ሚክያስ 7:18-19የርስቱን ትሩፍ ኀጢአት ይቅር የሚል፣ የሚምር እንደ አንተ ያለ አምላክ ማነው? ለዘላለም አትቈጣም፤ ነገር ግን ምሕረት በማድረግ ደስ ይልሃል።ተመልሰህ ትራራልናለህ፤ ኀጢአታችንን በእግርህ ትረግጣለህ፤ በደላችንንም ሁሉ ወደ ጥልቁ ባሕር ትጥላለህ።
ኢሳይያስ 55:6-7እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት።ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው። ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤ ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።
ዘካርያስ 8:12“ዘሩ ጥሩ ሆኖ ይበቅላል፤ ወይኑ ፍሬውን ያፈራል፤ ምድሪቱ አዝመራዋን ታበረክታለች፤ ሰማያትም ጠላቸውን ይሰጣሉ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ለቀሪው ሕዝብ ርስት አድርጌ እሰጣለሁ።
ኢሳይያስ 41:17-18“ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ ዳሩ ግን ምንም አያገኙም፤ ጕረሯቸው በውሃ ጥም ደርቋል። ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር እመልስላቸዋለሁ፤ እኔ የእስራኤል አምላክ አልተዋቸውም።በተራቈቱ ኰረብቶች ላይ ወንዞችን፣ በሸለቆዎች ውስጥ ምንጮችን አፈልቃለሁ። ምድረ በዳውን የውሃ ኵሬ፣ የተጠማውን ምድር የውሃ ምንጭ አደርጋለሁ።
ዘዳግም 30:3አምላክህ እግዚአብሔር ምርኮህን ይመልስልሃል፤ ይራራልሃልም፤ አንተን ከበተነበት አሕዛብ መካከልም እንደ ገና ይሰበስብሃል።
ኤርምያስ 33:11የሐሤትና የደስታ ድምፅ፣ የሙሽራውና የሙሽራዪቱ ድምፅ፣ እንዲሁም፣ “ ‘ “እግዚአብሔር ቸር ነውና፤ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤” የሚል የምስጋናን መሥዋዕት ይዘው ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጡ ሰዎች ድምፅ ይሰማል፤ የምድሪቱን ምርኮ ቀድሞ እንደ ነበረ እመልሳለሁና፤’ ይላል እግዚአብሔር።
መዝሙር 37:5መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል፤
ኢሳይያስ 46:4እስከ ሽምግልናችሁ፣ እስከ ሽበትም፣ የምሸከማችሁ እኔ ነኝ፤ እኔው ነኝ። ሠርቻችኋለሁ፤ እሸከማችኋለሁ፤ እደግፋችኋለሁ፤ አድናችኋለሁ።
ዕብራውያን 12:12-13ስለዚህ የዛለውን ክንዳችሁንና የደከመውን ጕልበታችሁን አበርቱ።ዐንካሳው እንዲፈወስ እንጂ የባሰውኑ እንዳያነክስ “ለእግራችሁ ቀና መንገድ አብጁ።”
ኤርምያስ 17:14እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈውሰኝ፤ እፈወሳለሁ፤ አድነኝ እኔም እድናለሁ፤ አንተ ምስጋናዬ ነህና።
ዘፀአት 15:26እርሱም አለ፤ “የአምላካችሁን እግዚአብሔር ድምፅ በጥንቃቄ ብትሰሙ፣ በፊቱም ትክክል የሆነውን ብትፈጽሙ፣ ትእዛዞቹን ልብ ብትሉና ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቁ፣ በግብጻውያን ላይ ያመጣሁባቸውን ማንኛውንም ዐይነት በሽታ በእናንተ ላይ አላመጣም፤ ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝና።”
መዝሙር 51:10አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።
ሕዝቅኤል 39:25“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ያዕቆብን አሁን ከስደት እመልሰዋለሁ፤ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እራራለሁ፤ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ።
ኢሳይያስ 54:7“ለጥቂት ጊዜ ተውሁሽ፤ ነገር ግን በታላቅ ርኅራኄ መልሼ እሰበስብሻለሁ።
ሆሴዕ 14:4“እኔ ከዳተኛነታቸውን እፈውሳለሁ፤ እንዲሁ በፈቃደኛነት እወድዳቸዋለሁ፤ ቍጣዬ ከእነርሱ ተመልሷልና።
2 ቆሮንቶስ 4:16ስለዚህ ተስፋ አንቈርጥም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየጠፋ ቢሄድም እንኳ፣ ውስጣዊው ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፤
ኢሳይያስ 61:3በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣ በዐመድ ፈንታ፣ የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣ በልቅሶ ፈንታ፣ የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስስላቸው፣ በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣ የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤ እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር የተከላቸው፣ የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።
ያዕቆብ 5:15በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ጌታም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትም ሠርቶ ከሆነ፣ ይቅር ይባላል።
ኢሳይያስ 35:1-2ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፤ በረሓው ሐሤት ያደርጋል፤ ይፈካል፤ እንደ አደይም ያብባል።እግዚአብሔር የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤ በዝማሬ ወደ ጽዮን ይገባሉ፤ ዘላለማዊ ደስታን ይጐናጸፋሉ፤ ደስታና ሐሤት ይቀድማሉ፤ ሐዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።በደስታና በዝማሬ ሐሤት ያደርጋል፤ የሊባኖስ ክብር ይሰጠዋል፤ የቀርሜሎስንና የሳሮንን ግርማ ይለብሳል። የአምላካችንን ታላቅ ግርማ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ያያሉ።
ሮሜ 8:28እግዚአብሔር፣ ለሚወድዱትና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩት፣ ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን።
ኢሳይያስ 49:13ሰማያት ሆይ፤ እልል በሉ፤ ምድር ሆይ፤ ደስ ይበልሽ፤ ተራሮች ሆይ፤ በደስታ ዘምሩ! እግዚአብሔር ሕዝቡን ያጽናናል፤ ለተቸገሩትም ይራራልና።
ዮሐንስ 10:10ሌባው ሊሰርቅ፣ ሊገድልና ሊያጠፋ ብቻ ይመጣል፤ እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ።
ኤርምያስ 30:3እነሆ፣ ሕዝቤን እስራኤልንና ይሁዳን’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር የምመልስበት ጊዜ ተቃርቧል፤ እነርሱም ይወርሷታል’ ይላል እግዚአብሔር።”
ሚክያስ 4:6-7እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዚያች ቀን ሽባውን እሰበስባለሁ፤ ስደተኞችንና ለሐዘን ያደረግኋቸውን፣ ወደ አንድ ቦታ አመጣለሁ።የሽባዎችን ትሩፍ፣ የተገፉትንም ብርቱ ሕዝብ አደርጋለሁ፤ ከዚያች ቀን አንሥቶ እስከ ዘላለም፣ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በእነርሱ ላይ ይነግሣል።
ኤርምያስ 24:6ዐይኔን ለበጎነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም።
ያዕቆብ 5:16ስለዚህ ኀጢአታችሁን እርስ በርሳችሁ ተናዘዙ፤ ትፈወሱም ዘንድ አንዱ ለሌላው ይጸልይ። የጻድቅ ሰው ጸሎት ኀይል አለው፤ ታላቅ ነገርም ያደርጋል።
ኤርምያስ 33:3‘ወደ እኔ ጩኽ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ አንተም የማታውቀውን ታላቅና የማይመረመር ነገር እገልጥልሃለሁ።’
ኢሳይያስ 49:8እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በተወደደ ጊዜ እመልስልሃለሁ፤ በድነት ቀን እረዳሃለሁ። ለሕዝቡ ቃል ኪዳን እንድትሆን፣ ምድሪቱን እንደ ገና እንድትሠራት፣ ጠፍ የሆኑትን ርስቶች ለየባለቤታቸው እንድትመልስ፣ እጠብቅሃለሁ፤ እሠራሃለሁም፤
2 ሳሙኤል 22:31“የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው፤ የእግዚአብሔርም ቃል የነጠረ ነው፤ መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻ ነው።
ራእይ 21:5በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም፣ “እነሆ፤ እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ” አለ፤ ደግሞም፣ “ይህ ቃል የታመነና እውነት ስለ ሆነ ጻፍ” አለ።
መዝሙር 46:1አምላካችን መጠጊያችንና ኀይላችን፣ በሚደርስብን መከራ ሁሉ የቅርብ ረዳታችን ነው።
ሮሜ 15:13በርሱ በመታመናችሁ የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ፤ ይኸውም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተስፋ ተትረፍርፎ እንዲፈስስላችሁ ነው።
ኢሳይያስ 43:2በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ወንዙን ስትሻገረው፣ አያሰጥምህም፤ በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣ አያቃጥልህም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም።
ኢሳይያስ 65:17“እነሆ፤ እኔ፣ አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ፤ ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም።
ሉቃስ 6:21እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፤ ኋላ ትጠግባላችሁና፤ እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፤ ኋላ ትሥቃላችሁና፤
ኢሳይያስ 50:4ልዑል እግዚአብሔር የተባ አንደበት ሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ደካሞችን ብርቱ ለማድረግ ምን ማለት እንዳለብኝ ዐውቃለሁ፤ በየማለዳው ያነቃኛል፤ በመማር ላይ እንዳለ ተማሪ ለመስማት ጆሮዬን ያነቃዋል።
ሉቃስ 4:18“የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛልና፤ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንዳወጣ፣
መዝሙር 71:20ብዙ መከራና ጭንቅ ብታሳየኝም፣ ሕይወቴን እንደ ገና ታድሳለህ፤ ከምድር ጥልቅም፣ እንደ ገና ታወጣኛለህ።
ኢሳይያስ 61:1የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና። ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል።
ኤርምያስ 32:42“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዚህ ሕዝብ ላይ ይህን ሁሉ ታላቅ ጥፋት እንዳመጣሁ እንደዚሁ ቃል የገባሁላቸውን መልካም ነገር ሁሉ እሰጣቸዋለሁ።
ማቴዎስ 11:28“እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ።
ኢሳይያስ 52:9እናንተ የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች፣ በአንድነት በእልልታ ዘምሩ፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቷል፤ ኢየሩሳሌምንም ተቤዥቷልና።
መዝሙር 55:22የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤ የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም።
ሰቈቃወ 3:22-23ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና።ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህም ብዙ ነው።
ኤርምያስ 31:16እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ድምፅሽን ከልቅሶ፣ ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክይ፤ ድካምሽ ያለ ዋጋ አይቀርምና፤” ይላል እግዚአብሔር። “ከጠላት ምድር ይመለሳሉ፤
መዝሙር 51:17እግዚአብሔር የሚቀበለው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም።
ኢዩኤል 2:25“በመካከላችሁ የሰደድሁት ታላቁ ሰራዊት፣ ትልልቁ አንበጣና ትንንሹ አንበጣ፣ ሌሎች አንበጦችና የአንበጣው መንጋ የበላውን፣ እነዚህ ሁሉ የበሏቸውን ዓመታት ዋጋ እመልስላችኋለሁ።
ዘካርያስ 9:12እናንተ በተስፋ የምትኖሩ እስረኞች፤ ወደ ምሽጎቻችሁ ተመለሱ፤ አሁንም ቢሆን ሁለት ዕጥፍ አድርጌ እንደምመልስላችሁ እናገራለሁ።
ኤርምያስ 29:11ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጣችሁ፣ የሰላም ሐሳብ እንጂ ለክፉ አይደለም።
ኢዮብ 42:10ኢዮብ ለወዳጆቹ ከጸለየ በኋላ፣ እግዚአብሔር እንደ ገና አበለጸገው፤ ቀድሞ በነበረው ፈንታ ዕጥፍ አድርጎ ሰጠው።
ኢሳይያስ 40:31እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።
2 ቆሮንቶስ 5:17ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር ዐልፏል፤ እነሆ፤ አዲስ ሆኗል።
መዝሙር 80:3አምላክ ሆይ፤ መልሰን፤ እንድንም ዘንድ፣ ፊትህን አብራልን።
ሆሴዕ 6:1“ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰባብሮናል፤ እርሱም ይጠግነናል፤ እርሱ አቍስሎናል፤ እርሱም ይፈውሰናል።
ኢሳይያስ 60:1“ብርሃንሽ መጥቷልና ተነሺ አብሪ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻል።
ኢሳይያስ 58:12ወገኖችህ የቀድሞ ፍርስራሾችን መልሰው ይሠራሉ፤ የጥንቱንም መሠረት ያቆማሉ፤ አንተም፣ የተናዱ ቅጥሮችን ዐዳሽ፣ ባለአውራ መንገድ ከተሞችን ጠጋኝ ትባላለህ።
ኤርምያስ 30:17አንተን ግን መልሼ ጤነኛ አደርግሃለሁ፤ ቍስልህንም እፈውሳለሁ፤’ ይላል እግዚአብሔር። ‘የተናቀች ማንም የማይፈልጋት ጽዮን’ ብለውሃልና።
ኢሳይያስ 61:7ሕዝቤ በኀፍረታቸው ፈንታ፣ ዕጥፍ ይቀበላሉ፤ በውርደታቸው ፈንታ፣ በርስታቸው ደስ ይላቸዋል፤ የምድራቸውንም ዕጥፍ ርስት ይወርሳሉ፤ ዘላለማዊ ደስታም የእነርሱ ይሆናል።
2 ዜና መዋዕል 7:14በስሜ የተጠራው ሕዝቤ ራሱን አዋርዶ ቢጸልይ፣ ፊቴን ቢፈልግና ከክፉ መንገዱ ቢመለስ፣ ከሰማይ እሰማዋለሁ፤ ኀጢአቱን ይቅር እላለሁ፤ ምድሩንም እፈውሳለሁ።
ኢሳይያስ 57:18መንገዶቹን አይቻለሁ፤ ቢሆንም እፈውሰዋለሁ፤ እመራዋለሁ፤ ለርሱና ስለ እርሱ ለሚያለቅሱትም መጽናናትን እመልሳለሁ፤
1 ጴጥሮስ 5:10በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።
መዝሙር 23:3ነፍሴንም ይመልሳታል። ስለ ስሙም፣ በጽድቅ መንገድ ይመራኛል።
ሕዝቅኤል 36:26አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ የድንጋይ ልባችሁን ከእናንተ አስወግዳለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ።
ኤርምያስ 33:6“ ‘ይሁን እንጂ፣ ፈውስንና ጤንነትን እንደ ገና እሰጣታለሁ፤ ሕዝቤንም እፈውሳለሁ፤ በብዙ ሰላምና በርጋታ እንዲኖሩ አደርጋለሁ።
ኢሳይያስ 43:18-19“የቀደመውን ነገር አታስቡ፤ ያለፈውን እርሱ።እነሆ፤ አዲስ ነገር አደርጋለሁ! እርሱም አሁን ይበቅላል፤ አታስተውሉትምን? በምድረ በዳም መንገድ አዘጋጃለሁ፤ በበረሓም ምንጭ አፈልቃለሁ፤
መዝሙር 103:5ጕልማሳነትሽም እንደ ንስር ይታደስ ዘንድ፣ ምኞትሽን በበጎ ነገር የሚያረካ እርሱ ነው።
ኢዩኤል 3:1“በዚያ ዘመን፣ በዚያ ጊዜ፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮ ስመልስ፣
ሕዝቅኤል 37:5ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ፤ ዐጥንቶች እንዲህ ይላል፤ እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፤ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ።
ኤርምያስ 31:4የእስራኤል ድንግል ሆይ፤ እንደ ገና ዐንጽሻለሁ፤ አንቺም ትታነጺአለሽ፤ ከበሮችሽንም እንደ ገና አንሥተሽ፣ ከሚፈነጥዙት ጋራ ትፈነድቂአለሽ።
1 ጴጥሮስ 5:7እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በርሱ ላይ ጣሉት።
ኢሳይያስ 57:19በእስራኤል አልቃሾች ከንፈር ላይ ምስጋና እፈጥራለሁ። በቅርብና በሩቅ ላሉት ሰላም፣ ሰላም ይሁን፤ እኔ እፈውሳቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።
መዝሙር 85:6ሕዝብህ በአንተ ሐሤት ያደርግ ዘንድ፣ መልሰህ ሕያዋን አታደርገንምን?
ኢዩኤል 2:21ምድር ሆይ፤ አትፍሪ፤ ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ፤ በርግጥ እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አድርጓል።
ኤርምያስ 31:9እያለቀሱ ይመጣሉ፤ እያጽናናሁ አመጣቸዋለሁ፤ እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፣ ኤፍሬም በኵር ልጄ ነውና፣ በውሃ ምንጭ ዳር፣ በማይሰናከሉበት ቀና መንገድ እመራቸዋለሁ።
ኢሳይያስ 44:22መተላለፍህን እንደ ደመና፣ ኀጢአትህን እንደ ማለዳ ጭጋግ ጠርጌ አስወግጃለሁ፤ ተቤዥቼሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ።”
ሰቈቃወ 5:21እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞው አድስ፤
ኢሳይያስ 55:12በደስታ ትወጣላችሁ፤ በሰላምም ትሸኛላችሁ፤ ተራሮችና ኰረብቶች፣ በፊታችሁ በእልልታ ይዘምራሉ፤ የሜዳ ዛፎች ሁሉ፣ ያጨበጭባሉ።
ሕዝቅኤል 34:16የጠፉትን እፈልጋለሁ፤ የባዘኑትንም እመልሳለሁ። የተጐዱትን እጠግናለሁ፤ የደከሙትንም አበረታለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውን ግን አጠፋለሁ። መንጋውን በፍትሕ እጠብቃለሁ።
ኢሳይያስ 30:26እግዚአብሔር የሕዝቡን ስብራት ሲጠግን፣ ያቈሰለውንም ሲፈውስ፣ ጨረቃ እንደ ፀሓይ ታበራለች፤ የፀሓይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት ዕጥፍ ይደምቃል።
ሶፎንያስ 3:17እግዚአብሔር አምላክሽ በመካከልሽ አለ፤ እርሱ ብርቱ ታዳጊ ነው፤ በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩ ያሳርፍሻል፤ በዝማሬም በአንቺ ላይ ከብሮ ደስ ይሰኛል።”
ኢሳይያስ 54:10ተራሮች ቢናወጡ፣ ኰረብቶች ከስፍራቸው ቢወገዱ እንኳ፣ ለአንቺ ያለኝ ጽኑ ፍቅር አይናወጥም፤ የገባሁትም የሰላም ቃል ኪዳን አይፈርስም” ይላል መሓሪሽ እግዚአብሔር።
ኤርምያስ 32:27“እነሆ፤ እኔ የሰው ልጆች ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ በውኑ የሚያቅተኝ ነገር አለን?
አሞጽ 9:14የተሰደደውን ሕዝቤን እስራኤልን እመልሳለሁ። “እነርሱም የፈራረሱትን ከተሞች መልሰው ሠርተው በውስጣቸው ይኖራሉ። የወይን ተክል ተክለው፣ ጠጁን ይጠጣሉ፤ አትክልት ተክለው ፍሬውን ይበላሉ።
ኢሳይያስ 41:10እኔ ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።
መዝሙር 30:11ዋይታዬን ወደ ሽብሸባ ለወጥህልኝ፤ ማቄን አውልቀህ ፍሥሓን አለበስኸኝ፤
ኤርምያስ 31:13ኰረዶች ይዘፍናሉ፤ ደስም ይላቸዋል፤ ጐረምሶችና ሽማግሌዎችም ይፈነጥዛሉ፤ ልቅሷቸውን ወደ ደስታ እለውጣለሁ፤ ከሐዘናቸውም አጽናናቸዋለሁ፤ ደስታንም እሰጣቸዋለሁ።
ኢሳይያስ 51:3እግዚአብሔር ጽዮንን በርግጥ ያጽናናታል፤ ፍርስራሾቿንም በርኅራኄ ይመለከታል፤ ምድረ በዳዋን እንደ ዔድን፣ በረሓዋንም እንደ እግዚአብሔር ተክል ቦታ ያደርጋል፤ ተድላና ደስታ፣ ምስጋናና የዝማሬ ድምፅ በርሷ ይገኛሉ።
መዝሙር 71:20-21ብዙ መከራና ጭንቅ ብታሳየኝም፣ ሕይወቴን እንደ ገና ታድሳለህ፤ ከምድር ጥልቅም፣ እንደ ገና ታወጣኛለህ።ክብሬን ትጨምራለህ፤ ተመልሰህም ታጽናናኛለህ።
ዘካርያስ 10:6“የይሁዳን ቤት አበረታለሁ፤ የዮሴፍንም ቤት እታደጋለሁ። ስለምራራላቸው፣ ወደ ቦታቸው እመልሳቸዋለሁ፤ እነርሱም በእኔ እንዳልተተዉ ሰዎች ይሆናሉ፤ እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር ነኝና፣ ጸሎታቸውን እሰማለሁ።
ኤርምያስ 3:22“እናንተ ከዳተኞች ልጆች ተመለሱ፤ ከዳተኝነታችሁን እፈውሳለሁ። “አንተ እግዚአብሔር አምላካችን ነህና፤ አዎን፤ ወደ አንተ እንመጣለን።