ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤
አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት አጥብቀው ይሻሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል።
እስኪ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?
በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን።
ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤
ተራሮች ቢናወጡ፣ ኰረብቶች ከስፍራቸው ቢወገዱ እንኳ፣ ለአንቺ ያለኝ ጽኑ ፍቅር አይናወጥም፤ የገባሁትም የሰላም ቃል ኪዳን አይፈርስም” ይላል መሓሪሽ እግዚአብሔር።
የሰበሰቡትን በጎሞር በሰፈሩ ጊዜ፣ ብዙ የሰበሰበ አላተረፈም፤ ጥቂትም የሰበሰበ አልጐደለበትም፤ እያንዳንዱ የሰበሰበው የሚያስፈልገውን ያህል ሆነ።
ከዚህም የተነሣ አብርሃም የዚያን ስፍራ ስም፣ “እግዚአብሔር ያዘጋጃል” ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ፣ “በእግዚአብሔር ተራራ ላይ ይዘጋጃል” ይባላል።
ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ባሮቼ ይበላሉ፤ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ ባሮቼ ይጠጣሉ፤ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ ባሮቼ ደስ ይላቸዋል፤ እናንተ ግን ታፍራላችሁ።
እርሱ ግን፣ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” አለኝ። ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ አንተን ከልብ እሻለሁ፤ ውሃ በሌለበት፣ በደረቅና በተራቈተ ምድር፣ ነፍሴ አንተን ተጠማች፤ ሥጋዬም አንተን ናፈቀች።
በምድርም ለዘራኸው ዘር ዝናብን ይሰጥሃል፤ ከመሬትም የሚገኘው ፍሬ ምርጥና የተትረፈረፈ ይሆናል። በዚያ ቀን ከብቶችህ በትልቅ ሜዳ ላይ ይሰማራሉ።
እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እምነታችሁ በማነሱ ምክንያት ነው፤ እላችኋለሁ፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ተራራ፣ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም፤ [
በስምህ የምጠራህ የእስራኤል አምላክ፣ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቅ ዘንድ፣ በተሰወረ ስፍራ የተከማቸውን ሀብት፣ በጨለማም ያለውን ንብረት እሰጥሃለሁ።
አምላክህ እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት ስለሚባርክህ፣ አንተ ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከማንም አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብን ትገዛለህ እንጂ ማንም አንተን አይገዛህም።
እነሆ፤ የእግዚአብሔር ዐይኖች በሚፈሩት ላይ ናቸው፤ ምሕረቱንም በሚጠባበቁት ላይ አትኵረዋል።
በዚህም ነፍሳቸውን ከሞት ያድናል፤ በራብ ዘመንም በሕይወት ያኖራቸዋል።
በአንድ ሳንቲም ከሚሸጡት ሁለት ድንቢጦች አንዲቷ እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ ምድር ላይ አትወድቅም።
ፊልጶስና በርተሎሜዎስ፣ ቶማስና ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ታዴዎስ የተባለው ልብድዮስ፣
የራስ ጠጕራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር የተቈጠረ ነው።
ስለዚህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች የበለጠ ዋጋ አላችሁ።
ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው በእያንዳንዱ ቃል እንጂ፣ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ሊያስተምርህ አስራበህ፤ አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቁትን መና መገበህ፤
እግዚአብሔር አምላክ ፀሓይና ጋሻ ነውና፤ እግዚአብሔር ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ያለ ነቀፋ የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም።
ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸው ዘንድ፣ እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ።
በሰጠሃቸውም ጊዜ፣ አንድ ላይ ያከማቻሉ፤ እጅህንም ስትዘረጋ፣ በመልካም ነገር ይጠግባሉ።
እግዚአብሔር ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ፀሓይ ባቃጠለው ምድር ፍላጎትህን ያሟላል፤ ዐጥንትህን ያበረታል፤ በውሃ እንደ ረካ የአትክልት ቦታ፣ እንደማይቋርጥም ምንጭ ትሆናለህ።
“ነገር ግን በእግዚአብሔር የሚታመን፣ መታመኛውም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።
በውሃ ዳር እንደ ተተከለ፣ ሥሩንም ወደ ወንዝ እንደ ሰደደ ዛፍ ነው፣ ሙቀት ሲመጣ አይፈራም፤ ቅጠሉም ዘወትር እንደ ለመለመ ነው፤ በድርቅ ዘመን አይሠጋም፤ ፍሬ ማፍራቱንም አያቋርጥም።”
የሁሉ ዐይን አንተን በተስፋ ይጠብቃል፤ አንተም ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸዋለህ።
አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታረካለህ።
ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ከሰማይ እንጀራ አዘንብላችኋለሁ። ሕዝቡም በየቀኑ እየወጡ ለዕለት የሚበቃቸውን ይሰብስቡ፤ በዚህም ትእዛዞቼን ይጠብቁ እንደ ሆነ እፈትናቸዋለሁ።
እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መልካም ስጦታን እንዴት አብልጦ አይሰጥ?
“እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ኑ፤ እናንተ ገንዘብ የሌላችሁ፣ ወደ ውሆች ኑ፤ ኑና ግዙ፤ ብሉም! ኑና ያለ ገንዘብ፣ ያለ ዋጋ፣ የወይን ጠጅና ወተት ግዙ።
ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ ማከማቻ ወይም ጐተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ይመግባቸዋል። እናንተማ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን?
እርሷም ሄዳ ይህንኑ ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው። እርሱም፣ “ሄደሽ ዘይቱን በመሸጥ ዕዳሽን ክፈይ፤ የተረፈውም ለአንቺና ለልጆችሽ መተዳደሪያ ይሁን” አላት።
ከዚያም ኢየሱስ፣ “ያለ ኰረጆ፣ ያለ ከረጢትና ያለ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ምንም አልጐደለብንም” አሉ።
በዚህ ዓለም ባለጠጎች የሆኑት እንዳይታበዩ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር እንጂ አስተማማኝነት በሌለው በሀብት ላይ ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው።
በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጕድለት ያሟላል፤ የእነርሱም ደግሞ በተራው የእናንተን ጕድለት ያሟላል፤ በዚህም ያላችሁን እኩል ትካፈላላችሁ።
እርሱ ግን ከላይ ደመናትን አዘዘ፤ የሰማይንም ደጆች ከፈተ፤
ይበሉም ዘንድ መና አዘነበላቸው፤ የሰማይንም መብል ሰጣቸው።
ሰዎች የኀያላንን እንጀራ በሉ፤ ጠግበው እስከሚተርፍ ድረስ ምግብ ላከላቸው።
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እግዚአብሔር ለምድሪቱ ዝናብ እስከሚሰጥበት ዕለት ድረስ፤ ከማድጋው ዱቄት አይጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አያልቅም።’ ”
እግዚአብሔር ለምድርህ በወቅቱ ዝናብን ለመስጠትና የእጅህን ሥራ ሁሉ ለመባረክ፣ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ አንተም ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከአንዳቸውም አትበደርም።