ዘዳግም 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሙሴ ዐሥሩ ትእዛዛትን እንደ ገና መቀበሉ ( ዘፀ. 34፥1-10 ) 1 “በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር እንደ ፊተኞች ያሉትን ሁለት የድንጋይ ጽላት ለአንተ ቀርፀህ ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፤ ለአንተም የእንጨት ታቦት ሥራ፤ 2 በሰበርሃቸው በፊተኞቹ ጽላት የነበሩትን ቃሎች ሁሉ በእነዚህ ጽላት እጽፋለሁ፤ በታቦቱም ውስጥ ታደርጋቸዋለህ አለኝ። 3 ከማይነቅዝ እንጨትም ታቦቱን ሠራሁ፤ እንደ ፊተኞችም ሁለት የድንጋይ ጽላት ቀረፅሁ፤ ወደ ተራራውም ወጣሁ፤ ሁለቱም ጽላት በእጄ ነበሩ፤ 4 እግዚአብሔርም በተራራው ላይ በእሳት መካከል የተናገራችሁን ዐሠርቱን ቃላት ቀድሞ ተጽፈው እንደ ነበረ በጽላቱ ላይ ጻፈ፤ እግዚአብሔርም እነርሱን ለእኔ ሰጠኝ። 5 ተመልሼም ከተራራው ወረድሁ፤ ጽላቱንም በሠራሁት ታቦት ውስጥ አደረግኋቸው፤ እግዚአብሔርም እንዳዘዘኝ በዚያ ኖሩ። 6 “የእስራኤልም ልጆች የማስቢ ወገን ከሚሆን ከኢያቅም ልጆች ቦታ ከቤሮስ ተጓዙ። በዚያም አሮን ሞተ፤ ተቀበረም፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ አልዓዛር ካህን ሆነ። 7 ከዚያም ወደ ገድገድ ተጓዙ፤ ከገድገድም ወደ ውኃ ፈሳሾች ምድር ወደ ኤጤባታ ተጓዙ። 8 በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ይሸከም ዘንድ፥ እርሱንም ለማገልገል በእግዚአብሔር ፊት ይቆም ዘንድ፥ በስሙም ይባርክ ዘንድ እግዚአብሔር እስከ ዛሬ ድረስ የሌዊን ነገድ ለየ። 9 ስለዚህ ለሌዋውያን ከወንድሞቻቸው ጋር ክፍልና ርስት የላቸውም፤ አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ነገራቸው እግዚአብሔር ርስታቸው ነውና። 10 “እኔም እንደ ፊተኛው ጊዜ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በተራራው ላይ ቆምሁ፤ እግዚአብሔርም በዚህ ጊዜ ደግሞ ሰማኝ፤ እግዚአብሔርም ሊያጠፋችሁ አልወደደም። 11 እግዚአብሔርም፦ ‘ተነሥተህ በሕዝቡ ፊት ተጓዝ፤ ለአባቶቻቸውም ልሰጣቸው ወደ ማልሁላቸው ምድር ይግቡ፤ ይውረሱአትም’ አለኝ። ከእስራኤል የሚፈለገው እግዚአብሔርን መፍራት መሆኑ 12 “እስራኤል ሆይ፥ አሁንስ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? አምላክህን እግዚአብሔርን ትፈራ ዘንድ፥ በመንገዱም ሁሉ ትሄድ ዘንድ፥ አምላክህንም እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ በፍጹምም ልብህ፥ በፍጹምም ነፍስህ ታመልከው ዘንድ ነው እንጂ፥ 13 መልካምም እንዲሆንልህ ዛሬ ለአንተ የማዝዘውን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝና ሥርዐት ትጠብቅ ዘንድ ነው እንጂ፤ 14 እነሆ፥ ሰማይ፥ ሰማየ ሰማያትም፥ ምድርም፥ በእርስዋም ያለው ሁሉ የአምላክህ የእግዚአብሔር ነው። 15 ብቻ እግዚአብሔር አባቶቻችሁን መረጣቸው፤ ወደዳቸውም፤ ከእነርሱም በኋላ እናንተን ዘራቸውን እንደ ዛሬው ሁሉ ከአሕዛብ ሁሉ መረጠ። 16 እናንተ የልባችሁን ክፋት ግዘሩ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አንገታችሁን አታደንድኑ። 17 አምላካችሁ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ፥ የጌቶች ጌታ፥ ታላቅ አምላክ፥ ኀያልም፥ የሚያስፈራም፥ በፍርድም የማያደላ፥ መማለጃም የማይቀበል ነውና። 18 ለመጻተኛ፥ ለድሃ አደጉና ለመበለቲቱ ይፈርዳል፤ መብልና ልብስም ይሰጠው ዘንድ ስደተኛውን ይወድዳል። 19 እናንተ በግብፅ ሀገር ስደተኞች ነበራችሁና ስለዚህ ስደተኛውን ውደዱ። 20 አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም አምልክ፤ እርሱንም ተከተል፤ በስሙም ማል። 21 ዐይኖችህ ያዩአቸውን እነዚህን ታላላቆች የከበሩትን ነገሮች ያደረገልህ እርሱ መመኪያችሁ ነው፤ እርሱም አምላክህ ነው። 22 አባቶችህ ሰባ ነፍስ ሆነው ወደ ግብፅ ወረዱ፤ አሁን ግን አምላክህ እግዚአብሔር ብዛትህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አደረገ። |