Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ነህምያ 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ ለሕዝቡ እንዳነበበ

1 የእስራኤል ሕዝብ በሰባተኛው ወር በየከተሞቻቸው መስፈራቸውን አበቁ፤ በዚያም ወር በመጀመሪያው ቀን በኢየሩሳሌም የውሃ በር ተብሎ በሚጠራው አደባባይ በውስጥ በኩል ሕዝቡ ሁሉ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ እነርሱም የሕግ ምሁሩን ዕዝራን እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ለእስራኤል ሕዝብ የሰጠውን የኦሪትን ሕግ መጽሐፍ ያመጣላቸው ዘንድ ለመኑት።

2 ስለዚህም ካህኑ ዕዝራ ሰባተኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን፥ ማስተዋል የሚችል ሕዝብ ሁሉ ሴት፥ ወንድ፥ ልጅ ዐዋቂው በሙሉ ወደተሰበሰቡበት ስፍራ፥ የሕጉን መጽሐፍ አመጣ፤

3 በዚያም አደባባይ ዕዝራ በቅጽሩ በር አጠገብ ቆሞ ከንጋት እስከ ቀትር የሕጉን መጽሐፍ ከፍ ባለ ድምፅ አነበበላቸው፤ ወንዶችም ሴቶችም ሁሉ በከፍተኛ ስሜት አዳመጡት።

4 የሕግ ምሁሩ ዕዝራ ለዚሁ ተግባር አመች ይሆን ዘንድ ከዕንጨት በተሠራ መድረክ ላይ ቆሞ ነበር፤ ከእርሱም ጋር በስተቀኙ በኩል የቆሙት ሰዎች ማቲትያ፥ ሼማዕ፥ ዓናያ፥ ኡሪያ፥ ሒልቂያና መዕሤያ ሲሆኑ፥ በስተ ግራው በኩል ደግሞ ፐዳያ፥ ሚሻኤል፥ ማልኪያ፥ ሐሹም፥ ሐሽባዳናህ፥ ዘካርያስና መሹላም ቆመው ነበር።

5 ዕዝራ ከሕዝቡ ከፍ ብሎ በተሠራው መድረክ ላይ በቆመ ጊዜ፥ ሁሉም ትኲር ብለው ይመለከቱት ነበር፤ እርሱም የሕጉን መጽሐፍ በከፈተ ጊዜ፥ ሁሉም ከተቀመጡበት ተነሡ፤

6 ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገነ። ሁሉም እጆቻቸውን ወደ ላይ በማንሣት “አሜን! አሜን!” ሲሉ መለሱ፤ ወደ ምድርም ለጥ ብለው ለእግዚአብሔር ሰገዱ።

7 ከዚህ በኋላ ተነሥተው ባሉበት ስፍራ ቆሙ፤ ከዚህ ቀጥሎ ስማቸው የተዘረዘረ ሌዋውያንም የሕጉን መጽሐፍ ትርጒም ለሕዝቡ አብራሩላቸው፤ እነርሱም ኢያሱ፥ ባኒ፥ ሼሬብያ፥ ያሚን፥ ዓቁብ፥ ሻበታይ፥ ሆዲያ፥ መዕሤያ፥ ቀሊጣ፥ ዐዛርያስ፥ ዮዛባድ፥ ሐናንና ፐላያ ነበሩ።

8 እነርሱም ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አነበቡለት፤ ሕዝቡም የሚነበበው ይገባው ዘንድ ያብራሩለት ነበር።

9 የሕጉን ቃል በሰሙ ጊዜ ሰዎቹ ስላለቀሱ፥ አገረ ገዢው ነህምያ፥ ካህኑና የሕግ ምሁሩ ዕዝራ፥ ሕዝቡን ያስተምሩ የነበሩት ሌዋውያን “ይህ ቀን ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ቀን ስለ ሆነ፥ አትዘኑ፤ አታልቅሱም” አሉአቸው።

10 ነህምያ፦ “ሂዱና ምርጡን ምግብ ብሉ፤ ጣፋጩን መጠጥ ጠጡ፤ ምንም ለሌላቸውም ላኩ፤ ይህ ቀን ለአምላካችን የተቀደሰ ቀን ነው፤ የእግዚአብሔር ደስታ ኀይላችሁ ስለ ሆነ አትዘኑ” አላቸው።

11 ሌዋውያኑም በዚህ በተቀደሰ ዕለት ማዘን እንደማይገባቸው በማስረዳት የሕዝቡን ጩኸት ጸጥ አደረጉ፤

12 የተነበበላቸውን ቃል ትርጒም በሚገባ ተረድተው ስለ ነበር ሕዝቡ ሁሉ ወደየቤታቸው ሄደው በመብላትና በመጠጣት እጅግ ተደሰቱ፤ ያላቸውንም ምግብ ከሌሎቹ ጋር አብረው ተካፈሉ፤


የዳስ በዓል መከበር

13 በማግስቱ የጐሣ አለቆች ከካህናቱና ከሌዋውያኑ ጋር በአንድነት ሆነው የሕጉን ቃላት ትምህርት ለማጥናት ወደ ዕዝራ ዘንድ ሄዱ።

14 እስራኤላውያን ሕጉን በሚያነቡበት ጊዜ የሰባተኛውን ወር በዓል በዳስ ውስጥ ሆነው እንዲያከብሩ መታዘዙን እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ባዘዘው ሕግ ውስጥ ተጽፎ አገኙ።

15 የዳስን በዓል በተመለከተ ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት ወደ ተራራማው አገር ሄደው የወይራ ዘይት ዛፍና የዱር ወይራ ቅርንጫፎችን የባርሰነትና የዘንባባ ቅርንጫፎችን ለማምጣት በየከተማውና በኢየሩሳሌም አካባቢ እንዲሄዱ አዘዙአቸው።

16 ስለዚህም ሕዝቡ የዛፍ ቅጠል እየቈረጡ አምጥተው በሚኖሩበት ግቢ፥ በየቤታቸው ጣራ ድምድማት ላይ፥ በቤተ መቅደሱ አደባባይና የውሃ በር ተብሎ በሚጠራው አደባባይ፥ እንዲሁም በኤፍሬም አደባባይ ዳስ ጣሉ፤

17 ከምርኮ ተመልሰው የመጡት ሰዎች ሁሉ ዳሶችን ሠርተው በዳሱ ውስጥ ተቀመጡ፤ ይህም ከነዌ ልጅ ኢያሱ ዘመን ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ነበር፤ እያንዳንዳቸውም ወሰን የሌለው ደስታ ተሰምቶአቸው ነበር።

18 በዓሉ ከተጀመረበት ዕለት አንሥቶ እስከ መጨረሻይቱ ቀን ድረስ ዕዝራ በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ አንዳንድ ክፍል ያነብላቸው ነበር፤ በዓሉንም እስከ ሰባት ቀን አከበሩ፤ በስምንተኛውም ቀን ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት የበዓሉ መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ተደረገ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos