ነህምያ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በወንድሞቻቸውም በአይሁድ ላይ ትልቅ የሕዝቡና የሚስቶቻቸው ጩኸት ሆነ። 2 “ከወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ጋር ብዙዎች ነን፤ በልተንም በሕይወት እንድንኖር እህልን እንሸምት” የሚሉ ነበሩ። 3 “ከራብ የተነሣም እህልን እንሸምት ዘንድ እርሻችንንና ወይናችንን፥ ቤታችንንም አስይዘናል” የሚሉ ነበሩ። 4 ሌሎቹም “ለንጉሡ ግብር እርሻችንንና ወይናችንን አስይዘን ገንዘብ ተበድረናል፤ 5 አሁንም ሥጋችን እንደ ወንድሞቻችን ሥጋ፥ ልጆቻችንም እንደ ልጆቻቸው ናቸው፤ እነሆም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ባሪያዎች ይሆኑ ዘንድ ሰጥተናል፤ ከሴቶችም ልጆቻችን ባሪያዎች ሆነው የሚኖሩ አሉ፤ ታላላቆችም እርሻችንንና ወይናችንን ይዘዋልና ልናድናቸው አንችልም” የሚሉ ነበሩ። 6 እኔም ጩኸታቸውንና ይህን ቃል በሰማሁ ጊዜ እጅግ ዐዘንሁ። 7 በልቤም አሰብሁ፤ ታላላቆቹንና ሹሞቹንም፥ “ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ ወለድ ትወስዳላችሁ” ብዬ ተጣላኋቸው፤ ትልቅም ጉባኤ ሰበሰብሁባቸው። 8 እኔም፥ “ለአሕዛብ የተሸጡትን ወንድሞቻችንን አይሁድን በፈቃዳችን ተቤዠን፤ እናንተስ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁን? እነርሱስ ለእኛ የተሸጡ ይሆናሉን?” አልኋቸው። እነርሱም ዝም አሉ፤ መልስም አላገኙም። 9 ደግሞም አልሁ፥ “የምታደርጉት ነገር መልካም አይደለም፤ ጠላቶቻችን አሕዛብ እንዳይሰድቡን አምላካችንን በመፍራት ትሄዱ ዘንድ አይገባችሁምን? 10 እኔ ደግሞ፥ ወንድሞችም፥ ብላቴኖችም ገንዘብና እህል ለእነርሱ አበድረናል፤ እባካችሁ፥ ይህን ወለድ እንተውላቸው። 11 እርሻቸውን፥ የወይናቸውንና የወይራቸውን ቦታ፥ ቤታቸውንም፥ ከእነርሱም የወሰዳችሁትን ገንዘቡንና እህሉን፥ ወይን ጠጁንና ዘይቱን እባካችሁ ዛሬ መልሱላቸው።” 12 እነርሱም፥ “እንመልስላቸዋለን፤ ከእነርሱም ምንም አንሻም፤ እንደተናገርህ እንዲሁ እናደርጋለን” አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ እንደዚህ ነገር ያደርጉ ዘንድ አማልኋቸው። 13 ደግሞም ልብሴን አራገፍሁና፥ “ይህን ነገር የማያደርገውን ሰው ከቤቱና ከሥራው እንዲሁ እግዚአብሔር ያራግፈው፤ እንዲሁ የተራገፈና ባዶ ይሁን” አልሁ። ጉባኤውም ሁሉ፥ “አሜን” አሉ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፤ ሕዝቡም እንደዚህ ነገር አደረጉ። 14 ንጉሡም በይሁዳ ምድር ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ካዘዘኝ ጊዜ ጀምሮ ከንጉሡ ከአርተሰስታ ከሃያኛው ዓመት እስከ ሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ዐሥራ ሁለት ዓመት ያህል እኔና ወንድሞች ለአለቃ የሚገባውን ቀለብ አልበላንም። 15 ከእኔ አስቀድመው የነበሩት አለቆች ግን በሕዝቡ ላይ አክብደው ነበር፤ ስለ እንጀራውና ስለ ወይኑ አርባ ሰቅል ብር ይወስዱ ነበር፤ ሎሌዎቻቸውም ደግሞ በሕዝቡ ላይ ይሰለጥኑ ነበር። እኔ ግን እግዚአብሔርን ስለ ፈራሁ እንዲህ አላደረግሁም። 16 ደግሞም የቅጥሩን ሥራ ሠራሁ፤ እርሻም አልገዛሁም፤ ብላቴኖችም ሁሉ ወደዚያው ወደ ሥራው ተሰበሰቡ። 17 ደግሞም በዙሪያችን ካሉት አሕዛብ ወደ እኛ ከመጡት ሌላ ከአይሁድና ከሹሞቹ መቶ አምሳ ሰዎች በገበታዬ ነበሩ። 18 ለአንድ ቀን አንድ በሬና ስድስት የሰቡ በጎች፥ አንድ ፍየልም፥ በዐሥር በዐሥር ቀንም ብዙ ልዩ ልዩ ዓይነት ወይን ጠጅ ይዘጋጅልኝ ነበር፤ ነገር ግን አገዛዝ በሕዝቡ ላይ ከብዶ ነበርና ለአለቃ የሚገባውን ቀለብ አልሻም ነበር። 19 አምላኬ ሆይ፥ ለዚህ ሕዝብ ያደረግሁትን ሁሉ ለበጎነት አስብልኝ። |