እንዲሁም የመለየት ጥበብን ብትማጠን፣ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ማስተዋልን ብትጣራ፣
እርሷንም እንደ ብር ብትፈልጋት፣ እንደ ተሸሸገ ሀብት አጥብቀህ ብትሻት፣
በዚያ ጊዜ ፈሪሀ እግዚአብሔርን ትረዳለህ፤ አምላክንም ማወቅ ታገኛለህ።
የምንጸልየውም ለጌታ እንደሚገባ እንድትኖሩና በሁሉም ደስ እንድታሰኙት ነው፤ ይኸውም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ እግዚአብሔርን በማወቅ እያደጋችሁ፣
እግዚአብሔርን እንወቀው፤ የበለጠ እናውቀውም ዘንድ አጥብቀን እንከተለው፤ እንደ ንጋት ብርሃን፣ በርግጥ ይገለጣል፤ ምድርን እንደሚያረሰርስ የበልግ ዝናብ፣ እንደ ክረምትም ዝናብ ወደ እኛ ይመጣል።”
የክብር አባት የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ይበልጥ እንድታውቁት፣ የጥበብና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ ያለ ማቋረጥ እለምናለሁ።
እንዲሁም በርሱ የተጠራችሁለት ተስፋ፣ ይህም በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩ
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጥበበኛ በጥበቡ አይታበይ፤ ኀያልም በኀይሉ አይመካ፤ ሀብታምም በሀብቱ አይኵራራ፤
የሚመካ ግን፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በማወቁና፣ በምድር ላይ ምሕረትን፣ ፍትሕንና ጽድቅን የማደርግ መሆኔን በመረዳቱ፣ በዚህ ይመካ፤ እኔ በእነዚህ ነገሮች፣ እደሰታለሁና፤” ይላል እግዚአብሔር።
የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣ፣ እውነተኛ የሆነውን እርሱን እንድናውቅ ማስተዋልን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እኛም እውነተኛ በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አለን። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።
ይህም የሚሆነው፣ ሁላችንም የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኘው አንድነት በመምጣትና ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እስከምንደርስ ነው።
ደግሞም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሠኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት።
መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ።
አንተ አዳኜ፣ አምላኬም ነህና፣ በእውነትህ ምራኝ፤ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሙሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።
ኢየሱስም በርሱ ያመኑትን አይሁድ እንዲህ አላቸው፤ “በትምህርቴ ብትጸኑ እናንተ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤
እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነጻ ያወጣችኋል።”
ደግሞም ልባቸው እንዲጽናናና በፍቅር እንዲተሳሰሩ፣ ፍጹም የሆነውን የመረዳት ብልጽግና አግኝተው የእግዚአብሔር ምስጢር የሆነውን ክርስቶስን እንዲያውቁ እተጋለሁ፤
ለዚህ ዓለም መርሕ ከክርስቶስ ጋራ ከሞታችሁ፣ ታዲያ በዚህ ዓለም እንደሚኖር ለምን ትገዙላቸዋላችሁ?
“አትያዝ! አትቅመስ! አትንካ!” እንደሚሉት ዐይነት፣
እነዚህ ሁሉ በሰው ትእዛዝና ትምህርት ላይ የተመሠረቱ ስለ ሆኑ በተግባር ላይ ሲውሉ ጠፊ ናቸው።
እነዚህ ነገሮች በገዛ ራስ ላይ ከሚፈጥሩት የአምልኮ ስሜት፣ ከዐጕል ትሕትናና ሰውነትን ከመጨቈን አንጻር በርግጥ ጥበብ ያለባቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን የሥጋን ልቅነት ለመቈጣጠር አንዳች ፋይዳ የላቸውም።
የተሰወረ የጥበብና የዕውቀት ሀብት ሁሉ የሚገኘው በርሱ ዘንድ ነውና።
እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል።
በውስጡ ካለው ከራሱ መንፈስ በቀር ከሰው መካከል የአንድን ሰው ሐሳብ የሚያውቅ ማን አለ? እንደዚሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር፣ የእግዚአብሔርን ሐሳብ የሚያውቅ ማንም የለም።
ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ፣ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንምና፤ ይህም እግዚአብሔር በነጻ የሰጠንን እናውቅ ዘንድ ነው።
ይኸውም በእምነት ክርስቶስ በልባችሁ እንዲያድር ነው። ደግሞም ሥር ሰድዳችሁ፣ በፍቅር ታንጻችሁ፣
የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደ ሆነ፣ ከቅዱሳን ሁሉ ጋራ የመገንዘብ ኀይልን እንድታገኙ ነው።
እስከ እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ልክ ደርሳችሁ እንድትሞሉ፣ ከመታወቅ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ታውቁም ዘንድ ነው።
ከዚህ የተነሣ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር የፈቃዱን ዕውቀት በመንፈሳዊ ጥበብና መረዳት ሁሉ ይሞላችሁ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለይና መለመን አላቋረጥንም፤
እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት።
ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው። ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤ ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።
እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው።
እናንተ ግን ከርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በውስጣችሁ ይኖራልና ማንም እንዲያስተምራችሁ አያስፈልግም፤ ነገር ግን የርሱ ቅባት ስለ ሁሉም ነገር፣ እውነተኛ የሆነውን እና ሐሰት ያልሆነው እናንተን እንደሚያስተምር፣ እናንተንም እንዳስተማራችሁ በርሱ ኑሩ።
የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል።
አታውቅምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው። አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም በማንም አይመረመርም።
ብፁዕ ነው፣ በክፉዎች ምክር የማይሄድ፣ በኀጢአተኞች መንገድ የማይቆም፣ በፌዘኞችም ወንበር የማይቀመጥ፤
ነገር ግን ደስ የሚሠኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል።
እርሱ የማይታየው አምላክ አምሳል ነው፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤
ሁሉ ነገር በርሱ ተፈጥሯል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በርሱና ለርሱ ተፈጥሯል።
እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በርሱ ነው።
ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ።
ከወርቅ ይልቅ የከበረ፣ እጅግ ከጠራ ወርቅም የተሻለ ነው፤ ከማር ይልቅ ይጣፍጣል፤ ከማር ወለላም ይበልጥ ይጥማል።
ደግሞም አገልጋይህ በርሱ ጥንቃቄ ያደርጋል፤ እርሱንም መጠበቅ ወሮታ አለው።
ስሕተቱን ማን ሊያስተውል ይችላል? ከተሰወረ በደል አንጻኝ።
ባሪያህን ከድፍረት ኀጢአት ጠብቅ፤ እንዳይሠለጥንብኝም ርዳኝ፤ ያን ጊዜ ያለ እንከን እሆናለሁ፤ ከታላቅ በደልም እነጻለሁ።
ዐለቴና አዳኜ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአፌ ቃልና የልቤ ሐሳብ፣ በፊትህ ያማረ ይሁን።
ቀን ለሌላው ቀን ይናገራል፤ ሌሊትም ለሌሊት ዕውቀትን ይገልጣል፤
በስምህ የምጠራህ የእስራኤል አምላክ፣ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቅ ዘንድ፣ በተሰወረ ስፍራ የተከማቸውን ሀብት፣ በጨለማም ያለውን ንብረት እሰጥሃለሁ።
ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤
ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።
“ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ፣ መንገዴ እንደ መንገዳችሁ አይደለምና” ይላል እግዚአብሔር።
“ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ፣ መንገዴ ከመንገዳችሁ፣ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እንዲሁ ከፍ ያለ ነው።
ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ፣ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል፤ ስለዚህ ሰዎች ማመካኛ የላቸውም።
በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ፤ እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ።
እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹም ልባቸውም ወደ እኔ ስለሚመለሱ፣ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
ሰውየውም መልሶ፣ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህና በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል” አለው።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ አንተን ከልብ እሻለሁ፤ ውሃ በሌለበት፣ በደረቅና በተራቈተ ምድር፣ ነፍሴ አንተን ተጠማች፤ ሥጋዬም አንተን ናፈቀች።
የጠቢባንን ቃል ልብ ብለህ ስማ፤ ልብህም ወደ ትምህርቴ ያዘንብል፤
በልብህ ስትጠብቃቸው፣ ሁሉም በከንፈሮችህ ላይ የተዘጋጁ ሲሆኑ ደስ ይላልና።
ስለዚህ መታመኛህ በእግዚአብሔር ላይ እንዲሆን፣ ዛሬ አንተን ራስህን አስተምርሃለሁ።
ለእነርሱም እግዚአብሔር የዚህ ምስጢር ክብር ባለጠግነት በአሕዛብ መካከል ምን ያህል እንደ ሆነ ለማሳወቅ መረጠ፤ እርሱም የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ውስጥ ያለው ክርስቶስ ነው።
በቀረውስ ወንድሞች ሆይ፤ እግዚአብሔርን ደስ ለማሠኘት እንዴት መኖር እንደሚገባችሁ አስተምረናችኋል፤ በርግጥም እንደዚያው እየኖራችሁ ነው። ስለ ሆነም በጌታ በኢየሱስ የምንለምናችሁና የምንመክራችሁ ከዚህ በበለጠ ሁኔታ በዚሁ እንድትገፉበት ነው።
የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል፤
“ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ በሩም ይከፈትላችኋል።
የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል።
ስለዚህ ስለ ክርስቶስ የተሰጠውን የመጀመሪያ ትምህርት ትተን ወደ ብስለት እንሂድ፤ ከሞተ ሥራ ንስሓ ስለ መግባትና በእግዚአብሔር ስለ ማመን እንደ ገና መሠረትን አንጣል፤
ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤
አንዳንድ ሰዎች የዘገየ እንደሚመስላቸው ጌታ የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ፣ ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ ስለ እናንተ ይታገሣል።
“እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ኑ፤ እናንተ ገንዘብ የሌላችሁ፣ ወደ ውሆች ኑ፤ ኑና ግዙ፤ ብሉም! ኑና ያለ ገንዘብ፣ ያለ ዋጋ፣ የወይን ጠጅና ወተት ግዙ።
ዝናምና በረዶ ከሰማይ ወርዶ፣ ምድርን በማራስ፣ እንድታበቅልና እንድታፈራ ለዘሪው ዘር፣ ለበላተኛም እንጀራ እንድትሰጥ ሳያደርግ፣ ወደ ላይ እንደማይመለስ ሁሉ፣
ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል።
በደስታ ትወጣላችሁ፤ በሰላምም ትሸኛላችሁ፤ ተራሮችና ኰረብቶች፣ በፊታችሁ በእልልታ ይዘምራሉ፤ የሜዳ ዛፎች ሁሉ፣ ያጨበጭባሉ።
በእሾኽ ፈንታ የጥድ ዛፍ፣ በኵርንችት ፈንታ ባርሰነት ይበቅላል። ይህም የእግዚአብሔር መታሰቢያ፣ ሊጠፋ የማይችል፣ የዘላለም ምልክት ይሆናል።”
ገንዘባችሁን እንጀራ ባልሆነ ነገር ላይ ለምን ታጠፋላችሁ? በማያጠግብስ ነገር ላይ ለምን ጕልበታችሁን ትጨርሳላችሁ? ስሙ፤ እኔን ስሙኝ፤ መልካም የሆነውንም ብሉ፤ ነፍሳችሁም በጥሩ ምግብ ትደሰታለች።
አሁን የምናየው በመስተዋት ውስጥ እንደሚታይ በድንግዝግዝ ነው፤ በዚያ ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን። አሁን የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያ ጊዜ እኔ ራሴ ሙሉ በሙሉ የታወቅሁትን ያህል ዐውቃለሁ።
ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ እኛም በብርሃን ብንመላለስ፣ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፤ የልጁም የኢየሱስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል።
በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በክርስቶስ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤
በፊቱ ቅዱስና እንከን አልባ እንድንሆን ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በርሱ መርጦናልና። በፍቅር፣
“እኔ የወይን ተክል ነኝ፤ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ማንም በእኔ ቢኖር እኔም በርሱ ብኖር፣ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና።
ሰማያትን የፈጠረ፣ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ያበጃት፣ የሠራት፣ የመሠረታት፣ የሰው መኖሪያ እንጂ፣ ባዶ እንድትሆን ያልፈጠራት፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።
እናንተ ግን ክርስቶስን ያወቃችሁት እንደዚህ ባለ መንገድ አይደለም፤
በርግጥ ስለ እርሱ ሰምታችኋል፤ በኢየሱስም እንዳለው እውነት በርሱ ተምራችኋል።
ቃሌም ስብከቴም የመንፈስን ኀይል በመግለጥ እንጂ፣ በሚያባብል የጥበብ ቃል አልነበረም፤
ይኸውም እምነታችሁ በእግዚአብሔር ኀይል እንጂ በሰው ጥበብ ላይ እንዳይመሠረት ነው።