ነህምያ 8:6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ሕዝቡም ሁሉ እጃቸውን እየዘረጉ፥ “አሜን፥ አሜን” ብለው መለሱ። ራሳቸውንም አዘነበሉ፤ በግንባራቸውም ወደ ምድር ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ሕዝቡም ሁሉ እጆቻቸውን በማንሣት፣ “አሜን! አሜን!” ብለው መለሱ፤ ከዚህ በኋላ በግምባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ዕዝራም ታላቁን አምላክ ጌታን ባረከ፤ ሕዝቡም ሁሉ እጆቻቸውን በመዘርጋት፦ አሜን፥ አሜን ብለው መለሱ። ራሳቸውን አዘነበሉ፥ በግምባራቸውም ተደፍተው ለጌታ ሰገዱ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገነ። ሁሉም እጆቻቸውን ወደ ላይ በማንሣት “አሜን! አሜን!” ሲሉ መለሱ፤ ወደ ምድርም ለጥ ብለው ለእግዚአብሔር ሰገዱ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ ሕዝቡም ሁሉ እጃቸውን እየዘረጉ፦ አሜን፥ አሜን ብለው መለሱ። ራሳቸውንም አዘነበሉ፥ በግምባራቸውም ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ። |
ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም፥ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ። ሕዝቡ ሁሉ አሜን ይበሉ፤ እግዚአብሔርንም ያመስግኑ።
ንጉሡ ዳዊትም በጉባኤው ሁሉ ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ እንዲህም አለ፥ “አቤቱ፥ የእስራኤል አምላክ አባታችን እግዚአብሔር ሆይ፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ቡሩክ ነህ።
ዳዊትም ጉባኤውን ሁሉ፥ “አምላካችን እግዚአብሔርን አመስግኑ” አላቸው። ጉባኤውም ሁሉ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፥ በጕልበታቸውም ተንበርክከው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ ደግሞም ለንጉሡ።
ኢዮሣፍጥም በምድር ላይ ሰገደ፤ ይሁዳም ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ በእግዚአብሔር ፊት ወደቁ፤ ለእግዚአብሔርም ሰገዱ።
አሁንም የቍጣውን መቅሠፍት ከእኛ እንዲመልስ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን አደርግ ዘንድ በልቤ አስቤአለሁ።
ንጉሡ ሕዝቅያስና አለቆቹም በዳዊትና በነቢዩ በአሳፍ ቃል እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ሌዋውያንን አዘዙ። በደስታም አመሰገኑ፤ አጐነበሱም፤ ሰገዱም።
ደግሞም ልብሴን አራገፍሁና፥ “ይህን ነገር የማያደርገውን ሰው ከቤቱና ከሥራው እንዲሁ እግዚአብሔር ያራግፈው፤ እንዲሁ የተራገፈና ባዶ ይሁን” አልሁ። ጉባኤውም ሁሉ፥ “አሜን” አሉ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፤ ሕዝቡም እንደዚህ ነገር አደረጉ።
ደግሞ ኢያሱና ባኒ፥ ሰራብያ፥ ያሚን፥ ዓቁብ፥ ሳባታይ፥ ሆዲያ፥ መዕሤያ፥ ቆሊጣ፥ ዓዛርያ፥ ኢዮዛባድ፥ ሐናን፥ ፌልዕያ፥ ሌዋውያኑም ሕጉን ለሕዝቡ ያስተምሩ ነበር፤ ሕዝቡም በየስፍራቸው ቆመው ነበር።
‘ይህ በግብፅ ሀገር የእስራኤልን ልጆች ቤቶች ሰውሮ ግብፃውያንን በመታ ጊዜ፥ ቤቶቻችንን የአዳነ የእግዚአብሔር የፋሲካው መሥዋዕት ነው’ ትሉአቸዋላችሁ።” ሕዝቡም ተጐነበሱ፤ ሰገዱም።
ሕዝቡም አመኑ፤ ደስም አላቸው፤ እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ጐብኝቶአልና፤ ጭንቀታቸውንም አይቶአልና፤ ሕዝቡም ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሰገዱ።
ነቢዩም ኤርምያስ እንዲህ አለ፥ “አሜን፥ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግ፤ የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ፥ ምርኮውንም ሁሉ ከባቢሎን ወደዚህ ስፍራ በመመለስ እግዚአብሔር የተናገርኸውን ትንቢት ይፈጽም።
እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ ስቡንም በላ፤ ሕዝቡም ሁሉ አይተው ተደነቁ፤ በግምባራቸውም ወደቁ።
ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ “አባቴ! ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን፤” አለ።
አንተ በመንፈስ ብታመሰግን፥ ያ የቆመው ያልተማረው በአንተ ምስጋና ላይ እንዴት አሜን ይላል? የምትናገረውንና የምትጸልየውን አያውቅምና።
በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን።
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኀይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል።