ነህምያ 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ እንዳነበበ 1 ሰባተኛውም ወር በደረሰ ጊዜ የእስራኤል ልጆች በከተሞቻቸው ነበሩ። ሕዝቡም ሁሉ በውኃው በር ፊት ወዳለው አደባባይ እንደ አንድ ሰው ሆነው ተሰበሰቡ፤ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ያዘዘውን የሙሴን ሕግ መጽሐፍ ያመጣ ዘንድ ጸሓፊውን ዕዝራን ነገሩት። 2 ካህኑም ዕዝራ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ሕጉን በወንዶችና በሴቶች ጉባኤ፥ አስተውለውም በሚሰሙት ሁሉ ፊት አመጣው። 3 በውኃውም በር ፊት ባለው አደባባይ ላይ ቆሞ፥ በወንዶችና በሴቶች በሚያስተውሉትም ፊት፥ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ቀትር ድረስ አነበበው፤ የሕዝቡም ሁሉ ጆሮ የሕጉን መጽሐፍ ለመስማት ያደምጥ ነበር። 4 ጸሓፊውም ዕዝራ ስለዚህ ነገር በተሠራ በዕንጨት መረባርብ ላይ ቆሞ ነበር፤ በአጠገቡ መቲትያ፥ ሰምያ፥ ሐናንያ፤ ኦርያ፥ ሕልቅያ፥ መዕሢያ በቀኙ በኩል፥ ፈድያ፥ ሚሳኤል፥ ሚልክያ፥ ሐሱም፥ ሐስበዳና፥ ዘካርያስ፥ ሜሱላም በግራው በኩል ቆመው ነበር። 5 ዕዝራም የሕዝቡ ሁሉ የበላይ ነበረና በሕዝቡ ሁሉ ፊት መጽሐፉን ገለጠ፤ በገለጠውም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቆሙ። 6 ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ሕዝቡም ሁሉ እጃቸውን እየዘረጉ፥ “አሜን፥ አሜን” ብለው መለሱ። ራሳቸውንም አዘነበሉ፤ በግንባራቸውም ወደ ምድር ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ። 7 ደግሞ ኢያሱና ባኒ፥ ሰራብያ፥ ያሚን፥ ዓቁብ፥ ሳባታይ፥ ሆዲያ፥ መዕሤያ፥ ቆሊጣ፥ ዓዛርያ፥ ኢዮዛባድ፥ ሐናን፥ ፌልዕያ፥ ሌዋውያኑም ሕጉን ለሕዝቡ ያስተምሩ ነበር፤ ሕዝቡም በየስፍራቸው ቆመው ነበር። 8 የእግዚአብሔርንም ሕግ መጽሐፍ አነበቡ፤ ዕዝራም እግዚአብሔርን ማወቅ ያስተምርና ያስታውቅ ነበር፤ ሕዝቡም የሚነበበውን ያስተውሉ ነበር። 9 ሕቴርሰታ ነህምያም፥ ጸሓፊውም ካህኑ ዕዝራ፥ ሕዝቡንም የሚያስተምሩ ሌዋውያን ሕዝቡን ሁሉ፥ “ዛሬ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ቀን ነው፤ አትዘኑ፤ አታልቅሱም” አሉአቸው፤ ሕዝቡ ሁሉ የሕጉን ቃል በሰሙ ጊዜ ያለቅሱ ነበርና። 10 እርሱም፥ “ሂዱ፤ የሰባውንም ብሉ፤ ጣፋጩንም ጠጡ፤ ለእነዚያም ምንም ለሌላቸው እድል ፈንታቸውን ላኩ፤ ዛሬ ለጌታችን የተቀደሰ ቀን ነው፤ እግዚአብሔርም ኀይላችን ነውና አትዘኑ” አላቸው። 11 ሌዋውያንም “ቀኑ የተቀደሰ ነውና ዝም በሉ፤ አትዘኑም” እያሉ ሕዝቡን ሁሉ ጸጥ ያደርጉ ነበር። 12 ሕዝቡም ሁሉ የተነገራቸውን ቃል አስተውለዋልና ሊበሉና ሊጠጡ፥ እድል ፈንታም ሊልኩ፥ ደስታም ሊያደርጉ ሄዱ። 13 በሁለተኛውም ቀን ከሕዝቡ ሁሉ የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም የሕጉን ቃል ይተረጕምላቸው ዘንድ ወደ ጸሓፊው ወደ ዕዝራ ተሰበሰቡ። 14 በሰባተኛውም ወር ባለው በዓል የእስራኤል ልጆች በዳስ ይቀመጡ ዘንድ በከተሞቻቸውና በኢየሩሳሌምም ይናገሩና ያውጁ ዘንድ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ በሕጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ። 15 ዕዝራም አላቸው፥ “ወደ ተራራ ሂዱ፤ የዘይትና የበረሃ ወይራ፥ የባርሰነትም፥ የዘንባባም፥ የለመለመውንም ዛፍ ቅርንጫፍ አምጡ፤ እንደ ተጻፈውም ዳሶችን ሥሩ።” 16 ሕዝቡም ወጥተው አመጡ፤ እያንዳንዱም በቤቱ ሰገነት ላይ፥ በአደባባዩም ላይ፥ በእግዚአብሔርም ቤት አደባባይ ላይ፥ በውኃውም በር አደባባይና በኤፍሬም በር አደባባይ ላይ ዳስ ሠሩ። 17 ከምርኮም የተመለሱት ማኅበር ሁሉ ዳስ ሠሩ፤ በዳሱም ውስጥ ተቀመጡ። ከነዌም ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ የእስራኤል ልጆች እንዲህ ያለ አላደረጉም ነበር። እጅግም ታላቅ ደስታ ሆነ። 18 ከመጀመሪያውም ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ ዕለት ዕለት የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ ያነብብ ነበር። በዓሉንም ሰባት ቀን ያህል አደረጉ፤ በስምንተኛውም ቀን እንደ ሕጋቸው ወጡ። |