አሞጽ 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእግዚአብሔር ፍርድ በእስራኤል ላይ 1 እግዚአብሔርን በመሠውያው ላይ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “አበቦች የተሳሉባቸውን ምሰሶዎችን ምታ፤ መድረኮቹም ይናወጣሉ፤ ራሳቸውንም ቍረጥ፤ እኔም ከእነርሱ የቀሩትን በሰይፍ እገድላለሁ፤ ከሚሸሹትም የሚያመልጥ የለም፤ ከሚያመልጡትም የሚድን የለም። 2 ወደ ሲኦል ቢወርዱ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፤ ወደ ሰማይም ቢወጡ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤ 3 በቀርሜሎስ ራስ ውስጥ ቢሸሸጉ ፈልጌ ከዚያ አወጣቸዋለሁ፤ በባሕሩም ጥልቅ ውስጥ ከዐይኔ ቢደበቁ በዚያ እባቡን አዝዛለሁ፤ እርሱም ይነድፋቸዋል፤ 4 በጠላቶቻቸውም ፊት ተማርከው ቢሄዱ በዚያ ሰይፍን አዝዛታለሁ፤ እርስዋም ትገድላቸዋለች፤ ዐይኔንም ለመልካም ሳይሆን ለክፋት በእነርሱ ላይ እጥላለሁ።” 5 ሁሉን የሚችል ጌታ እግዚአብሔር ምድርን ሁሉ ይዳስሳል፤ ያነዋውጣታልም፤ የሚኖሩባትም ሁሉ ያለቅሳሉ፤ ግድያ እንደ ወንዝ ይፈስሳል፤ ደግሞም እንደ ግብፅ ወንዝ ይወርዳል። 6 አዳራሹን በሰማይ የሠራ፥ ትእዛዙንም በምድር ላይ የመሠረተ፥ የባሕርንም ውኃ ጠርቶ በምድር ፊት የሚያፈስሰው እርሱ ነው፤ ስሙም ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ነው። 7 “የእስራኤል ልጆች ሆይ! እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር። እስራኤልን ከግብፅ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከቀጰዶቅያ፥ ሶርያውያንንም ከጕድጓድ ያወጣሁ አይደለምን? 8 እነሆ የጌታ የእግዚአብሔር ዐይኖች በኀጢአተኛ መንግሥት ላይ ናቸው፤ ከምድርም ፊት አጠፋታለሁ፤ ነገር ግን የያዕቆብን ቤት ፈጽሜ አላጠፋም፤ ይላል እግዚአብሔር። 9 እነሆ አዝዛለሁ፤ እህልም በመንሽ እንደሚዘራ የእስራኤልን ቤት በአሕዛብ ሁሉ መካከል እዘራለሁ፤ ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም። 10 ክፉው ነገር አይደርስብንም፤ አያገኘንምም የሚሉ የሕዝቤ ኀጢአተኞች ሁሉ በሰይፍ ይሞታሉ። የእስራኤል ተስፋ 11 “በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ቤት አነሣለሁ፤ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ፤ የፈረሰውንም አድሳለሁ፤ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ፤ 12 ይኸውም የቀሩ ሰዎችንና ስሜም የተጠራባቸውን አሕዛብን ሁሉ ይፈልጉ ዘንድ ነው” ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር። 13 “እነሆ፥ እንዲህ ያለ ወራት ይመጣልን? ይላል እግዚአብሔር፤ እርሻ ከአጨዳ ጋር፥ ዘርም ከእሸት ጋር አንድ ይሆናል፤ ከተራሮችም ማር ይፈስሳል፤ ኮረብታውም ይለመልማል። 14 የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፤ የፈረሱትንም ከተሞች ሠርተው ይቀመጡባቸዋል፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ የወይን ጠጃቸውንም ይጠጣሉ፤ ተክልን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። 15 በምድራቸውም እተክላቸዋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ከሰጠኋቸው ከምድራቸው አይነቀሉም” ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር አምላክ። |