ዘዳግም 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የተከለከለ የልቅሶ ልማድ 1 “ለሞተ ሰውም በዐይናችሁ መካከል ፊታችሁን አትንጩ፤ ራሳችሁንም አትላጩ፤ 2 ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፥ በምድርም ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ እግዚአብሔር አንተን መርጦአልና። የሚበሉና የማይበሉ እንስሶች ( ዘሌ. 11፥1-47 ) 3 “ርኩስን ነገር ሁሉ አትብሉ። 4 የምትበሉአቸው እንስሶች እነዚህ ናቸው፤ በሬ፥ በግ፥ ፍየል፥ 5 ዋልያ፥ ሚዳቋ፥ የበረሃ ፍየል፥ ጎሽ፥ ብሖር፥ ሳላ፥ ድኵላ። 6 ከእንስሶች ሰኰናው የተሰነጠቀውን፥ ጥፍሩም ከሁለት የተከፈለውን፥ የሚያመሰኳውንም እንስሳ ሁሉ ትበላለህ። 7 ነገር ግን ከሚያመሰኩ ወይም ሰኰናቸው ከተሰነጠቀ እነዚህን አትበሉም፤ ግመልን፥ ሽኮኮን፥ ጥንቸልን አትበሉም፤ ያመሰኳሉና፥ ነገር ግን ሰኰናቸው አልተሰነጠቀምና እነዚህ ለእናንተ ርኩሳን ናቸው። 8 እርያም፥ ሰኰናው ስለተሰነጠቀ፥ ጥፍሩም ከሁለት ስለተከፈለ፥ ነገር ግን ሰለማያመሰኳ፥ እርሱ ለእናንተ ርኩስ ነው፤ ሥጋዉን አትብሉ፤ በድኑንም አትንኩ። 9 “በውኆች ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ የምትበሉአቸው እነዚህ ናቸው፤ ክንፍና ቅርፊትም ያላቸውን ትበላላችሁ፤ 10 ክንፍና ቅርፊትም የሌላቸውን አትበሉም፤ ለእናንተ ርኩሳን ናቸው። 11 “ንጹሓን የሆኑትን ወፎች ሁሉ ብሉ። 12 ሊበሉ የማይገባቸው ግን እነዚህ ናቸው፤ ንስር፥ ገዴ፥ ዓሣ አውጭ። 13 ጭልፊት፥ ጭላትና መሰሎቻቸው፥ 14 ቍራና መሰሎቹ፤ 15 ሰጎን፥ አራት ራስ አሞራ፥ ዝዪ፥ በቋል በየወገኑ። 16 ጉጉት፥ ጋጋኖ፥ የውኃ ዶሮ። 17 ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራና መሰሎቻቸው፥ 18 ዕርኩም፥ ሽመላ፥ ሳቢሳና መሰሎቹ፥ ጅንጅላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ። 19 የሚበርሩም አዕዋፍ ሁሉ ለእናንተ ንጹሓን አይደሉምና ከእነርሱ አትብሉ፤ 20 ነገር ግን ንጹሓን የሆኑትን ወፎች ሁሉ ብሉ። 21 የበከተዉን ሁሉ አትብሉ፤ ይበላው ዘንድ በሀገርህ ደጅ ለተቀመጠ መጻተኛ ወይም ለባዕድ ስጠው፤ አንተ ለአምላካህ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ ነህና፥ የፍየሉን ጠቦት በእናቱ ወተት አትቀቅል። የዐሥራት አወጣጥ ሕግ 22 “ከእርሻህ ዘርተህ በየዓመቱ ከምታገኘው እህልህ ሁሉ ዐሥራት ታወጣለህ። 23 በዘመንህም ሁሉ አምላክህን እግዚአብሔርን መፍራትን ትማር ዘንድ፥ ስሙ እንዲጠራበት በመረጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት የእህልህን፥ የወይንህን፥ የዘይትህንም ዐሥራት፥ የላምህንና የበግህንም በኵራት ብላ። 24 አምላክህ እግዚአብሔር ባርኮሃልና፥ መንገዱ ሩቅ ቢሆን፥ አምላክህም እግዚአብሔር ስሙን ያኖርበት ዘንድ የመረጠው ስፍራ ቢርቅብህ፥ ይህን ወደዚያ ለመሸከም ባትችል፥ 25 በብር ትሸጠዋለህ፤ ብሩንም በእጅህ ይዘህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ትሄዳለህ። 26 በዚያም በብሩ ሰውነትህ የፈለገውን፥ በሬ ወይም በግ፥ ወይም የወይን ጠጅ፥ ወይም ብርቱ መጠጥ፥ ሰውነትህ የሚሻውን ሁሉ ትገዛለህ፤ በዚያም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ትበላዋለህ፤ አንተና ቤተ ሰብህም ደስ ይላችኋል። 27 ድርሻና ርስት ከአንተ ጋር ስለሌለው በከተማህ ውስጥ ያለውን ሌዋዊ ቸል አትበል። 28 “በየሦስተኛው ዓመት መጨረሻ በዚያ ዓመት የፍሬህን ዐሥራት ሁሉ አምጥተህ በከተማዎችህ ውስጥ ታኖረዋለህ። 29 ሌዋዊዉም፥ ከአንተ ጋር ክፍልና ርስት የለውምና፥ በከተማህ ውስጥ ያለ መጻተኛ፥ ድሃ-አደግም፥ መበለትም መጥተው ይበላሉ፤ ይጠግባሉም፤ ይኸውም አምላክህ እግዚአብሔር በምታደርገው በእጅህ ሥራ ሁሉ ይባርክህ ዘንድ ነው። |