ኢሳይያስ 20 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በኢትዮጵያና በግብፅ የተነገረ ትንቢት 1 የአሦር ንጉሥ አርና ጣንታንን በሰደደ ጊዜ፥ እርሱም ወደ አዛጦን በመጣ ጊዜ፥ አዛጦንንም ወግቶ በያዛት ጊዜ፥ 2 በዚያ ዓመት እግዚአብሔር የአሞጽን ልጅ ኢሳይያስን፥ “ሂድ፥ ማቅህን ከወገብህ አውጣ፤ ጫማህንም ከእግርህ አውልቅ፤ ያለጫማም በባዶ እግርህ ሂድ” ብሎ ተናገረው። እንዲህም አደረገ፤ ራቁቱንም ያለ ጫማ ሄደ። 3 እግዚአብሔርም አለ፥ “ባሪያዬ ኢሳይያስ ሦስት ዓመት ራቁቱን በባዶ እግሩ እንደ ሄደ፥ እንዲሁ በግብፅና በኢትዮጵያ ላይ ሦስት ዓመት ምልክትና ተአምራት ይደረጋል። 4 እንዲሁ የአሦር ንጉሥ የግብፅንና የኢትዮጵያን ምርኮ፥ ጐበዛዝቱንና ሽማግሌዎቹን ራቁታቸውንና ባዶ እግራቸውን አድርጎ፥ ገላቸውንም ገልጦ ለግብፅ ኀፍረት ይነዳቸዋል። 5 ግብፃውያን ከኢትዮጵያውያን ጋር ይሸነፋሉ፤ ግብፃውያንም ከታመኑባቸው ጋር ይፈራሉ፤ ያፍሩማል። 6 በዚያም ቀን በዚች ደሴት የሚቀመጡ፦ እነሆ፥ ለርዳታ ወደ እነርሱ የሸሸንበት ተስፋችን ይህ ነበረ፤ ከአሦር ንጉሥ ራሳቸውን ያላዳኑ እኛን እንዴት ያድኑናል?” ይላሉ። |