መዝሙር 134 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሃሌ ሉያ። 1 የእግዚአብሔርን ስም አመስግኑ፤ እናንተ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሆይ፥ አመስግኑት። 2 በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ፥ በአምላካችን ቤት አደባባይ የምትቆሙ። 3 እግዚአብሔር ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ለስሙ ዘምሩ፥ መልካም ነውና፤ 4 እግዚአብሔር ያዕቆብን ለራሱ፥ እስራኤልንም ርስቱ እንዲሆን መርጦታልና፤ 5 እግዚአብሔር ታላቅ እንደ ሆነ፥ አምላካችንም ከአማልክት ሁሉ እንዲበልጥ አውቃለሁና። 6 በሰማይና በምድር፥ በባሕርና በጥልቆችም ሁሉ፥ እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ። 7 ከምድር ዳር ደመናትን ያወጣል፤ ለዝናም ጊዜም መብረቅን አደረገ፤ ነፋሳትንም ከመዛግብቱ ያወጣል። 8 የግብፅን በኵር ልጆች ሁሉ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ገደለ። 9 ግብፅ ሆይ፥ በመካከልሽ በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ ላይ ተአምራትንና ድንቅን ሰደደ። 10 ብዙ አሕዛብን መታ፥ ብርቱዎችንም ነገሥታት ገደለ። 11 የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ የባሳንንም ንጉሥ ዐግን፥ የከነዓንን ነገሥታት ሁሉ ገደለ፤ 12 ርስት ምድራቸውንም ለሕዝቡ ለእስራኤል ርስት አድርጎ ሰጠ። 13 አቤቱ፥ ስምህ ለዘለዓለም ነው፥ መታሰቢያህም ለልጅ ልጅ ነው፤ 14 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳልና፥ ባሪያዎቹንም ያጽናናልና። 15 የአሕዛብ ጣዖታት የብርና የወርቅ፥ የሰው እጅ ሥራ ናቸው። 16 አፍ አላቸው፥ ግን አይናገሩም፤ ዐይን አላቸው፥ ግን አያዩም፤ 17 ጆሮ አላቸው፥ ግን አይሰሙም፤ አፍንጫ አላቸው፥ ግን አያሸቱም፤ እጅ አላቸው፥ ግን አይዳስሱም፤ እግር አላቸው፥ ግን አይሄዱም፤ በጕሮሮአቸው አይናገሩም፥ እስትንፋስም በአፋቸው የለም። 18 የሚሠሩአቸው ሁሉ፥ የሚታመኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ። 19 የእስራኤል ወገኖች ሆይ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ የአሮን ወገኖች ሆይ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ 20 የሌዊ ወገኖች ሆይ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑት። 21 በኢየሩሳሌም የሚያድር እግዚአብሔር በጽዮን የተመሰገነ ነው። |