ሐዋርያት ሥራ 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በርናባስና ሳውል ለስብከተ ወንጌል እንደ ተመረጡ 1 በአንጾኪያ በነበረችው ቤተ ክርስቲያንም ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖን፥ የቀሬናው ሉቅዮስ፥ ከአራተኛው ክፍል ገዢ ከሄሮድስ ጋር ያደገው ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። 2 የእግዚአብሔርን ሥራ ሲሠሩ፥ ሲጾሙም መንፈስ ቅዱስ፥ “በርናባስንና ሳውልን እኔ ለፈለግኋቸው ሥራ ለዩልኝ” አላቸው። 3 ያንጊዜም ከጾሙና ከጸለዩ፥ እጃቸውንም በራሳቸው ላይ ከጫኑባቸው በኋላ ላኩአቸው። በርናባስና ሳውል በቆጵሮስ እንደ አስተማሩ 4 ከመንፈስ ቅዱስም ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። 5 ወደ ሰልሚና ሀገርም ገብተው በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሩ፤ ዮሐንስም እየአገለገላቸው ከእነርሱ ጋር ነበር። 6 በደሴቲቱም ሁሉ ሲዘዋወሩ ጳፉ ወደምትባል ሀገር ደረሱ፤ በዚያም አንድ አይሁዳዊ የሆነ ሐሰተኛ ነቢይና አስማተኛ ሰው አገኙ፤ ስሙም በርያሱስ ይባላል። 7 እርሱም ብልህ ሰው በሆነ ሰርግዮስ ጳውሎስ በሚባል አገረ ገዢ ዘንድ ይኖር ነበረ። የእግዚአብሔርንም ቃል ሊሰማ ወድዶ በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠራቸው። 8 አስማተኛው ኤልማስም የስሙ ትርጓሜ እንዲህ ነበረና፥ ገዥውን ከማመን ሊከለክለው ፈልጎ ተቃወማቸው። 9 ጳውሎስ በተባለው በሳውል ላይም ቅዱስ መንፈስ ሞላበት፤ አተኵሮም ተመለከተው። 10 እንዲህም አለው፥ “ሽንገላንና ክፋትን ሁሉ የተመላህ፥ የሰይጣን ልጅ፥ የጽድቅ ሁሉ ጠላት ሆይ፥ የቀናውን የእግዚአብሔርን መንገድ ማጣመምህን ትተው ዘንድ እንቢ አልህን? 11 እነሆ፥ አሁን የእግዚአብሔር እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም፤” ወዲያውኑም ታወረ፤ ጨለማም ዋጠው፤ የሚመራውም ፈለገ። 12 አገረ ገዢውም የሆነውን በአየ ጊዜ ተገረመ፤ በጌታችን ትምህርትም አመነ። በርናባስና ጳውሎስ በጲስድያ አንጾኪያ እንደ አስተማሩ 13 ከዚህም በኋላ እነ ጳውሎስ ከጳፉ ከተማ ወጥተው ሄዱና የጵንፍልያ አውራጃ ወደምትሆን ወደ ጰርጌን ገቡ፤ ዮሐንስ ግን ትቶአቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። 14 እነርሱም ከጰርጌን አልፈው የጲስድያ አውራጃ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ። 15 ኦሪትንና ነቢያትን ካነበቡ በኋላም የምኵራቡ አለቆች፥ “እናንተ ወንድሞቻችን ሆይ፥ ለሕዝብ ሊነገር የሚገባው የምክር ቃል እንደ አላችሁ ተናገሩ” ብለው ላኩባቸው። 16 ጳውሎስም ተነሥቶ ዝም እንዲሉ አዘዘና እንዲህ አላቸው፥ “እናንት የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርንም የምትፈሩ ሁሉ፥ ስሙ። 17 የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መረጣቸው፤ ወገኖቹንም በተሰደዱበት በምድረ ግብፅ ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ ከዚያም ከፍ ባለ ክንዱ አወጣቸው። 18 አርባ ዘመንም በምድረ በዳ መገባቸው። 19 ሰባቱን የከነዓንን አሕዛብ አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው። 20 ከዚህም በኋላ አራት መቶ አምሳ ዓመት እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ዘመን ድረስ መሳፍንትን ሾመላቸው። 21 ከዚያም ወዲያ ንጉሥ ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ነገድ የተወለደውን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት አነገሠላቸው። 22 እርሱንም ሻረው፤ ከእርሱም በኋላ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ ‘የእሴይን ልጅ ዳዊትን ፈቃዴን ሁሉ የሚፈጽም እንደ ልቤም የታመነ ሰው ሆኖ አገኘሁት’ ብሎ መሰከረለት። 23 እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጣቸው ከዳዊት ዘር ለእስራኤል መድኀኒት አድርጎ ኢየሱስን አመጣላቸው። 24 እርሱ ከመምጣቱ አስቀድሞ ዮሐንስ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሓ ጥምቀትን ሰበከላቸው። 25 ዮሐንስም መልእክቱን ሲፈጽም እንዲህ አላቸው፦ ‘እኔን ለምን ትጠራጠሩኛላችሁ? እርሱን አይደለሁም፤ የጫማውን ማዘቢያ ከእግሩ ልፈታ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ እነሆ፥ ይመጣል።’ 26 “እናንተ ከአብርሃም ወገን የተወለዳችሁ ወንድሞቻችን እግዚአብሔርንም የምትፈሩ፥ ይህ የሕይወት ቃል ለእናንተ ተልኮአል። 27 በኢየሩሳሌም የሚኖሩና አለቆቻቸው ግን እርሱን አላወቁም፤ የነቢያት መጻሕፍትንም በየሰንበቱ ሁሉ ሲያነቡ አላስተዋሉትም፤ ነገር ግን ይሙት በቃ ፈረዱበት፥ ስለ እርሱ የተጻፈውንም ሁሉ ፈጸሙበት። 28 ለሞትም የሚያበቃ ምንም በደል ባላገኙበት ጊዜ እንዲገድለው ጲላጦስን ለመኑት። 29 ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ ከመስቀል አውርደው በመቃብር ቀበሩት። 30 እግዚአብሔር ግን ከሙታን ለይቶ አስነሣው። 31 ከተነሣም በኋላ ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም አብረውት ለወጡት ብዙ ቀን ተገለጠላቸው። እነርሱም በሕዝብ ዘንድ ምስክሮች ሆኑት። 32 “እኛም እግዚአብሔር ለአባቶቻችን ያናገረላቸውን ተስፋ እንነግራችኋለን። 33 በሁለተኛው መዝሙር፦ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ’ እንዳለ ኢየሱስን አስነሥቶ ተስፋውን ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአል። 34 መፍረስ መበስበስንም እንዳያይ እግዚአብሔር ከሙታን ለይቶ እንዳስነሣው እንዲህ አለ፦ ‘የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ። 35 በሌላ ስፍራም እንዲህ ይላል፦ ‘ጻድቅህን መፍረስ መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም።’ 36 ዳዊት ግን በዘመኑ ለእግዚአብሔር ትእዛዝ አገልግሎአል፤ እንደ አባቶቹ ሞተ፥ ተቀበረም፤ መፍረስ መበስበስንም አይቶአል። 37 ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መፍረስ መበስበስን አላየም። 38 እንግዲህ ወንድሞቻችን፥ በእርሱ ኀጢአታችሁ እንደሚሰረይላችሁ ተስፋ የሰጣችሁን ዕወቁ። 39 ከሁሉም ይልቅ በሙሴ ሕግ መጽደቅ የተሳናችሁ ናችሁ። በእርሱ ግን ያመነ ሁሉ ይጸድቃል። 40 እንግዲህ እንዲህ የሚለው የነቢያት ቃል እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ። 41 ‘እነሆ፥ እናንተ የምታቃልሉ፥ እዩ፤ ተደነቁም፤ ያለዚያ ግን ትጠፋላችሁ፤ ማንም ቢነግራችሁ የማታምኑትን ሥራ እኔ በዘመናችሁ እሠራለሁና።’ ” 42 ከምኵራብም ከወጡ በኋላ ይህን ነገር በሁለተኛው ሰንበት እንዲነግሩአቸው ማለዱአቸው። 43 ጉባኤውም በተፈታ ጊዜ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ከተመለሱት ከደጋጉ ሰዎች ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ጸጋ ይድኑ ዘንድ እያስረዱ ነገሯቸው። 44 በሁለተኛው ሰንበትም የከተማው ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ። 45 አይሁድም የተሰበሰበውን ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ ቀኑባቸው፤ እየተሳደቡም ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ተቃወሙ። 46 ጳውሎስና በርናባስም ደፍረው እንዲህ ብለው ተናገሩአቸው፥ “የእግዚአብሔርን ቃል ለእናንተ አስቀድሞ ልንነግራችሁ ይገባል፤ እንቢ ብትሉና ራሳችሁን ለዘለዓለም ሕይወት የተዘጋጀ ባታደርጉ ግን እነሆ፥ ወደ አሕዛብ እንመለሳለን። 47 እግዚአብሔር፦ እስከ ምድር ዳርቻ ላሉት ሁሉ መድኀኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ” ብሎ አዝዞናልና። 48 አሕዛብም ይህን ሰምተው ደስ አላቸው፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፤ ለዘለዓለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ። 49 የእግዚአብሔርም ቃል በሀገሩ ሁሉ ተዳረሰ። 50 አይሁድ ግን እግዚአብሔርን የሚፈሩ የከበሩ ሴቶችንና የከተማውን ሽማግሌዎች አነሳሡአቸው፤ በጳውሎስና በበርናባስ ላይም ስደትን አስነሡ፤ ከሀገራቸውም አባረሩአቸው። 51 እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ። 52 መንፈስ ቅዱስም በደቀ መዛሙርት ላይ ሞላ፤ ደስም አላቸው። |