ኤርምያስ 2:2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “ሂድ፤ እንዲህ ብለህ በኢየሩሳሌም ጆሮ ተናገር፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የብላቴንነትሽን ምሕረት፥ የታጨሽበትንም ፍቅር፥ በምድረ በዳ ዘር ባልተዘራበት ምድር እንደ ተከተልሽኝ አስቤአለሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም “ሂድና ጮኸህ ይህን ለኢየሩሳሌም ጆሮ አሰማ፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘በወጣትነትሽ ጊዜ የነበረሽን ታማኝነት፣ በሙሽርነትሽም ወራት እንዴት እንደ ወደድሽኝ፣ በምድረ በዳ ዘር በማይዘራበት ምድር፣ እንዴት እንደ ተከተልሽኝ አስታውሳለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) “ሂድ፥ በኢየሩሳሌም ጆሮዎች ላይ አውጅ፥ እንዲህም በል፦ ጌታ እንዲህ ይላል፦ የብላቴንነትሽን ጽኑ ፍቅር የታጨሽበትንም ፍቅር፥ በምድረ በዳ ዘር ባልተዘራበት ምድር እንደ ተከተልሽኝ አስታውሼዋለሁ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ሂድና ለኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘በመጀመሪያ በምድረ በዳ ምንም በማያበቅልበት ትከተሉኝ ነበር፤ በዚያን ጊዜ ሙሽራይቱ ለሙሽራው የምታሳየውን ፍቅርና ታማኝነት ለኔም ታሳይ እንደ ነበረ አስታውሳለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ሂድ፥ በኢየሩሳሌም ጆሮ ጩኽ፥ እንዲህም በል፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የብላቴንነትሽን ምሕረት የታጨሽበትንም ፍቅር፥ በምድረ በዳ ዘር ባልተዘራበት ምድር እንደ ተከተልሽኝ አስቤአለሁ። |
እስራኤልም እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ያደረጋትን ታላቂቱን እጅ አዩ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርም አመኑ፤ ባሪያውንም ሙሴን አከበሩ።
ሙሴም፥ “እግዚአብሔር ያንጐራጐራችሁበትን ማንጐራጐራችሁን ሰምቶአልና በመሸ ጊዜ ትበሉ ዘንድ ሥጋን፥ በማለዳም ትጠግቡ ዘንድ እንጀራን እግዚአብሔር ይሰጣችኋል፤ እኛም ምንድን ነን? ማንጐራጐራችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ በእኛ ላይ አይደለም” አለ።
እናንት የጽዮን ቈነጃጅት፥ እናቱ በሠርጉ ቀን በልቡ ደስታ ቀን ያቀዳጀችውን አክሊል ደፍቶ ንጉሥ ሰሎሞንን ታዩ ዘንድ ውጡ።
መዓዛዋ እንደ ከርቤና እንደ ዕጣን የሆነው፥ ከልዩ የሽቱ ቅመም ሁሉ የሆነው፥ ይህች ከምድረ በዳ እንደ ጢስ ዐምድ የወጣችው ማን ናት?
በኀይልህ ጩኽ፤ አትቈጥብ፤ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፤ ለሕዝቤ ኀጢአታቸውን፥ ለያዕቆብ ቤትም በደላቸውን ንገር።
እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ይህችን ቃል ሁሉ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ተናገር፤ እንዲህም በል፦ የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ስሙ፤ አድርጉትም።
እነርሱም፥ “ከግብፅ ምድር ያወጣን፥ በምድረ በዳና በባድማ፥ ዕንጨትና ውኃ፥ የእንጨት ፍሬም በሌለበት ምድር፥ ሰው በማያልፍበትና የሰው ልጅም በማይቀመጥበት ምድር የመራን እግዚአብሔር ወዴት አለ? አላሉም።
“በእግዚአብሔር ቤት በር ቁም፤ ይህንም ቃል እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ለእግዚአብሔር ትሰግዱ ዘንድ በእነዚህ በሮች የምትገቡ ከይሁዳ ያላችሁ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
ከኀጢአትሽና ከዝሙትሽ ሁሉ ይህ ይከፋል፤ አንቺ ዕራቁትሽን ሳለሽ፥ ኀፍረትም ሞልቶብሽ ሳለሽ፥ በደምሽም ተለውሰሽ ሳለሽ፥ የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽም።
ነገር ግን በሕፃንነትሽ ወራት ከአንቺ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳኔን ዐስባለሁ፤ የዘለዓለምንም ቃል ኪዳን አጸናልሻለሁ።
በአንቺ ዘንድ በአለፍሁና በአየሁሽ ጊዜ፥ እነሆ ጊዜሽ እንደ ደረሰ፥ በአንቺም የሚያድሩ ሰዎች ጊዜ እንደ ደረሰ አየሁ። እጆችን በላይሽ ዘረጋሁ፤ ኀፍረተ ሥጋሽንም ከደንሁ፤ ማልሁልሽም፤ ከአንቺም ጋራ ቃል ኪዳን ገባሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺም ለእኔ ሆንሽ።
በግብፅ ሀገር አመነዘሩ፤ በኮረዳነታቸው ሳሉ አመነዘሩ፤ በዚያም ጡቶቻቸው ወደቁ፤ በዚያም ድንግልናቸውን አጡ።
በግብፅም የነበረውን ዝሙቷን አልተወችም፤ በዚያም በኮረዳነቷ ጊዜ ከእርስዋ ጋር ተኝተው ነበር፤ የድንግልናዋንም ጡቶች ዳብሰው ነበር፤ ዝንየታቸውንም አፍስሰውባት ነበር።
ከዚያም የተገኘውን ገንዘብዋን እሰጣታለሁ፤ ምክርዋንም በአኮር ሸለቆ እገልጣለሁ፤ እንደ ሕፃንነትዋ ወራት፥ ከግብፅም እንደ ወጣችበት ቀን ትዘምራለች።
ወዳጆችዋንም ትከተላለች፤ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ ትፈልጋቸውማለች፤ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ እርስዋም፥ “ከዛሬ ይልቅ የዚያን ጊዜ ይሻለኝ ነበርና ተመልሼ ወደ ቀደመው ባሌ እሄዳለሁ” ትላለች።
በብብታቸው እንደ መሬት፤ በእግዚአብሔርም ቤት እንደ ንስር ይመጣል። ቃል ኪዳኔን ተላልፈዋልና፥ በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና።
እስራኤልን በምድረ በዳ እንደ አለ ወይን ሆኖ አገኘሁት፤ አባቶቻችሁንም በመጀመሪያዋ ዓመት እንደ በለስ በኵራት ሆነው አየኋቸው፤ እነርሱ ግን ወደ ብዔልፌጎር መጡ፤ ለነውርም ተለዩ፤ እንደ ወደዱትም ርኩስ ሆኑ።
አምላክህ እግዚአብሔር የእጅህን ሥራ ሁሉ ባርኮልሃልና፤ ይህን ታላቅና የሚያስፈራ ምድረ በዳ እንዴት እንደ ዞርኸው ዕወቅ፤ በዚህ አርባ ዓመት ውስጥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነበረ፤ ከተናገርኸው ሁሉ አንዳችም አላሳጣህም።
አምላክህ እግዚአብሔር ይፈትንህ ዘንድ፥ በልብህም ያለውን ትእዛዙን ትጠብቅ ወይም አትጠብቅ እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ፥ ሊያስጨንቅህ በምድረ በዳ የመራህን መንገድ ሁሉ አስብ።
አመንዝሮች ሆይ! ዓለምን መውደድ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።