Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ራእይ 21 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


አዲሲቱ ኢየሩሳሌም

1 ከዚህ በኋላ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የመጀመሪያው ሰማይና የመጀመሪያዪቱ ምድር ዐልፈዋልና፤ ባሕርም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።

2 ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባሏ እንደ ተዋበች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ።

3 ደግሞም እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ከዙፋኑ ሲወጣ ሰማሁ፤ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋራ ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋራ ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል።

4 እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፏልና።”

5 በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም፣ “እነሆ፤ እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ” አለ፤ ደግሞም፣ “ይህ ቃል የታመነና እውነት ስለ ሆነ ጻፍ” አለ።

6 እንዲህም አለኝ፤ “ተፈጸመ፤ አልፋና ዖሜጋ፣ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ፤ ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ ያለ ዋጋ እሰጣለሁ።

7 ድል የሚነሣ ይህን ሁሉ ይወርሳል፤ እኔም አምላክ እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል።

8 ነገር ግን ፈሪዎች፣ የማያምኑ፣ ርኩሶች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝሮች፣ አስማተኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ውሸተኞች ሁሉ ዕጣ ፈንታቸው በዲንና በእሳት ባሕር ውስጥ መጣል ይሆናል። ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።”

9 ሰባቱ የመጨረሻ መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ፣ “ና፤ የበጉ ሚስት የሆነችውን ሙሽራ አሳይሃለሁ” አለኝ።

10 በመንፈስም ወደ አንድ ትልቅና ረዥም ተራራ ወስዶኝ፣ ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ።

11 እርሷም በእግዚአብሔር ክብር ታበራ ነበር፤ የብርሃኗም ድምቀት እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ፣ እንደ መስተዋት የጠራ ነበር።

12 ዐሥራ ሁለት በሮች የነበሩት ትልቅና ረዥም ቅጥርም ነበራት፤ በበሮቹም ላይ ዐሥራ ሁለት መላእክት ቆመውና የዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ስም ተጽፎ ነበር።

13 በምሥራቅ ሦስት በሮች፣ በሰሜን ሦስት በሮች፣ በደቡብ ሦስት በሮች፣ በምዕራብ ሦስት በሮች ነበሩ።

14 የከተማዪቱም ቅጥር ዐሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩት፤ በእነርሱም ላይ የዐሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር።

15 ከእኔ ጋራ ይነጋገር የነበረው መልአክ የከተማዪቱን በሮች ቅጥር የሚለካበት የወርቅ ዘንግ ነበረው።

16 ከተማዪቱም ርዝመቷና ስፋቷ እኩል ሆኖ አራት ማእዘን ነበረች። እርሱም ከተማዪቱን በዘንጉ ለካ፤ ርዝመቷም ዐሥራ ሁለት ሺሕ ምዕራፍ ሆነ፤ ስፋቷና ከፍታዋም እንዲሁ ሆነ።

17 ደግሞም የከተማዪቱን ቅጥር ለካ፤ ርዝመቱም የመልአክ መለኪያ በሆነው በሰው መለኪያ መቶ አርባ አራት ክንድ ነበር።

18 ቅጥሩ የተሠራው ከኢያሰጲድ ነበር፤ ከተማዪቱም እንደ መስተዋት ንጹሕ ከሆነ ወርቅ የተሠራች ነበረች።

19 የከተማዪቱ ቅጥር መሠረቶች በሁሉም ዐይነት የከበረ ድንጋይ ያጌጡ ነበር፤ የመጀመሪያው መሠረት ኢያሰጲድ፣ ሁለተኛው ሰንፔር፣ ሦስተኛው ኬልቄዶን፣ አራተኛው መረግድ፣

20 ዐምስተኛው ሰርዶንክስ፣ ስድስተኛው ሰርድዮን፣ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፣ ስምንተኛው ቢረሌ፣ ዘጠነኛው ወራውሬ፣ ዐሥረኛው ክርስጵራስስ፣ ዐሥራ አንደኛው ያክንት፣ ዐሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ።

21 ዐሥራ ሁለቱም በሮች ዐሥራ ሁለት ዕንቍዎች ነበሩ፤ እያንዳንዱም በር ከአንድ ዕንየተሠራ ነበረ። የከተማዪቱም አውራ መንገድ እንደ መስተዋት ብርሃን የሚያስተላልፍ ንጹሕ ወርቅ ነበረ።

22 ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክና በጉ መቅደሷ ስለ ሆኑ፣ በከተማዪቱ ውስጥ ቤተ መቅደስ አላየሁም።

23 የእግዚአብሔር ክብር ብርሃን ስለሚሰጣትና በጉም መብራቷ ስለ ሆነ፣ ከተማዋ ፀሓይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጋትም።

24 ሕዝቦች በብርሃኗ ይመላለሳሉ፤ የምድር ነገሥታትም ክብራቸውን ወደ እርሷ ያመጣሉ።

25 በዚያ ሌሊት ስለሌለ፣ በሮቿ በየትኛውም ቀን አይዘጉም።

26 የሕዝቦች ግርማና ክብር ወደ እርሷ ይገባል።

27 በበጉ የሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፣ ርኩሰትን የሚያደርግና ውሸትን የሚናገር ሁሉ አይገባባትም።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች