መዝሙር 63 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር። 1 አቤቱ፥ ወደ አንተ የለመንሁትን ጸሎቴን ስማኝ፥ ከጠላትም ጥርጥር ነፍሴን አድናት። 2 ከክፉዎች ሴራ ከብዙዎች ዐመፅ አድራጊዎች ሰውረኝ። 3 እንደ እባብ ምላሳቸውን አሰሉ፤ መራራ ነገርን ለማድረግ፥ 4 ንጹሕንም በስውር ለመግደል ቀስትን ገተሩ፤ በድንገት ይነድፏቸዋል አይፈሩምም። 5 ለእነርሱ ለራሳቸው ክፉ ነገርን አጸኑ፤ ወጥመድን ይሰውሩ ዘንድ ተማከሩ፤ የሚያምንም የለም ይላሉ። 6 ዐመፃን ፈለጓት፥ ሲፈትኑም ሲጀምሩም አለቁ፤ ሰው በጥልቅ ልብ ውስጥ ይገባል፥ 7 እግዚአብሔርም ከፍ ከፍ ይላል። መቅሠፍታቸው እንደ ልጆች ሕንፃ ሆነ፤ 8 አንደበታቸው በላያቸው ደከመ፥ የሚያዩአቸውም ሁሉ ደነገጡ። 9 ሰው ሁሉ ፈራ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ ተናገሩ፥ ሥራውንም ዐወቁ። 10 ጻድቅ በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፥ በእርሱም ይታመናል፤ ልባቸውም የቀና ሁሉ ይከብራሉ። |