Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘካርያስ 8 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ለመባረክ ቃል ገባ

1 እንደ ገናም የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ጽዮን እጅግ ቀንቻለሁ፤ ስለ እርሷም በቅናት ነድጃለሁ።”

3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ወደ ጽዮን እመለሳለሁ፤ በኢየሩሳሌም እኖራለሁ፤ ኢየሩሳሌምም የእውነት ከተማ ትባላለች፤ የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ተራራም ቅዱስ ተራራ ይባላል።”

4 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሽማግሌዎችና አሮጊቶች እንደ ገና በኢየሩሳሌም አደባባይ ይቀመጣሉ፤ እያንዳንዳቸውም ከዕድሜያቸው ብዛት የተነሣ ምርኵዝ ይይዛሉ።

5 የከተማዪቱም አደባባዮች እዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ።”

6 እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “በዚያ ጊዜ ይህ ለቀረው የእስራኤል ሕዝብ አስደናቂ መስሎ ሊታይ ይችላል፤ ለእኔ ግን አስደናቂ ሊሆን ይችላልን?” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

7 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሕዝቤን ከምሥራቅና ከምዕራብ አገር እታደጋለሁ።

8 በኢየሩሳሌም እንዲኖሩ መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም በጽድቅና በታማኝነት አምላካቸው እሆናለሁ።”

9 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት ሲጣል፣ በዚያ የነበሩ ነቢያት የተናገሩትን ቃል አሁን የምትሰሙ ሁሉ፣ ለመገንባት እጃችሁን አበርቱ።

10 ከዚያ በፊት ለሰው ደመወዝ፣ ለእንስሳም ኪራይ አይከፈልም ነበር፤ ጠላት በመኖሩም ማንም ሥራውን በሰላም ማከናወን አልቻለም፤ እያንዳንዱ ሰው በባልንጀራው ላይ እንዲነሣ አድርጌ ነበርና።

11 አሁን ግን ቀድሞ እንዳደረግሁት በዚህ በቀረው ሕዝብ ላይ አላደርግም” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

12 “ዘሩ ጥሩ ሆኖ ይበቅላል፤ ወይኑ ፍሬውን ያፈራል፤ ምድሪቱ አዝመራዋን ታበረክታለች፤ ሰማያትም ጠላቸውን ይሰጣሉ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ለቀሪው ሕዝብ ርስት አድርጌ እሰጣለሁ።

13 የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፤ በአሕዛብ መካከል የርግማን ምሳሌ ነበራችሁ፤ አሁን ግን አድናችኋለሁ፤ እናንተም በረከት ትሆናላችሁ። አትፍሩ፤ ነገር ግን እጃችሁን አበርቱ።”

14 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አባቶቻችሁ ባስቈጡኝ ጊዜ ያለ አንዳች ሐዘኔታ ጥፋት ላመጣባችሁ እንደ ወሰንሁ፣” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት፤

15 “አሁን ደግሞ ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ መልካም ነገርን ላደርግ ወስኛለሁ፤ አትፍሩ።

16 ልታደርጓቸው የሚገባችሁ ነገሮች እነዚህ ናቸው፤ እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ፤ በአደባባያችሁም እውነትንና ትክክለኛ ፍርድን አስፍኑ፤

17 በባልንጀራችሁ ላይ ክፋትን በልባችሁ አታውጠንጥኑ፤ በሐሰት መማልን አትውደዱ፤ እነዚህን ሁሉ እጸየፋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።

18 እንደ ገናም የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

19 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የአራተኛው፣ የአምስተኛው፣ የሰባተኛውና የዐሥረኛው ወር ጾሞች ለይሁዳ ቤት የደስታ፣ የተድላና የሐሤት በዓላት ይሆናሉ፤ ስለዚህ እውነትንና ሰላምን ውደዱ።”

20 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ብዙ ሕዝቦችና የብዙ ከተሞች ነዋሪዎች ገና ይመጣሉ፤

21 የአንዲቱ ከተማ ነዋሪዎችም፣ ‘እግዚአብሔርን ለመለመን የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ለመፈለግ፣ ኑ፤ በፍጥነት እንሂድ፤ እኔም ራሴ እሄዳለሁ’ እያሉ ወደ ሌላዪቱ ከተማ ይሄዳሉ።

22 ብዙ ሕዝብና ኀያላን መንግሥታትም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ለመፈለግና ለመለመን ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣሉ።”

23 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በእነዚያም ቀናት ከየወገኑና ከየቋንቋው ዐሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ አጥብቀው በመያዝ፣ ‘እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ እንዳለ ሰምተናልና ዐብረን እንሂድ’ ” ይሉታል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች