ዘፀአት 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)8፥ የአንበጣ መንጋ 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ “ወደ ፈርዖን ግባ፤ እኔ የፈርዖንንና የሹሞቹን ልብ አጽንቼአለሁና፥ ተአምራቴ በእነርሱ ላይ በትክክል ይመጣ ዘንድ፤ 2 በግብፃውያንም ላይ የተዘባበትሁትን ሁሉ፥ ያደረግሁባቸውንም ተአምራቴን በልጆቻችሁና በልጅ ልጆቻችሁ ጆሮች ትነግሩ ዘንድ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።” 3 ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፤ አሉትም፥ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔን ማፈርን እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 4 ሕዝቤን ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን፥ እነሆ፥ ነገ በዚህ ጊዜ በተራራዎችህ ሁሉ ላይ አንበጣን አመጣለሁ፤ 5 የምድሩንም ፊት ይሸፍናል፤ ምድሩን ለማየት አይቻልም፤ ከበረዶውም ተርፎ በምድር ላይ የቀረላችሁን ትርፍ ሁሉ ይበላል፤ ያደገላችሁንም የእርሻውን ዛፍ ሁሉ ይበላል፤ 6 ቤቶችህም የሹሞችህም ሁሉ ቤቶች፥ የግብፃውያን ሁሉ ቤቶች በእርሱ ይሞላሉ፤ አባቶችህ፥ የአባቶችህም አባቶች በምድር ላይ ከተቀመጡበት ቀን ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያላዩት ነው።” ሙሴም ተመልሶ ከፈርዖን ዘንድ ወጣ። 7 የፈርዖንም ሹሞች፥ “ይህ ሰው እስከ መቼ እንቅፋት ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን ያመልኩት ዘንድ ሰዎችን ልቀቅ፤ ግብፅስ እንደ ጠፋች ገና አታውቅምን?” አሉት። 8 ሙሴንና አሮንንም ወደ ፈርዖን ጠሩአቸው፤ ፈርዖንም እንዲህ አላቸው፥ “ሂዱ፤ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ነገር ግን ከእናንተ ጋር የሚሄዱት እነማን ናቸው?” 9 ሙሴም አለው፥ “እኛ ከታናናሾቻችንና ከሽማግሌዎቻችን፥ ከወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ጋር እንሄዳለን፤ በጎቻችንንና ላሞቻችንንም እንወስዳለን። የአምላካችን የእግዚአብሔር በዓል ነውና።” 10 ፈርዖንም አላቸው፥ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤ እነሆ፥ እናንተን ስለቅ ልጆቻችሁንም መልቀቅ አለብኝን? ክፉ ነገር እንደሚገጥማችሁ ዕወቁ። 11 እንዲህም አይደለም፤ እናንተ ወንዶቹ ሂዱ፤ ይህን ፈልጋችኋልና እግዚአብሔርን አምልኩ” አላቸው። ሙሴንና አሮንንም ከፈርዖን ፊት አስወጡአቸው። 12 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “በግብፅ ሀገር ላይ እጅህን ዘርጋ፤ አንበጣም በምድር ላይ ይወጣል፤ ከበረዶውም የተረፈውን የምድር ቡቃያ ሁሉና የዛፉን ፍሬ ሁሉ ይበላል።” 13 ሙሴም በትሩን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም የደቡብን ነፋስ ያን ቀን ሁሉ ሌሊቱንም ሁሉ አመጣ፤ ማለዳም በሆነ ጊዜ የደቡብ ነፋስ አንበጣን አመጣ። 14 አንበጣም በግብፅ ሀገር ሁሉ ላይ ወጣ፤ በግብፅም ዳርቻ ሁሉ ላይ ተቀመጠ፤ እጅግም ብዙና ጠንካራ ነበር፤ ይህንም የሚያህል አንበጣ በፊት አልነበረም፤ ወደፊትም ደግሞ እንደ እርሱ አይሆንም። 15 የምድሩንም ፊት ፈጽሞ ሸፈነው፤ ሀገሪቱም ጠፋች፤ የሀገሪቱን ቡቃያ ሁሉ ከበረዶውም የተረፈውን፥ በዛፉ የነበረውን ፍሬ ሁሉ በላ፤ ለምለም ነገር በዛፎች ላይ፥ በእርሻውም ቡቃያ ሁሉ ላይ በግብፅ ሀገር ሁሉ አልቀረም። 16 ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በፍጥነት ጠራ፥ “በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት፥ በእናንተም ላይ በደልሁ፤ 17 አሁን እንግዲህ እንደገና በዚህ ጊዜ ብቻ ኀጢአቴን ይቅር በሉኝ፤ ይህንም ሞት ብቻ ከእኔ ያነሣልኝ ዘንድ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ” አላቸው። 18 ሙሴም ከፈርዖን ፊት ወጣ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ። 19 እግዚአብሔርም ከባሕር ዐውሎ ነፋሱን አስወገደ፤ አንበጣዎችንም ወስዶ በኤርትራ ባሕር ውስጥ ጣላቸው፤ አንድ አንበጣም እንኳን በግብፅ ዳርቻ ሁሉ አልቀረም። 20 እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አጸና የእስራኤልንም ልጆች አልልቀቀም። 9፥ ጨለማ 21 እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ፤ በግብፅም ሀገር ላይ ጨለማ ይሁን፤ ጨለማውም የሚዳሰስ ነው” አለው። 22 ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ በግብፅም ሀገር ሁሉ ላይ ጽኑ ጨለማና ጭጋግ ሦስት ቀን ሆነ፤ 23 ማንም ወንድሙን አላየም፤ ሦስት ቀን ሙሉም ከመኝታው ማንም አልተነሣም፤ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ግን በተቀመጡበት ስፍራ ሁሉ ብርሃን ነበራቸው። 24 ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ፥ “ሂዱ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ነገር ግን በጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ብቻ ተዉ፤ ልጆቻችሁና ሴቶቻችሁ ግን ከእናንተ ጋር ይሂዱ” አላቸው። 25 ሙሴም አለው፥ “አይሆንም! አንተ ደግሞ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የምንሠዋው መሥዋዕትንና የሚቃጠል መሥዋዕትን ትሰጠናለህ። 26 ከብቶቻችን ከእኛ ጋር ይሄዳሉ፤ አንድ ሰኰናም አይቀርም፤ አምላካችንን እግዚአብሔርን ለማምለክ ከእነርሱ እንወስዳለንና፤ አምላካችንን እግዚአብሔርን እንደምናመልከው ከዚያ እስክንደርስ አናውቅም።” 27 እግዚአብሔርም የፈርዖንን ልብ አጸና፤ ሊለቅቃቸውም አልወደደም። 28 ፈርዖንም ሙሴን፥ “ከእኔ ዘንድ ሂድ፤ በፊቴ በምትታይበት ቀን ትሞታለህና ዳግመኛ ፊቴን እንዳታይ ተጠንቀቅ” አለው። 29 ሙሴም፥ “እንደ ተናገርህ ይሁን፤ ፊትህን እንደገና አላይም” አለ። |