ኢሳይያስ 43:3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኀኒትህ ነኝ፤ ግብፅንና ኢትዮጵያን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ሴዎንንም ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የእስራኤልም ቅዱስ መድኀኒትህ ነኝና፤ ግብጽን ለአንተ ቤዛ እንድትሆን፣ ኢትዮጵያንና ሳባን በአንተ ፈንታ እሰጣለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ ጌታ መድኃኒትህ ነኝ፤ ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ እሰጣለሁ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እኔ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር አምላካችሁና አዳኛችሁ ነኝ፤ እናንተን ለመታደግ ግብጽን፥ ኢትዮጵያውያንንና ሳባን እሰጣለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኃኒትህ ነኝ፥ ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ። |
የፈርዖንም ሹሞች፥ “ይህ ሰው እስከ መቼ እንቅፋት ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን ያመልኩት ዘንድ ሰዎችን ልቀቅ፤ ግብፅስ እንደ ጠፋች ገና አታውቅምን?” አሉት።
ይህም ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በግብፅ ምድር ለዘለዓለም ምልክት ይሆናል፤ ከሚያስጨንቋቸው የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉና፥ እርሱም የሚያድናቸውን ሰው ይልክላቸዋል፤ ይፈርዳል፤ ያድናቸዋልም።
እግዚአብሔርም አለ፥ “ባሪያዬ ኢሳይያስ ሦስት ዓመት ራቁቱን በባዶ እግሩ እንደ ሄደ፥ እንዲሁ በግብፅና በኢትዮጵያ ላይ ሦስት ዓመት ምልክትና ተአምራት ይደረጋል።
“ከዚህ መንገድ መልሱን፤ ከዚህም ፈቀቅ አድርጉን በሉ፤ የእስራኤልንም ቅዱስ ትምህርት ከእኛ ዘንድ አስወግዱ” ይሏቸዋል።
ያዕቆብ ሆይ፥ አትፍራ፤ በቍጥር ጥቂት የነበርህ እስራኤል ሆይ፥ እኔ እረዳሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ የሚቤዥህም የእስራኤል ቅዱስ ነው።
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ግብፅና የኢትዮጵያ ንግዶች ደከሙ፤ ቁመተ ረዥሞች የሳባ ሰዎች ወደ አንተ ያልፋሉ፤ ለአንተም ይገዙልሃል፤ እጆቻቸውን ታስረው በኋላህ ይከተሉሃል፤ በፊትህም ያልፋሉ፤ ለአንተም እየሰገዱ፦ በእውነት እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም ብለው ይለምኑሃል።
የሚናገሩ ከሆነ ከጥንት ጀምሮ ይህን ምስክርነት ያደረገ ማን እንደ ሆነ በአንድነት ያውቁ ዘንድ ይቅረቡ። ያሳየሁም የተናገርሁም እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኀኒት ነኝ፥ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም።
የአስጨናቂዎችሽንም ሥጋቸውን ይበላሉ፤ እንደ ጣፋጭ ወይን ጠጅም ደማቸውን ጠጥተው ይሰክራሉ፤ ሥጋ ለባሹም ሁሉ እኔ እግዚአብሔር መድኀኒትሽና ታዳጊሽ፥ የያዕቆብን ኀይል የምደግፍ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
የአሕዛብንም ወተት ትጠጫለሽ፤ የነገሥታትንም ብልጽግና ትበያለሽ፤ እኔም እግዚአብሔር የእስራኤል ቅዱስ፥ መድኀኒትሽና ታዳጊሽ እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ።
ጌታ ሆይ! አንተ የእስራኤል ተስፋ ነህ፤ በመከራም ጊዜ ታድነዋለህ፤ በምድር እንደ እንግዳ፥ ወደ ማደሪያም ዘወር እንደሚል መንገደኛ ስለ ምን ትሆናለህ?
“ስለዚህ እነሆ በዚህ ወራት አስታውቃቸዋለሁ፤ እጄንና ኀይሌንም አሳያቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ያውቃሉ።”
ቅዱሱም ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ይታወቃል፤ ቅዱሱንም ስሜን ከእንግዲህ ወዲህ አላረክስም፤ አሕዛብም የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር፥ እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
ሰማይን ያጸናሁ፥ ምድርንም የፈጠርሁ፥ እጆችም የሰማይ ሠራዊትን ያቆሙ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። እንዳትከተላቸውም እነርሱን አላሳየሁህም። ከግብፅ ምድርም ያወጣሁህ እኔ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አትወቅ፤ ከእኔ በቀር የሚያድንህ የለምና።
እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና፤ ሰውነታችሁን ቀድሱ፤ ቅዱሳንም ሁኑ፤ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፤
“የእስራኤል ልጆች ሆይ! እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር። እስራኤልን ከግብፅ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከቀጰዶቅያ፥ ሶርያውያንንም ከጕድጓድ ያወጣሁ አይደለምን?
አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፣ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፣ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፣ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫንይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።
ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኀይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።