ በግብጻውያን ላይ ያመጣሁባቸውን ማንኛውንም ዐይነት በሽታ በእናንተ ላይ አላመጣም፤ ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝና።”
“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ያዕቆብን አሁን ከስደት እመልሰዋለሁ፤ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እራራለሁ፤ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ።
በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣ በዐመድ ፈንታ፣ የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣ በልቅሶ ፈንታ፣ የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስስላቸው፣ በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣ የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤ እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር የተከላቸው፣ የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።
ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፤ በረሓው ሐሤት ያደርጋል፤ ይፈካል፤ እንደ አደይም ያብባል።
እግዚአብሔር የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤ በዝማሬ ወደ ጽዮን ይገባሉ፤ ዘላለማዊ ደስታን ይጐናጸፋሉ፤ ደስታና ሐሤት ይቀድማሉ፤ ሐዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።
በደስታና በዝማሬ ሐሤት ያደርጋል፤ የሊባኖስ ክብር ይሰጠዋል፤ የቀርሜሎስንና የሳሮንን ግርማ ይለብሳል። የአምላካችንን ታላቅ ግርማ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ያያሉ።
እነሆ፣ ሕዝቤን እስራኤልንና ይሁዳን’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር የምመልስበት ጊዜ ተቃርቧል፤ እነርሱም ይወርሷታል’ ይላል እግዚአብሔር።”
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዚያች ቀን ሽባውን እሰበስባለሁ፤ ስደተኞችንና ለሐዘን ያደረግኋቸውን፣ ወደ አንድ ቦታ አመጣለሁ።
የሽባዎችን ትሩፍ፣ የተገፉትንም ብርቱ ሕዝብ አደርጋለሁ፤ ከዚያች ቀን አንሥቶ እስከ ዘላለም፣ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በእነርሱ ላይ ይነግሣል።
ዐይኔን ለበጎነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በተወደደ ጊዜ እመልስልሃለሁ፤ በድነት ቀን እረዳሃለሁ። ለሕዝቡ ቃል ኪዳን እንድትሆን፣ ምድሪቱን እንደ ገና እንድትሠራት፣ ጠፍ የሆኑትን ርስቶች ለየባለቤታቸው እንድትመልስ፣ እጠብቅሃለሁ፤ እሠራሃለሁም፤
በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ወንዙን ስትሻገረው፣ አያሰጥምህም፤ በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣ አያቃጥልህም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም።
ልዑል እግዚአብሔር የተባ አንደበት ሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ደካሞችን ብርቱ ለማድረግ ምን ማለት እንዳለብኝ ዐውቃለሁ፤ በየማለዳው ያነቃኛል፤ በመማር ላይ እንዳለ ተማሪ ለመስማት ጆሮዬን ያነቃዋል።
“የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛልና፤ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንዳወጣ፣
የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና። ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል።
“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዚህ ሕዝብ ላይ ይህን ሁሉ ታላቅ ጥፋት እንዳመጣሁ እንደዚሁ ቃል የገባሁላቸውን መልካም ነገር ሁሉ እሰጣቸዋለሁ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ድምፅሽን ከልቅሶ፣ ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክይ፤ ድካምሽ ያለ ዋጋ አይቀርምና፤” ይላል እግዚአብሔር። “ከጠላት ምድር ይመለሳሉ፤
“በመካከላችሁ የሰደድሁት ታላቁ ሰራዊት፣ ትልልቁ አንበጣና ትንንሹ አንበጣ፣ ሌሎች አንበጦችና የአንበጣው መንጋ የበላውን፣ እነዚህ ሁሉ የበሏቸውን ዓመታት ዋጋ እመልስላችኋለሁ።
ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጣችሁ፣ የሰላም ሐሳብ እንጂ ለክፉ አይደለም።
ወገኖችህ የቀድሞ ፍርስራሾችን መልሰው ይሠራሉ፤ የጥንቱንም መሠረት ያቆማሉ፤ አንተም፣ የተናዱ ቅጥሮችን ዐዳሽ፣ ባለአውራ መንገድ ከተሞችን ጠጋኝ ትባላለህ።
ሕዝቤ በኀፍረታቸው ፈንታ፣ ዕጥፍ ይቀበላሉ፤ በውርደታቸው ፈንታ፣ በርስታቸው ደስ ይላቸዋል፤ የምድራቸውንም ዕጥፍ ርስት ይወርሳሉ፤ ዘላለማዊ ደስታም የእነርሱ ይሆናል።
በስሜ የተጠራው ሕዝቤ ራሱን አዋርዶ ቢጸልይ፣ ፊቴን ቢፈልግና ከክፉ መንገዱ ቢመለስ፣ ከሰማይ እሰማዋለሁ፤ ኀጢአቱን ይቅር እላለሁ፤ ምድሩንም እፈውሳለሁ።
በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።
“የቀደመውን ነገር አታስቡ፤ ያለፈውን እርሱ።
እነሆ፤ አዲስ ነገር አደርጋለሁ! እርሱም አሁን ይበቅላል፤ አታስተውሉትምን? በምድረ በዳም መንገድ አዘጋጃለሁ፤ በበረሓም ምንጭ አፈልቃለሁ፤
እያለቀሱ ይመጣሉ፤ እያጽናናሁ አመጣቸዋለሁ፤ እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፣ ኤፍሬም በኵር ልጄ ነውና፣ በውሃ ምንጭ ዳር፣ በማይሰናከሉበት ቀና መንገድ እመራቸዋለሁ።
የጠፉትን እፈልጋለሁ፤ የባዘኑትንም እመልሳለሁ። የተጐዱትን እጠግናለሁ፤ የደከሙትንም አበረታለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውን ግን አጠፋለሁ። መንጋውን በፍትሕ እጠብቃለሁ።
እግዚአብሔር የሕዝቡን ስብራት ሲጠግን፣ ያቈሰለውንም ሲፈውስ፣ ጨረቃ እንደ ፀሓይ ታበራለች፤ የፀሓይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት ዕጥፍ ይደምቃል።
እግዚአብሔር አምላክሽ በመካከልሽ አለ፤ እርሱ ብርቱ ታዳጊ ነው፤ በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩ ያሳርፍሻል፤ በዝማሬም በአንቺ ላይ ከብሮ ደስ ይሰኛል።”
ተራሮች ቢናወጡ፣ ኰረብቶች ከስፍራቸው ቢወገዱ እንኳ፣ ለአንቺ ያለኝ ጽኑ ፍቅር አይናወጥም፤ የገባሁትም የሰላም ቃል ኪዳን አይፈርስም” ይላል መሓሪሽ እግዚአብሔር።
የተሰደደውን ሕዝቤን እስራኤልን እመልሳለሁ። “እነርሱም የፈራረሱትን ከተሞች መልሰው ሠርተው በውስጣቸው ይኖራሉ። የወይን ተክል ተክለው፣ ጠጁን ይጠጣሉ፤ አትክልት ተክለው ፍሬውን ይበላሉ።
ኰረዶች ይዘፍናሉ፤ ደስም ይላቸዋል፤ ጐረምሶችና ሽማግሌዎችም ይፈነጥዛሉ፤ ልቅሷቸውን ወደ ደስታ እለውጣለሁ፤ ከሐዘናቸውም አጽናናቸዋለሁ፤ ደስታንም እሰጣቸዋለሁ።
እግዚአብሔር ጽዮንን በርግጥ ያጽናናታል፤ ፍርስራሾቿንም በርኅራኄ ይመለከታል፤ ምድረ በዳዋን እንደ ዔድን፣ በረሓዋንም እንደ እግዚአብሔር ተክል ቦታ ያደርጋል፤ ተድላና ደስታ፣ ምስጋናና የዝማሬ ድምፅ በርሷ ይገኛሉ።
ብዙ መከራና ጭንቅ ብታሳየኝም፣ ሕይወቴን እንደ ገና ታድሳለህ፤ ከምድር ጥልቅም፣ እንደ ገና ታወጣኛለህ።
ክብሬን ትጨምራለህ፤ ተመልሰህም ታጽናናኛለህ።
“የይሁዳን ቤት አበረታለሁ፤ የዮሴፍንም ቤት እታደጋለሁ። ስለምራራላቸው፣ ወደ ቦታቸው እመልሳቸዋለሁ፤ እነርሱም በእኔ እንዳልተተዉ ሰዎች ይሆናሉ፤ እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር ነኝና፣ ጸሎታቸውን እሰማለሁ።