መክብብ 7 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምጥበብ 1 መልካም ስም ከመልካም ሽቱ ይበልጣል፤ ከልደትም ቀን የሞት ቀን ይሻላል። 2 ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ፣ ወደ ሐዘን ቤት መሄድ ይሻላል፤ ሞት የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፤ ሕያው የሆነም ይህን ልብ ማለት ይገባዋል። 3 ሐዘን ከሣቅ ይሻላል፤ ያዘነ ፊት ለልብ መልካም ነውና። 4 የጠቢባን ልብ በሐዘን ቤት ነው፤ የሞኞች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው። 5 የሞኞችን መዝሙር ከመስማት፣ የጠቢባንን ሰዎች ተግሣጽ መስማት ይሻላል። 6 የሞኞች ሣቅ፣ ከድስት ሥር እንደሚንጣጣ የእሾኽ ማገዶ ነው፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 7 ግፍ ጠቢብን ሞኝ ያደርጋል፤ ጕቦም ልብን ያበላሻል። 8 የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል፤ ትዕግሥተኛም ከትዕቢተኛ ይሻላል። 9 የሞኞች ቍጣ በዕቅፋቸው ውስጥ ስለ ሆነ፣ በመንፈስህ ለቍጣ አትቸኵል። 10 አንተም፣ “ከእነዚህ ቀናት የቀድሞዎቹ ለምን ተሻሉ?” አትበል፤ እንዲህ ያሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ጠቢብነት አይደለምና። 11 ጥበብ እንደ ርስት መልካም ነገር ነው፤ ጠቃሚነቱም ፀሓይን ለሚያዩ ሰዎች ነው። 12 ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ጥበብም ጥላ ከለላ ነው፤ የዕውቀት ብልጫዋ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው። 13 አምላክ ያደረገውን ተመልከት፤ እርሱ ያጣመመውን፣ ማን ሊያቃናው ይችላል? 14 ጊዜው መልካም ሲሆን፣ ደስ ይበልህ፤ ጊዜው ክፉ ሲሆን ግን ይህን ዐስብ፤ አምላክ አንዱን እንዳደረገ፣ ሌላውንም አድርጓል፤ ስለዚህ ሰው ስለ ወደ ፊት ሁኔታው፣ ምንም ሊያውቅ አይችልም። 15 በዚህ ከንቱ በሆነው ሕይወቴ እነዚህን ሁለቱን ነገሮች አይቻለሁ፤ ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ፣ ኀጥእም በክፋቱ ዕድሜው ሲረዝም። 16 እጅግ ጻድቅ፣ እጅግም ጠቢብ አትሁን፤ ራስህን ለምን ታጠፋለህ? 17 እጅግ ክፉ አትሁን፤ ሞኝም አትሁን፤ ለምንስ ያለ ቀንህ ትሞታለህ? 18 አንዱን ይዞ ሌላውንም አለመልቀቅ መልካም ነው፤ አምላክን የሚፈራ ሰው ጽንፈኛነትን ያስወግዳል። 19 በአንድ ከተማ ካሉ ዐሥር ገዦች ይልቅ፣ ጥበብ ጠቢቡን ሰው ኀያል ታደርገዋለች። 20 ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኀጢአት የማይሠራ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም። 21 የሚነገረውን ቃል ሁሉ ለማድመጥ አትሞክር፤ አለዚያ አገልጋይህ ሲረግምህ ትሰማ ይሆናል፤ 22 ብዙ ጊዜ አንተ ራስህ፣ ሌሎችን እንደ ረገምህ ልብህ ያውቃልና። 23 እኔም ይህን ሁሉ በጥበብ ፈትኜ፣ “ጠቢብ ለመሆን ቈርጫለሁ” አልሁ፤ ይህ ግን ከእኔ የራቀ ነበር። 24 ጥበብ ምንም ይሁን ምን፣ እጅግ ጥልቅና ሩቅ ነው፤ ማንስ ሊደርስበት ይችላል? 25 ስለዚህ ጥበብንና የነገሮችን አሠራር ለመመርመርና ለማጥናት፣ የክፋትን መጥፎነት፣ የሞኝነትንም እብደት ለማስተዋል፣ አእምሮዬን መለስሁ። 26 ልቧ ወጥመድና አሽክላ፣ እጆቿም እግር ብረት የሆኑ፣ ከሞት የከፋችዋን ሴት አገኘሁ፤ አምላክን ደስ የሚያሰኝ ከእጇ ያመልጣል፤ ኀጢአተኛውን ግን አጥምዳ ትይዘዋለች። 27 ሰባኪው እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ መርምሬ ያገኘሁት ነገር ይህ ነው፤ “የነገሮችን ብልኀት መርምሮ ለማግኘት፣ አንዱን በአንዱ ላይ በመጨመር፣ 28 ገና በመመርመር ላይ ሳለሁ፣ ግን ያላገኘሁት፣ ከሺሕ ወንዶች መካከል አንድ ቅን ሰው አገኘሁ፣ በእነዚያ ሁሉ መካከል ግን አንዲት ቅን ሴት አላገኘሁም። 29 ይህን አንድ ነገር ብቻ አገኘሁ፤ አምላክ ሰውን ቅን አድርጎ መሥራቱን፣ ሰዎች ግን ውስብስብ ዘዴ ቀየሱ።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.