መዝሙር 129 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የመዓርግ መዝሙር። 1 አቤቱ፥ አንተን ከጥልቅ ጠራሁህ። 2 አቤቱ፥ ቃሌን ስማኝ፤ ጆሮህም የልመናዬን ቃል የሚያደምጥ ይሁን። 3 አቤቱ፥ ኀጢአትንስ ብትጠባበቅ፥ አቤቱ፥ ማን ይቆማል? 4 ይቅርታ ከአንተ ዘንድ ነውና። 5 አቤቱ፥ ስለ ስምህ ተስፋ አደረግሁህ፤ ነፍሴ በሕግህ ታገሠች። 6 ከማለዳው ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊት ነፍሴ በእግዚአብሔር ታመነች። ከማለዳ ጀምሮ እስራኤል በእግዚአብሔር ታመነ። 7 ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታ፥ በእርሱም ዘንድ ብዙ ማዳን አለና፥ 8 እርሱም እስራኤልን ከኀጢአቱ ሁሉ ያድነዋል። |