ይሁዳ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሰላምታ 1 የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ፤ 2 ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ። ስለ ሐሰተኞች መምህራን 3 ወዳጆች ሆይ! ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ። 4 ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኀጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ፤ ብቻውን ንጉሣችንንና ጌታችንንም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ። 5 ዳሩ ግን ሁሉን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ምንም የተማራችሁ ብትሆኑ ጌታ ከግብጽ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ። 6 መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል። 7 እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል። 8 እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ደግሞ እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ፤ ጌትነትንም ይጥላሉ፤ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ። 9 የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር “ጌታ ይገሥጽህ!” አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም። 10 እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፤ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ። 11 ወዮላቸው! በቃየል መንገድ ሄደዋልና፤ ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፤ በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል። 12 እነዚህ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው፤ እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ፤ በነፋስ የተወሰዱ ውሃ የሌለባቸው ደመናዎች፥ ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች፥ 13 የገዛ ነውራቸውን አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባሕር ማዕበል፥ ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸው። 14-15 ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ “እነሆ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፥ በኀጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኀጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዐመፀኞችም ኀጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኀጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል፤” ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ። 16 እነዚህ እንደ ምኞታቸው እየሄዱ የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸው የሚያጕረመርሙ ናቸው፤ እንዲረባቸውም ለሰው ፊት እያደሉ አፋቸው ከመጠን ይልቅ ታላቅ ቃል ይናገራል። ማስጠንቀቂያና ምክር 17 እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ! በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤ 18 እነርሱ “በመጨረሻው ዘመን በኀጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ፤” ብለዋችኋልና። 19 እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው። 20 እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ! ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥ 21 ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ። 22 አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፤ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፤ 23 አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ። 24 ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው፤ 25 ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኀይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን። |