ምክንያቱም የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ።
ምንም የማይጐድላችሁ ፍጹማንና ምሉኣን እንድትሆኑ ትዕግሥት ሥራውን ይፈጽም።
ራእዩ የተወሰነለትን ጊዜ ይጠብቃልና፤ ስለ መጨረሻውም ይናገራል፤ እርሱም አይዋሽም፤ የሚዘገይ ቢመስልም ጠብቀው፤ በርግጥ ይመጣል፤ ከቶም አይዘገይም።
እግዚአብሔር ግን ምሕረት ሊያደርግላችሁ ይታገሣል፤ ርኅራኄም ሊያሳያችሁ ይነሣል። እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነውና፣ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁት ብፁዓን ናቸው!
በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋራ ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቁ።
ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።
በዚህ ብቻ ሳይሆን በመከራችንም ሐሤት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን።
ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ታገሡ። ገበሬ መሬቱ መልካምን ፍሬ እስከሚሰጥ ድረስ እንዴት እንደሚታገሥ፣ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እንዴት እንደሚጠባበቅ አስተውሉ።
እናንተም እንዲሁ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ ምክንያቱም የጌታ መምጫ ተቃርቧል።
ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣ “ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም” ብሏል።
ስለዚህ በሙሉ ልብ፣ “ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንላለን።
በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው።
ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጣችሁ፣ የሰላም ሐሳብ እንጂ ለክፉ አይደለም።
ነገሥታት አሳዳጊ አባቶችሽ፣ እቴጌዎቻቸው ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤ በግንባራቸው ተደፍተው ይሰግዱልሻል፤ የእግርሽን ትቢያ ይልሳሉ፤ አንቺም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፤ እኔን ተስፋ የሚያደርጉም አያፍሩም።”
የእስራኤል ቅዱስ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ትበረታላችሁ፤ እናንተ ግን ይህን አላደረጋችሁም፤
የባሪያዎች ዐይን ወደ ጌታቸው እጅ፣ የባሪያዪቱም ዐይን ወደ እመቤቷ እጅ እንደሚመለከት፣ ምሕረት እስከሚያደርግልን ድረስ፣ የእኛም ዐይኖች ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ይመለከታሉ።
በእግዚአብሔር ታመን፤ መልካምንም አድርግ፤ በምድሪቱ ተቀመጥ፤ ዘና ብለህ ተሰማራ።
የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል፤ አንደበቱም ፍትሓዊ ነገር ያወራል።
የአምላኩ ሕግ በልቡ አለ፤ አካሄዱም አይወላገድም።
ክፉዎች ጻድቁን ይከታተሉታል፤ ሊገድሉትም ይሻሉ።
እግዚአብሔር ግን በእጃቸው አይጥለውም፤ ፍርድ ፊት ሲቀርብም አሳልፎ አይሰጠውም።
እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፤ መንገዱንም ጠብቅ፤ ምድሪቱን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ክፉዎችም ሲጠፉ ታያለህ።
ክፉና ጨካኙን ሰው፣ እንደ ሊባኖስ ዝግባ ለምልሞ አየሁት፤
ዳግመኛ በዚያ ሳልፍ፣ እነሆ፣ በቦታው አልነበረም፤ ብፈልገውም አልተገኘም።
ንጹሓንን ልብ በል፤ ቅኑንም አስተውል፤ የሰላም ሰው ተስፋ አለውና።
ኀጢአተኞች ግን በአንድነት ይጠፋሉ፤ የክፉዎችም ዘር ይወገዳል።
የጻድቃን ድነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ በመከራ ጊዜም መጠጊያቸው እርሱ ነው።
በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።
ይህን የምለው ስለ ቸገረኝ አይደለም፤ ምክንያቱም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ያለኝ ይበቃኛል ማለትን፣
ማጣትን ዐውቀዋለሁ፤ ማግኘትንም ዐውቀዋለሁ። ብጠግብም ሆነ ብራብ፣ ባገኝም ሆነ ባጣ፣ በማንኛውም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተምሬአለሁ።
ደግሞም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሠኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት።
“እኔ የወይን ተክል ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ማንም በእኔ ቢኖር እኔም በርሱ ብኖር፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና።
እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ።
አንተ አዳኜ፣ አምላኬም ነህና፣ በእውነትህ ምራኝ፤ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሙሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።
ስለ እግዚአብሔር ሲል የግፍ መከራን የሚቀበል ሰው ምስጋናን ያገኛል።
በድነታችሁ እንድታድጉ፣ አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ፤
ክፉ ሥራ ሠርታችሁ ብትቀጡና ብትታገሡ ምን ምስጋና ይኖራችኋል? ነገር ግን መልካም ሥራ ሠርታችሁ መከራ ብትቀበሉና ብትታገሡ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ያስገኝላችኋል።
በዚያ ቀን እንዲህ ይባላል፤ “እነሆ፤ አምላካችን ይህ ነው፤ በርሱ ታመንን፤ እርሱም አዳነን፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ በርሱ ታመንን፤ በማዳኑም ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ።”
እንግዲህ እነዚህን የመሳሰሉ ብዙ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ ሸክም የሚሆንብንን ሁሉ፣ በቀላሉም ተብትቦ የሚይዘንን ኀጢአት አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንሩጥ።
አንዳንድ ሰዎች የዘገየ እንደሚመስላቸው ጌታ የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ፣ ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ ስለ እናንተ ይታገሣል።
በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።
ስለዚህ ተስፋ አንቈርጥም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየጠፋ ቢሄድም እንኳ፣ ውስጣዊው ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፤
ምክንያቱም ቀላልና ጊዜያዊ የሆነው መከራችን ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል።
ስለዚህ ዐይናችን የሚያተኵረው በሚታየው ነገር ላይ ሳይሆን በማይታየው ላይ ነው፤ የሚታየው ጊዜያዊ ነውና፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለዚህ እስከምፈርድበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ፤ አሕዛብን ላከማች፣ መንግሥታትን ልሰበስብ፣ መዓቴንና ጽኑ ቍጣዬን በላያቸው ላፈስስ ወስኛለሁ። በቅናቴ ቍጣ እሳት፣ መላዋ ምድር ትቃጠላለችና።