ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እርሱም አለኝ፥ “መጀመሪያ በሰው ልጅ ነው፤ በኋላ ግን እኔ ራሴ ነኝ፤ ሰማይና ምድር፥ ሀገሮችም ሳይፈጠሩ፥ የዓለም መንገድም ሳይጸና፥ ነፋሳትም ሳይነፍሱ፤ 2 የነጐድጓድ ድምፅም ሳይሰማ፥ የመብረቅ ብልጭታም ሳይበራ፥ የገነት ምድር ሳይፈጠር፥ 3 የአበቦችም ውበት ሳይታይ፥ የመሬት መነዋወጥ ኀይልም ሳይጸና፥ የመላእክትም ሠራዊት ሳይቈጠሩ። 4 የሰማይም ምጥቀቱ ሳይታይ፥ የሰማያትም መስፈርት ሳይሰፈር፥ 5 የሚመጣው ዓለም ፍለጋ ሳይታወቅ፥ የኃጥኣን ጥላ ሳይወገድ፦ የጌታ ማኅተም ሕግን በሚጠብቁና ሃይማኖትን በሚያምኑ ላይ ሳይታተም፥ 6 ያንጊዜ እኔ ራሴ ይህን ዓለም እጐበኝ ዘንድ አሰብሁ፤ ሌላም አይደለም።” 7 መልሼም እንዲህ አልሁት፥ “የመጀመሪያው ዓለም ምልክቱ፥ ጊዜውስ ምንድን ነው? ፍጻሜውስ መቼ ነው? የሁለተኛውስ ዓለም መጀመሪያው መቼ ነው?” 8 እንዲህም አለኝ፥ “ከአብርሃም እስከ ይስሐቅ ነው፤ ያዕቆብና ዔሳው ከእርሱ ተወልደዋል፥ በተወለዱም ጊዜ ያዕቆብ የኤሳውን ተረከዝ ይዞ ተወለደ። 9 ኤሳው የዚህ ዘመን ፍጻሜ ምሳሌ ነው፤ ያዕቆብም የአዲሱ ዘመን መጀመሪያ ነው። 10 የሰው መጨረሻ አካሉ ተረከዙ ነውና፤ የሰውም መጀመሪያ አካሉ እጁ ነው። ነገር ግን ዕዝራ አትመራመር።” 11 እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “አቤቱ ጌታዬ፥ በዐይኖችህ ፊት ባለሟልነትንስ ካገኘሁ፥ 12 ባለፈው ሌሊት አስቀድሞ በከፊል የነገርኸኝን የዚህን ምልክት መጨረሻ ለባሪያህ ንገረው።” 13 እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “ተነሥተህ በእግርህ ቁም፤ ጩኸት የተመላበትንም ቃል እነግርሃለሁ። 14 አንተ በውስጡ የቆምህበት ቦታ ቢነዋወጥ በነገርሁህ ጊዜ አትደንግጥ፤ ስለ ነገር መጨረሻ ነውና። 15 ያንጊዜ የምድር መሠረቶች ነገርን ያስረዳሉ። 16 ነገሩ ስለ እነርሱ ነውና፥ ይንቀጠቀጣሉ፤ ይነዋወጣሉም፤ በመጨረሻቸው ያልፉ ዘንድ አላቸውና፥” 17 ከዚህም በኋላ ይህን በሰማሁ ጊዜ ተነሥቼ በእግሮች ቆምሁ፤ እነሆ፥ የሚናገረውንም ቃል ሰማሁ፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውኃ ድምፅ ነበር። 18 በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ይጐበኛቸው ዘንድ ልዑል በደረሰ ጊዜ እነሆ፥ ዘመን ይመጣል ይል ነበር። 19 ጽዮን በታነጸች ጊዜ ያመፁብኝን ዐመፃቸውን ያንጊዜ እመራመራቸው ዘንድ አለኝ። 20 ይመጣ ዘንድ ያለው ዓለም በታተመ ጊዜ የማደርገው ምልክት ይህ ነው፤ በሰማይ መጻሕፍት ይገለጣሉ፤ ሁሉም ያየኛል። 21 ዓመት የሆናቸው ሕፃናት ፈጽመው ይናገራሉ፤ የፀነሱ ሴቶችም የሦስት ወርና የአራት ወር ሕፃናትን ይወልዳሉ፤ ሕያዋንም ሆነው ይነሣሉ። 22 የማትታይ ምድርም ዘርዕ ተዘርቶባት ትታያለች፥ ውስጣቸው ሙሉ የነበሩ ቤቶችም ባዷቸውን ይገኛሉ። 23 ነጋሪት ይሰማል፤ የሰማውም ሁሉ ይደነግጣል። 24 በእነዚያም ወራት ወዳጆች ከወዳጆቻቸው ጋር እርስ በርሳቸው እንደ ጠላት ይዋጋሉ። ምድርም በውስጧ የሚኖሩባትን ታስደነግጣቸዋለች፤ የውኃው ምንጮችም ይገታሉ፤ እስከ ሦስት ሰዓትም ድረስ አይፈስሱም። 25 “ከዚህ ከነገርሁህ ሁሉ የቀረ ሰው ሁሉ የሚድን እርሱ ነው፤ ትድግናዬን የዘመኔንም ፍጻሜ የሚያይ እርሱ ነው። 26 ያንጊዜም ያረጉና ከተወለዱ ጅምሮ ሞትን ያልቀመሱ እነዚያን ሰዎች ያዩአቸዋል፤ በዓለም የሚኖሩ ሰዎችም ልቡና ይለወጣል፤ ሌላ ልቡናም ይሰጣቸዋል። 27 ክፋት ትደመሰሳለችና፥ ተንኰልም ትጠፋለችና። 28 ሃይማኖት ትለመልማለች፤ ሞት ድል ይነሣል፤ ያለ ፍሬ ለብዙ ዘመን የነበረች ጽድቅ ትገለጣለች።” 29 በተናገረኝም ጊዜ እኔ የቆምሁበት ስፍራ ጥቂት ጥቂት እያለ ይነዋወጥ ነበር። 30 እርሱም አለኝ፥ “ባለፈችው ሌሊት እንደ ነገርሁህ ይህን ምልክት እነግርህ ዘንድ መጣሁ። 31 ዳግመኛ ሰባት ቀን ብትጾምና ብትጸልይ ከዚህ የሚበልጥ ዳግመኛ እነግርሃለሁ። 32 ቃልህ በልዑል ዘንድ መሰማትን ተሰምትዋልና። ከሕፃንነትህም ጀምሮ ያለው የጽድቅህ ኀይል ተገልጧልና። 33 ስለዚህም ይህን ነገር እነግርህ ዘንድ ልዑል ላከኝ። 34 እንዲህም አለኝ፦ እመን፤ አትፍራ፤ በኋላ ዘመን እንዳትጠራጠር ስለ ቀደመውም ክፉ አሳብህ አትቸኩል።” ሦስተኛው ራእይ 35 ከዚህም በኋላ የነገረኝን ሦስቱን ሱባዔያት እጨርስ ዘንድ ዳግመኛ ሰባት ቀን እያለቀስሁ ጾምሁ። 36 በዚያች ሌሊት ልቤ ታወከችብኝ፤ በልዑልም ፊት እናገር ጀመርሁ። 37 ሰውነቴ ፈጽማ ትናደዳለችና፥ ልቡናዬም ትናወጣለችና። 38 እንዲህም አልሁ፥ “አቤቱ ጌታዬ፥ በመጀመሪያው መፍጠርህ በመጀመሪያዪቱ ቀን ሰማይና ምድር ይፈጠር አልህ፤ እንዲሁም ተፈጠረ፤ ቃልህም ፍጥረትን ይፈጥር ነበር። 39 መንፈስም ይሰፍፍ ነበር። ጨለማም ሞልቶ ነበር፥ ፀጥ ብሎም ነበር። ድምፅም አልነበረም፤ የሰው ልጅ ድምፅ ገና አልነበረምና። 40 ያንጊዜም ብርሃን ከአዳራሽህ እንዲገኝ ፍጥረትህም እንዲገለጥ አዘዝህ። 41 “ዳግመኛም በሁለተኛው ቀን በሰማያት ያለ ነፋስን ፈጠርህ፤ እኩሌታውም ወደ ላይ ይወጣ ዘንድ፥ እኩሌታውም በታች ይኖር ዘንድ በውኃው መካከል እንዲለይ አዘዝኸው። 42 ዳግመኛም በሦስተኛው ቀን ውኃውን ከምድር በሰባተኛው እጅ ላይ እንዲሰበሰብ አዘዝኸው። የምድር ስድስቱ እጅም በውስጣቸው ያርሱ ዘንድ፥ ዘርም ይዘሩ ዘንድ፥ በፊትህም ይኖሩ ዘንድ ደረቅ ሆኖ ይቅር አልህ። 43 ቃልህም በወጣ ጊዜ ፍጥረት ይፈጠር ነበር። 44 ያንጊዜም ቍጥር የሌለው ብዙ ፍሬ በቀለ፤ የሁሉም ጣዕሙ፥ ያበባውም መልክ ልዩ ልዩ ነበር፤ የእንጨቱም ዓይነት ልዩ ልዩ ነበር፤ መዓዛውም ልዩ ልዩ ነበር። 45 “ባራተኛይቱም ቀን ያበሩ ዘንድ የጨረቃና የፀሐይ ብርሃን፥ የከዋክብትም ሥርዐት ይፈጠር ዘንድ አዘዝህ። 46 ይፈጠር ዘንድ ላለው ሰውም ያገለግሉ ዘንድ አዘዝሃቸው። 47 “ባምስተኛውም ቀን የናጌብ ውኃ ያለበትን ያን ሰባተኛውን እጅ ሕይወት ያላቸውን ወፎችንና ዓሣዎችን ያስገኝ ዘንድ አዘዝኸው። 48 ስለዚህ ትውልድ ሁሉ ጌትነትህን ይናገሩ ዘንድ የማይናገርና ደመ ነፍስ የሌለው ያ ውኃ ሕይወት ያለውን አስገኘ። 49 ያንጊዜም የፈጠርሃቸውን ሁለቱን እንስሳት ጠበቅህ፤ ያንዱን ስሙን ብሔሞት አልኸው፤ የሁለተኛውንም ስሙን ሌዋታን አልኸው። 50 በየራሳቸውም ለየሃቸው፤ የናጌብ ውኃ ያለበት ያ ሰባተኛው እጅ ሊወስናቸው አይችልምና፥ 51 አራቱ ተራሮች ባሉበት በዚያ እርሱ በውስጡ ይኖር ዘንድ ለብሔሞት ከስድስቱ እጅ አንዱን እጅ የብስን ሰጠኸው። 52 “ለሌዋታንም የባሕሩን ሰባተኛ እጅ ሰጠኸው፤ ለምትወዳቸው ምግብ ይሆኑ ዘንድም ጠበቅሃቸው። 53 በስድስተኛዪቱም ቀን በፊትህ እንስሳን፥ የሰማይ ወፎችንና የዱር አውሬዎችን ታስገኝ ዘንድ ምድርን አዘዝሃት። 54 በዚህም ሁሉ ላይ አዳምን ገዥ አድርገህ ሾምኸው፤ አስቀድመህ በፈጠርኸው ፍጥረት ላይም ገዥ ሆነ። በእርሱም ምክንያት የመረጥኸን እኛ ወገኖችህ ከእርሱ ተገኘን። 55 “አቤቱ፥ ይህን ሁሉ በፊትህ ተናገርሁ፤ ይህን ዓለም ሰለ እናንተ ፈጠርሁት ብለሃልና። 56 ከአዳም የተወለዱ ሌሎች አሕዛብ ግን እንደ ኢምንት ናቸው፤ እንደ ምራቅም ይመስላሉ፤ እንደ አፍሻት ጠብታም ናቸው፤ ደስታቸውም እንደ ኢምንት ነው። 57 አሁንም እነሆ እንደ ኢምንት ናቸው ያልሃቸው እነዚያ አሕዛብ እነሆ በእኛ ላይ ሠለጠኑ፤ ረገጡንም። 58 የምወደው የበኸር አንድያ ልጄ ያልኸን እኛ ወገኖችህ ግን በአሕዛብ እጅ ገባን። 59 ነገር ግን ዓለምን ስለ እኛ ከፈጠርኸው ዓለማችንን ለምን አንወርስም? ይህስ እስከ መቼ ድረስ ነው?” |