መዝሙር 28 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከድንኳን በመውጣት ጊዜ የዳዊት መዝሙር። 1 የአማልክት ልጆች ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አምጡ፥ የጊደሮችን ጥጃ ለእግዚአብሔር አምጡ። ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ፥ 2 የስሙን ክብር ለእግዚአብሔር አምጡ፥ በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ። 3 የእግዚአብሔር ቃል በውኆች ላይ ነው። የክብር አምላክ አንጐደጐደ፥ እግዚአብሔር በብዙ ውኆች ላይ ነው። 4 የእግዚአብሔር ቃል በኀይል ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል በታላቅ ክብር ነው። 5 የእግዚአብሔር ቃል ዝግባን ይሰብራል፤ እግዚአብሔር የሊባኖስን ዝግባ ይቀጠቅጣል። 6 እንደ ሊባኖስ ላም ያከሳዋል። ተወዳጅ ግን አንድ ቀንድ እንዳለው ርኤም ልጅ ነው። 7 የእግዚአብሔር ቃል የእሳቱን ነበልባል ይቈርጣል። 8 የእግዚአብሔር ቃል ምድረ በዳውን ያናውጣል፥ እግዚአብሔር የቃዴስን ምድረ በዳ ያናውጣል። 9 የእግዚአብሔር ቃል ዋሊያዎችን ያጠነክራቸዋል፥ ዛፎችንም ይገልጣል፤ ሁሉም በመቅደሱ፦ ምስጋና ይላል። 10 እግዚአብሔር የጥፋት ውኃን ሰብስቦአል፤ እግዚአብሔር ለዘለዓለም ንጉሥ ሆኖ ይቀመጣል። 11 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኀይልን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን በሰላም ይባርካቸዋል። |