ዘፀአት 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ተአምራዊ ኀይል 1 ሙሴም መለሰ፥ “እነሆ፥ ባያምኑኝ፥ ቃሌንም ባይሰሙ፦ ‘እግዚአብሔርም አልተገለጠልህም’ ቢሉኝ ምን እላቸዋለሁ?” አለ። 2 እግዚአብሔርም፥ “ይህ በእጅህ ያለው ምንድን ነው?” አለው። እርሱም፥ “በትር ነው” አለ። 3 “ወደ መሬት ጣለው” አለው፤ እርሱም በመሬት ጣለው፤ እባብም ሆነ፤ ሙሴም ከእርሱ ሸሸ። 4 እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “እጅህን ዘርግተህ ጅራቱን ያዝ” አለው፤ ሙሴም እጁን ዘርግቶ፥ ጅራቱን ይዞ፥ አነሣው በእጁም በትር ሆነ። 5 እግዚአብሔርም፥ “የአባቶቻቸው አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ፥ የያዕቆብም አምላክ እንደ ታየህ ያምኑሃል” አለው። 6 ዳግመኛም እግዚአብሔር፥ “እጅህን ወደ ብብትህ አግባ አለው።” እጁንም ወደ ብብቱ አገባት፤ “እጅህንም ከብብትህ አውጣ” አለው፤ እጁንም ከብብቱ አወጣ፤ እጁም ለምጽ ሆነች። 7 ዳግመኛም፥ “እጅህን ወደ ብብትህ መልስ” አለው። እጁንም ወደ ብብቱ መለሳት፤ “እጅህን ከብብትህ አውጣ” አለው፤ እጁንም ከብብቱ አወጣ፤ ተመልሳም ገላውን መሰለች። 8 ደግሞም አለው፥ “እንዲህም ይሆናል፤ ባያምኑህ፥ በፊተኛዪቱም ምልክት ቃልህን ባይሰሙ፥ በሁለተኛዪቱ ምልክት ቃልህን ያምናሉ። 9 እንዲህም ይሆናል፤ እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ፥ ቃልህንም ባይሰሙ፥ ከወንዙ ውኃን ውሰድ፤ በደረቁም መሬት ላይ አፍስሰው፤ ከወንዙም የወሰድኸው ውኃ በደረቁ መሬት ላይ ደም ይሆናል።” 10 ሙሴም እግዚአብሔርን አለው፥ “ጌታ ሆይ፥ እማልድሃለሁ፤ ትናንት፥ ከትናንት ወዲያ ባሪያህን ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም። እኔ አፌ ኰልታፋ፥ ምላሴም ተብታባ የሆነ ሰው ነኝ።” 11 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ለሰው አፍን የሰጠ ማን ነው? ዲዳስ፥ ደንቆሮስ፥ የሚያይስ፥ ዕውርስ የሚያደርግ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? 12 እንግዲህ አሁን ሂድ፤ እኔም አንደበትህን አረታለሁ፤ ትናገረውም ዘንድ ያለህን አለብምሃለሁ” አለው። 13 ሙሴም፥ “ጌታ ሆይ፥ እማልድሃለሁ፤ መናገር የሚችል የምትልከው ሌላ ሰው ፈልግ” አለው። 14 እግዚአብሔርም በሙሴ ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እንዲህም አለ፥ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ እንደሚናገርልህ አውቃለሁ፤ እነሆም፥ እርሱ ሊገናኝህ ይመጣል፤ በአየህም ጊዜ በልቡ ደስ ይለዋል። 15 አንተም ትናገረዋለህ፤ ቃሌንም በአፉ ታደርገዋለህ፤ እኔ አንደበትህንና አንደበቱን አረታለሁ፤ የምታደርጉትንም አለብማችኋለሁ። 16 እርሱ ስለ አንተ ከሕዝቡ ጋር ይነጋገራል፤ እርሱ አፍ ይሆንልሃል፤ አንተም በእግዚአብሔር ዘንድ ትሆንለታለህ። 17 ይህችንም ተአምራት የምታደርግባትን በትር በእጅህ ያዝ።” የሙሴ ወደ ግብፅ መመለስ 18 ሙሴም ሄደ፤ ወደ አማቱ ወደ ዮቶርም ተመለሰ፥ “እስከ ዛሬ በሕይወት እንደ አሉ አይ ዘንድ ተመልሼ ወደ ግብፅ ወደ ወንድሞች እሄዳለሁ” አለው። ዮቶርም ሙሴን፥ “በደኅና ሂድ” አለው። 19 ከብዙ ዘመንም በኋላ የግብፅ ንጉሥ ሞተ። እግዚአብሔርም ሙሴን በምድያም፥ “ነፍስህን የሚሹአት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብፅ ሂድ” አለው። 20 ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወሰደ፤ በአህዮች ላይም አስቀመጣቸው፤ ወደ ግብፅም ሀገር ተመለሰ፤ ሙሴም ያችን የእግዚአብሔርን በትር በእጁ ይዞ ሄደ። 21 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ወደ ግብፅ ተመልሰህ ስትሄድ በእጅህ ያደረግሁትን ተአምራቴን ሁሉ በፈርዖን ፊት ታደርገው ዘንድ ተመልከት፤ እኔ ግን ልቡን አጸናዋለሁ፤ ሕዝቡንም አይለቅቅም። 22 አንተ ግን ፈርዖንን እንዲህ ትለዋለህ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ 23 ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ አልሁህ፤ አንተም ልትለቅቃቸው ባትፈቅድ፤ እኔ የበኵር ልጅህን እንደምገድል ዕወቅ።” 24 እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ በአደረበት ስፍራ የእግዚአብሔር መልአክ ተገናኘው፤ ሊገድለውም ፈለገ። 25 ሚስቱ ሲፓራም ባልጩት ወሰደች፤ የልጅዋንም ሸለፈት ገረዘች፤ “ይህ የልጄ የግርዛቱ ደም ስለ እርሱ ፈንታ ይሁን” ብላ ከእግሩ በታች ወደቀች። 26 ከእርሱም ሄደ፤ የዚያ ጊዜ፥ “ይህ የልጄ የግርዛቱ ደም ስለ እርሱ ፈንታ ይሁን” ብላለችና። 27 እግዚአብሔርም አሮንን አለው፥ “ሄደህ በምድረ በዳ ሙሴን ተገናኘው፤” ሄዶም በእግዚአብሔር ተራራ ተገናኘው፤ እርስ በርሳቸውም ተሳሳሙ። 28 ሙሴም እግዚአብሔር የላከውን ቃል ሁሉ፥ የአዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ለአሮን ነገረው። 29 ሙሴና አሮንም ሄዱ፤ የእስራኤልንም ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰቡ። 30 አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረውን ቃል ሁሉ ተናገረ፤ ተአምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። 31 ሕዝቡም አመኑ፤ ደስም አላቸው፤ እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ጐብኝቶአልና፤ ጭንቀታቸውንም አይቶአልና፤ ሕዝቡም ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሰገዱ። |