ዘፀአት 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በኵር ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ መሆኑ 1 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “በእስራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም፥ ከእንስሳም መጀመሪያ የተወለደውን ማሕፀንን የሚከፍት በኵር ሁሉ ለእኔ ለይልኝ፤ የእኔ ነው።” የቂጣ በዓል 3 ሙሴም ሕዝቡን አለ፥ “ከባርነት ቤት ከግብፅ የወጣችሁባትን ይህችን ቀን ዐስቡ፤ እግዚአብሔር ከዚህ ቦታ በበረታች እጅ አውጥቶአችኋልና። ስለዚህ የቦካ እንጀራ አትብሉ። 4 እናንተ በዚች ቀን በሚያዝያ ወር ወጥታችኋልና። 5 እግዚአብሔርም ለእናንተ ይሰጣት ዘንድ ለአባቶቻችሁ ወደማለላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር፥ ወደ ከናኔዎናውያን፥ ወደ ኬጢዎናውያንም፥ ወደ አሞሬዎናውያንም፥ ወደ ኤዌዎናውያን፥ ወደ ኢያቡሴዎናውያንም፥ ወደ ጌርጌሴዎናውያንም፥ ወደ ፌርዜዎናውያንም ምድር በአገባችሁ ጊዜ ይህችን ሥርዐት በዚህ ወር አድርጉ። 6 ስድስት ቀን ቂጣ ትበላላችሁ፤ ሰባተኛውም ቀን የእግዚአብሔር በዓል ይሆናል። 7 ሰባት ቀንም ሙሉ ቂጣ ትበላላችሁ፤ በእናንተም ዘንድ እርሾ ያለበት እንጀራ አይታይ፤ በአውራጃዎቻችሁ ሁሉ እርሾ አይኑር። 8 በዚያም ቀን፦ ‘ከግብፅ በወጣሁ ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ ስለአደረገልኝ ነው’ ስትል ለልጅህ ትነግረዋለህ። 9 እግዚአብሔርም በበረታች እጅ ከግብፅ አውጥቶሃልና የእግዚአብሔር ሕግ በአፍህ ይሆን ዘንድ በእጅህ እንደ ምልክት፥ በዐይኖችህም መካከል እንደ መታሰቢያ ይሁንልህ። 10 ከቀን ወደ ቀን በየጊዜው ይህን ሕግ ጠብቁት። 11 “እግዚአብሔርም ለአባቶችህ እንደማለ ወደ ከነዓናውያን ምድር በአገባህ ጊዜ፥ እርስዋንም ለአንተ በሰጠህ ጊዜ፥ 12 ማሕፀንን የሚከፍተውን ሁሉ ለይ፤ ከመንጋህና ከከብትህም መጀመሪያ የሚወለደው ተባት ለእግዚአብሔር ይሆናል። 13 የአህያውን በኵር በበግ ትለውጠዋለህ፤ ባትለውጠው ግን ትዋጀዋለህ። የሰውንም በኵር ሁሉ ከልጆችህ መካከል ትዋጀዋለህ። 14 እንዲህም ይሆናል፤ ከዚህ በኋላ ልጅህ፦ ‘ይህ ምንድን ነው?’ ብሎ በጠየቀህ ጊዜ እንዲህ ትለዋለህ፦ እግዚአብሔር በብርቱ እጅ ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር አወጣን፤ 15 ፈርዖንም እኛን ለመልቀቅ እንቢ ባለ ጊዜ እግዚአብሔር ከሰው በኵር ጀምሮ እስከ እንስሳ በኵር ድረስ በግብፅ ምድር ያለውን በኵር ሁሉ ገደለ፤ ስለዚህ ወንድ ሆኖ ማሕፀንን የከፈተውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሠዋለሁ፤ ነገር ግን የልጆችን በኵር ሁሉ እዋጃለሁ።’ 16 እግዚአብሔርም በብርቱ እጅ ከግብፅ አውጥቶሃልና በእጅህ እንደ ምልክት ፥ ከዐይኖችህም እንደማይርቅ ነገር ይሁንልህ።” የደመና ዐምድና የእሳት ዐምድ 17 እንዲህም ሆነ፤ ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ፥ ምንም ቅርብ ቢሆን እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ምድር መንገድ አልመራቸውም፤ እግዚአብሔር፥ “ሕዝቡ ሰልፉን በአየ ጊዜ እንዳይጸጽተው፥ ወደ ግብፅም እንዳይመለስ” ብሎአልና። 18 ነገር ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን በዙሪያ መንገድ በኤርትራ ባሕር ባለችው ምድረ በዳ መራቸው። የእስራኤልም ልጆች በአምስተኛው ትውልድ ከግብፅ ምድር ወጡ። 19 ሙሴም የዮሴፍን ዐጽም ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ “እግዚአብሔር መጐብኘትን በጐበኛችሁ ጊዜ ዐጽሜን ውሰዱ፤ ከእናንተም ጋር ከዚህ አውጡ” ብሎ የእስራኤልን ልጆች አምሎአቸው ነበርና። 20 የእስራኤል ልጆችም ከሱኮት ተጓዙ፤ በምድረ በዳውም ዳር በኦቶም ሰፈሩ። 21 እግዚአብሔርም መንገድ ሊያሳያቸው ቀን በዐምደ ደመና፥ ሌሊትም በዐምደ እሳት ይመራቸው ነበር። 22 ዐምደ ደመናው በቀን፥ ዐምደ እሳቱም በሌሊት ከሕዝቡ ፊት ከቶ ፈቀቅ አላለም። |