ኤርምያስ 28 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ነቢዩ ኤርምያስና ሐሰተኛው ነቢይ ሐናንያ 1 ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ በዚያ ዓመት፥ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ መንግሥት መጀመሪያ፥ በአራተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ሐሰተኛው ነቢይ የገባዖን ሰው የዓዙር ልጅ ሐናንያ በእግዚአብሔር ቤት በካህናትና በሕዝብ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦ 2 “የሠራዊት ጌታ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር ሰብሬአለሁ። 3 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከዚች ስፍራ ወደ ባቢሎን የወሰዳቸውን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች ሁሉ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደዚህች ስፍራ እመልሳለሁ፤ 4 ወደ ባቢሎንም የሄዱትን የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳን ምርኮ ሁሉ ወደዚች ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር እሰብራለሁና።” 5 ነቢዩ ኤርምያስም በካህናቱና በእግዚአብሔር ቤት በቆሙት ሕዝብ ሁሉ ፊት ለሐሰተኛው ነቢይ ለሐናንያ ተናገረ። 6 ነቢዩም ኤርምያስ እንዲህ አለ፥ “አሜን፥ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግ፤ የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ፥ ምርኮውንም ሁሉ ከባቢሎን ወደዚህ ስፍራ በመመለስ እግዚአብሔር የተናገርኸውን ትንቢት ይፈጽም። 7 ነገር ግን በጆሮህና በሕዝቡ ሁሉ ጆሮ የምናገረውን የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ 8 ከጥንት ከእኔና ከአንተ በፊት የነበሩ ነቢያት በብዙ ሀገርና በታላላቅ መንግሥታት ላይ ስለ ሰልፍና ስለ ክፉ ነገር ስለ ቸነፈርም ትንቢት ተናገሩ። 9 ስለ ሰላም ትንቢት የተናገረ ነቢይ ትንቢቱ በደረሰ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በእውነት የላከው ነቢይ እንደ ሆነ ይታወቃል።” 10 ሐሰተኛው ነቢይ ሐናንያም በሕዝቡ ሁሉ ፊት ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ወስዶ ሰበረው። 11 ሐናንያም በሕዝቡ ሁሉ ፊት፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንግዲህ በሁለት ዓመት ውስጥ የባቢሎንን ንጉሥ የናቡከደነፆርን ቀንበር ከአሕዛብ ሁሉ አንገት እሰብራለሁ” አለ። ነቢዩ ኤርምያስም መንገዱን ሄደ። 12 ሐናንያም ቀንበሩን ከነቢዩ ኤርምያስ አንገት ከሰበረ በኋላ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 13 “ሂድ፥ ለሐናንያ እንዲህ ብለህ ንገረው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ የእንጨትን ቀንበር ሰብረሃል፤ እኔ ግን በእርሱ ፋንታ የብረትን ቀንበር እሠራለሁ። 14 የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ይገዙለት ዘንድ የብረትን ቀንበር በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ አንገት ላይ አድርጌአለሁ፤ እነርሱም ይገዙለታል፤ የምድረ በዳ አራዊትን ደግሞ ሰጥቼዋለሁ።” 15 ነቢዩም ኤርምያስ ሐሰተኛውን ሐናንያን፥ “ሐናንያ ሆይ ስማ፤ እግዚአብሔር አልላከህም፤ ነገር ግን ይህ ሕዝብ በሐሰት እንዲታመን አድርገሃል። 16 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ከገጸ ምድር አስወግድሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ዐመፅን ተናግረሃልና በዚህ ዓመት ትሞታለህ” አለው። 17 ሐሰተኛው ነቢይ ሐናንያም በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ሞተ። |