ዘሌዋውያን 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለሚበሉና ስለማይበሉ እንስሳት ( ዘዳ. 14፥3-21 ) 1 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 2 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብላችሁ ንገሩአቸው፦ በምድር ካሉት እንስሳት ሁሉ የምትበሉአቸው እንስሳት እነዚህ ናቸው። 3 የተሰነጠቀ ሰኰና ያለውንና የሚያመሰኳውን እንስሳ ሁሉ ብሉ። 4 ነገር ግን ከሚያመሰኩት ፥ ሰኰናቸውም ስንጥቅ ከሆነው ከእነዚህ አትበሉም፤ ግመል ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ለእናንተ ርኩስ ነው። 5 ጥንቸል ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ይህ ለእናንተ ርኩስ ነው። 6 ሽኮኮ ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ለእናንተ ርኩስ ነው። 7 እርያም ሰኰናው ተሰንጥቆአል፤ ነገር ግን ስለማያመሰኳ ለእናንተ ርኩስ ነው። 8 የእነዚህን ሥጋ አትበሉም፤ በድናቸውንም አትነኩም፤ ለእናንተ ርኩሳን ናቸው። 9 “በውኃ ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ እነዚህን ትበላላችሁ፤ በውኆች፥ በባሕሮችም፥ በወንዞችም ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ትበላላችሁ። 10 በውኆች ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ፥ በውኆች ውስጥ የሕይወት ነፍስ ከአላቸው ሁሉ፥ በባሕሮችና በወንዞች ውስጥ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፉ ናቸው። 11 በእናንተም ዘንድ የተጸየፉ ይሆናሉ። ሥጋቸውንም አትበሉም፤ በድናቸውንም ትጸየፋላችሁ። 12 ክንፍና ቅርፊትም የሌላቸው በውኃ ውስጥ የሚኖሩት ሁሉ ለእናንተ ርኩሳን ናቸው። 13 “ከወፎችም ወገን የምትጸየፉአቸው እነዚህ ናቸው፤ አይበሉም፤ የተጸየፉ ናቸው፤ ንስር፥ ገዴ አሞራ፥ ዓሣ አውጭ፥ 14 ጭላት፥ ጭልፊት፥ አንጭ አሞራ በየወገኑ፤ 15 ቁራ ሁሉ በየወገኑ፤ 16 ሰጎን በየወገኑ፤ ጠለቋ፥ ዝዪ፥ በቋል በየወገኑ፤ 17 ጉጉት፥ እርኩም፥ ጋጋኖ፥ 18 የውኃ ዶሮ፥ ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራ፥ 19 ሸመላ፥ ሳቢሳ በየወገኑ፤ ጅንጅላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ። 20 “የሚበርርም፥ በአራት እግሮችም የሚሄድ ተንቀሳቃሽ ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ነው። 21 ነገር ግን ከሚበርሩት፥ አራትም እግሮች ካሉአቸው፥ ከእግሮቻቸውም በላይ በምድር ላይ የሚዘልሉባቸው ጭኖች ካሉአቸው ተንቀሳቃሾች እነዚህን ትበላላችሁ፤ 22 ከእነርሱም እነዚህን አትበሉም፤ ኩብኩባ የሚመስለውም፥ ፌንጣ የሚመስለውም፥ አሸን የሚመስለውም፥ አንበጣ የሚመስለውም። 23 የሚበርር፥ አራትም እግሮች ያሉት ተንቀሳቃሽ ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ነው። 24 “በእነዚህም ርኩስ ትሆናላችሁ፤ የእነርሱንም በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 25 ከእነርሱም በድን የሚያነሣ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 26 ሰኰናም ያለው፥ ነገር ግን ሰኰናው ያልተሰነጠቀ፥ የማያመሰኳም እንስሳ ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ነው፤ እርሱን የሚነካ ሁሉ ርኩስ ነው። 27 በአራት እግሮቹ ከሚሄድ እንስሳ ሁሉ በመዳፎቹ ላይ የሚሄድ ለእናንተ ርኩስ ነው፤ የእርሱን በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 28 በድናቸውንም የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው። እነርሱም በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው። 29 “በምድር ላይም ከሚንቀሳቀስ ተንቀሳቃሽ እነዚህ ለእናንተ ርኩሳን ናቸው፤ ሙጭልጭላ፥ አይጥ፥ እንሽላሊት በየወገኑ፥ 30 ኤሊ፥ አዞ፥ ገበሎ፥ አርጃኖ፥ እስስት። 31 ከሚንቀሳቀሱት ሁሉ በእናንተ ዘንድ ርኩሳን የሚሆኑ እነዚህ ናቸው። ከእነርሱም በድናቸውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 32 ከእነርሱም በድናቸው በምንም ላይ ቢወድቅ እርሱ ርኩስ ነው፤ የዕንጨት ዕቃ ወይም ልብስ ወይም ቍርበት ወይም ከረጢት ቢሆን የሚሠራበት ዕቃ ሁሉ እርሱን በውኃ ውስጥ ይንከሩት፤ እስከ ማታም ርኩስ ነው፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። 33 ከእነርሱም አንዳች በውስጡ የወደቀበትን የሸክላውን ዕቃ ሁሉ ስበሩት፤ በውስጡም ያለው ሁሉ ርኩስ ነው። 34 በእርሱ ውስጥ ያለው፤ ውኃም የሚፈስስበት፥ የሚበላ መብል ሁሉ ርኩስ ነው፤ በዚህም ዕቃ ሁሉ ያለው የሚጠጣ መጠጥ ሁሉ ርኩስ ነው። 35 ከእነዚህም በድን የሚወድቅበት ሁሉ ርኩስ ነው፤ እቶን ወይም ምድጃ ቢሆን ይሰባበራል፤ ርኩሳን ናቸውና፤ ለእናንተ ርኩሳን ይሆናሉ። 36 ነገር ግን ምንጩ፥ ጉድጓዱም፥ የውኃውም ኵሬ ንጹሓን ናቸው፤ በድናቸውን ግን የሚነካ ርኩስ ነው። 37 ከበድናቸውም በሚዘራ ዘር ላይ አንዳች ቢውድቅ እርሱ ንጹሕ ነው። 38 ነገር ግን በዘሩ ላይ ውኃ ቢፈስስበት፥ ከዚህ በኋላ ከበድናቸው አንዳች ቢወድቅበት፥ ለእናንተ ርኩስ ነው። 39 “ለመብል ከሚሆኑላችሁ እንስሳት የሞተ ቢኖር፥ በድኑን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 40 ከበድኑም የሚበላ ልብሱን ያጥባል፤ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ በድኑንም የሚያነሣ፤ ልብሱን ይጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 41 “በምድርም ላይ የሚንቀሳቀስ ተንቀሳቃሽ አውሬ ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ነው፤ አትብሉትም። 42 በሆዱ የሚሳብ፥ በአራትም እግሮች የሚሳብ፥ ብዙ እግሮችም ያሉት፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ ርኩሳን ናቸውና አትብሉአቸው። 43 በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ ሰውነታችሁን አታርክሱ፤ በእነርሱም እንዳትረክሱ ሰውነታችሁን አታርክሱባቸው። 44 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና፤ ሰውነታችሁን ቀድሱ፤ ቅዱሳንም ሁኑ፤ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፤ 45 በምድርም ላይ በሚሳብ ተንቀሳቃሽ ሁሉ ሰውነታችሁን አታሳድፉ። እኔ አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ እንግዲህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ። 46 “የእንስሳና የወፍ፥ በውኃውም ውስጥ የሚንቀሳቀስ የፍጥረት ሁሉ፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀስ የፍጥረት ሁሉ ሕግ ይህ ነው። 47 በርኩስና በንጹሕ መካከል፥ የሕይወት ነፍስ ካላቸውም በምትበሉትና በማትበሉት መካከል እንድትለዩ ነው።” |