ሐዋርያት ሥራ 13:17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መረጣቸው፤ ወገኖቹንም በተሰደዱበት በምድረ ግብፅ ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ ከዚያም ከፍ ባለ ክንዱ አወጣቸው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ፣ አባቶቻችንን መረጣቸው፤ በግብጽ ምድር እያሉም ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ በኀያል ክንዱም ከዚያ አወጣቸው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብጽ አገር በእንግድነት ሳሉ ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ ከፍ ባለችውም ክንዱ ከዚያ አወጣቸው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ የቀድሞ አባቶቻችንን መረጠ፤ በግብጽ አገር በነበሩበት ጊዜም ትልቅ ሕዝብ አደረጋቸው፤ በታላቅ ኀይሉም ከዚያ አገር አወጣቸው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብፅ አገር በእንግድነት ሳሉ ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፥ ከፍ ባለችውም ክንዱ ከዚያ አወጣቸው። |
እንዲህም ይሆናል፤ ከዚህ በኋላ ልጅህ፦ ‘ይህ ምንድን ነው?’ ብሎ በጠየቀህ ጊዜ እንዲህ ትለዋለህ፦ እግዚአብሔር በብርቱ እጅ ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር አወጣን፤
እግዚአብሔርም በብርቱ እጅ ከግብፅ አውጥቶሃልና በእጅህ እንደ ምልክት ፥ ከዐይኖችህም እንደማይርቅ ነገር ይሁንልህ።”
እግዚአብሔርም የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንንና የሹሞቹን ልብ አጸና፤ እርሱም የእስራኤልን ልጆች አሳደደ፤ የእስራኤልም ልጆች ከፍ ባለች እጅ ወጡ።
አባቶችህ ሰባ ነፍስ ሆነው ወደ ግብፅ ወረዱ፤ አሁን ግን አምላክህ እግዚአብሔር ብዛትህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አደረገ።
ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፥ በምድርም ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ እግዚአብሔር አንተን መርጦአልና።
አምላካችን እግዚአብሔር በዐይናችሁ ፊት በግብፅ ለእናንተ እንደ ሠራው ሁሉ ፥ በፈተናና በተአምራት፥ በድንቅና በሰልፍ፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በታላቅም ማስፈራራት እግዚአብሔር ከሌላ ሕዝብ መካከል ገብቶ ለእርሱ ሕዝብን ይወስድ ዘንድ ሞክሮ እንደ ሆነ፥
አምላክህ እግዚአብሔር ዓይንህ እያየች፥ ታላቅ መቅሠፍትን፥ ምልክትንም፥ ተአምራትንም፥ የጸናችውንም እጅ፥ የተዘረጋውንም ክንድ አድርጎ እንዳወጣህ፤ እንዲሁ አምላክህ እግዚአብሔር አንተ በምትፈራቸው በአሕዛብ ሁሉ ላይ ያደርጋል።
ምድራቸውን ትወርሳት ዘንድ የምትገባው ስለ ጽድቅህና ስለ ልብህ ቅንነት አይደለም፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ በሚያጠፋቸው በእነዚያ አሕዛብ ኀጢአት ምክንያትና ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውን ቃል ያጸና ዘንድ ነው።
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤
ወዮልን! ከእነዚህ ኀያላን አማልክት እጅ ማን ያድነናል? እነዚህ አማልክት ግብፃውያንን በምድረ በዳ በልዩ ልዩ መቅሠፍት የመቱ ናቸው።