ነህምያ 8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ለሕጉ እንዲገዙ ዕዝራ ሕዝቡን መሰብሰቡ 1 ሕዝቡም ሁሉ በውኃው በር ፊት ወዳለው አደባባይ እንደ አንድ ሰው ሆነው ተሰበሰቡ፤ ጌታ ለእስራኤል ያዘዘውን የሙሴን ሕግ መጽሐፍ እንዲያመጣ ለጸሐፊው ለዕዝራ ነገሩት። 2 ካህኑ ዕዝራ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ሕጉን ወንዶች፥ ሴቶችና አስተውለው መስማት የሚችሉ ባሉበት በጉባኤው ሁሉ ፊት አመጣው። 3 በውኃው በር ፊት ባለው አደባባይ ላይ ቆሞ፥ ወንዶች፥ ሴቶች፥ የሚያስተውሉም ባሉበት፥ ከማለዳ ጀመሮ እስከ ቀትር ድረስ አነበበው፤ የሕዝቡም ሁሉ ጆሮ የሕጉን መጽሐፍ በጽሞና ያደምጥ ነበር። 4 ጸሐፊውም ዕዝራ ለዚህ ተብሎ በተሠራ የእንጨት መድረክ ላይ ቆሞ ነበር፤ በአጠገቡ ማቲትያ፥ ሼማዕ፥ ዓናያ፥ ኡሪያ፥ ሒልቅያና ማዓሴያ በቀኙ በኩል፤ ፐዳያ፥ ሚሻኤል፥ ማልኪያ፥ ሐሹም፥ ሐሽባዳና፥ ዘካርያስ፥ ሜሹላም በግራው በኩል ቆመው ነበር። 5 ዕዝራም ከሕዝቡ ሁሉ በላይ ከፍ ብሎ ነበርና በሕዝቡ ሁሉ ዐይን ፊት መጽሐፉን ከፈተ፤ በከፈተውም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቆሙ። 6 ዕዝራም ታላቁን አምላክ ጌታን ባረከ፤ ሕዝቡም ሁሉ እጆቻቸውን በመዘርጋት፦ አሜን፥ አሜን ብለው መለሱ። ራሳቸውን አዘነበሉ፥ በግምባራቸውም ተደፍተው ለጌታ ሰገዱ። 7 ደግሞ ኢያሱ፥ ባኒ፥ ሼሬብያ፥ ያሚን፥ ዓቁብ፥ ሻብታይ፥ ሆዲያ፥ ማዓሤያ፥ ቅሊጣ፥ አዛርያ፥ ዮዛባድ፥ ሐናን፥ ፐላያና ሌዋውያኑ ሕጉን ለሕዝቡ ያስረዱ ነበር፤ ሕዝቡም በቆሙበት ነበሩ። 8 በመጽሐፉ ያለውን የእግዚአብሔርን ሕግ በግልጽ አነበቡ፥ የተነበበው እንዲገባቸውም ያስረዷቸው ነበር። 9 ገዢው ነህምያ፥ ጸሐፊው ካህኑ ዕዝራ፥ ሕዝቡን የሚያስተምሩ ሌዋውያን ሕዝቡን ሁሉ፦ “ይህ ቀን ለጌታ አምላካችሁ ቅዱስ ነው፤ አታልቅሱ እንባም አታፍስሱ” አሉአቸው፤ ሕዝቡ ሁሉ የሕጉን ቃል በሰሙ ጊዜ ያለቅሱ ነበርና። 10 እርሱም፦ “ሂዱ፥ የሰባውን ብሉ፥ ጣፋጩንም ጠጡ፥ ለእነዚያ ምንም ላልተዘጋጀላቸው ድርሻቸውን ላኩ፤ ይህ ቀን ለጌታችን ቅዱስ ነውና፤ አትዘኑ የጌታ ደስታ ኃይላችሁ ነውና” አላቸው። 11 ሌዋውያንም፦ “ቀኑ ቅዱስ ነውና ዝም በሉ፥ አትዘኑም” እያሉ ሕዝቡን ሁሉ ዝም አሰኙት። 12 ሕዝቡም ሁሉ ሊበሉ፥ ሊጠጡ፥ ለሌላቸው ድርሻቸውን ሊልኩና ታላቅ ደስታ ሊያደርጉ ሄዱ፤ የተነገራቸውን ቃል ማስተዋል ችለው ነበርና። የዳስ በዓል መከበር 13 በሁለተኛው ቀን ከሕዝቡ ሁሉ አለቆች የሆኑ አባቶች፥ ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም የሕጉን ቃል እንዲተረጉምላቸው ወደ ጸሐፊው ወደ ዕዝራ ተሰበሰቡ። 14 በሰባተኛው ወር ባለው በዓል የእስራኤል ልጆች በዳስ እንዲቀመጡ ጌታ በሙሴ በኩል ያዘዘውን በሕጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ፤ 15 በከተሞቻቸው ሁሉና በኢየሩሳሌምም፦ “እንደተጻፈው ዳሶችን ለመስራት ወደ ተራራ ውጡ፥ የዘይትና የበረሀ ወይራ፥ የባርሰነት፥ የዘንባባና የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ አምጡ” ብለው ይናገሩና ያውጁ። 16 ሕዝቡም ወጥተው አመጡ፥ እያንዳንዱ በቤቱ ሰገነት ላይ፥ በየግቢያቸው፥ በእግዚአብሔር ቤት ግቢ፥ በ “ውኃ በር” አደባባይና በኤፍሬም በር አደባባይ ላይ ዳሶችን ሠሩ። 17 ከምርኮ የተመለሱት ማኅበር ሁሉ ዳሶችን ሠሩ፥ በዳሶቹም ውስጥ ተቀመጡ። ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ የእስራኤል ልጆች እንዲህ ያለ ነገር አድርገው አያውቁም ነበርና። እጅግ ታላቅ ደስታም ሆነ። 18 ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ ዕዝራ ዕለት ዕለት የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ ያነብብ ነበር። በዓሉን ሰባት ቀን አከበሩ፤ በስምንተኛው ቀን በሕጉ መሠረት የተቀደሰ ጉባኤ ነበረ። |