እግዚአብሔርም፣ “እግዚአብሔር በዚያ ያልፋልና ወደ ተራራው ወጥተህ በእግዚአብሔር ፊት ቁም” አለው። ከዚያም ታላቅና ኀይለኛ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጣጠቀ፤ ዐለቶችንም በእግዚአብሔር ፊት ብትንትናቸውን አወጣ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም፤ ከነፋሱም ቀጥሎ የምድር መነዋወጥ ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በምድር መነዋወጡ ውስጥ አልነበረም።
ከምድር መነዋወጡም ቀጥሎ እሳት መጣ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም፤ ከእሳቱም ቀጥሎ ለስለስ ያለ ድምፅ ተሰማ።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ።
አንተ አዳኜ፣ አምላኬም ነህና፣ በእውነትህ ምራኝ፤ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሙሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።
የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል፤
ጆሯችሁን ከፍታችሁ ወደ እኔ ቅረቡ፤ ነፍሳችሁም እንድትኖር አድምጡኝ። ለዳዊት በገባሁት በጽኑ ፍቅሬ፣ ከእናንተም ጋራ የዘላለም ኪዳን አደርጋለሁ።
ልዑል እግዚአብሔር የተባ አንደበት ሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ደካሞችን ብርቱ ለማድረግ ምን ማለት እንዳለብኝ ዐውቃለሁ፤ በየማለዳው ያነቃኛል፤ በመማር ላይ እንዳለ ተማሪ ለመስማት ጆሮዬን ያነቃዋል።
ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በፍጹም ብትታዘዝና እኔ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙን ሁሉ በጥንቃቄ ብትከተል፣ አምላክህ እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ያደርግሃል።
ከዚያም የምድር አሕዛብ ሁሉ በእግዚአብሔር ስም መጠራትህን ያያሉ፤ ይፈሩሃልም።
እግዚአብሔርም ሊሰጥህ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር በማሕፀንህ ፍሬ፣ በእንስሳትህም ግልገል፣ በምድርህም ሰብል የተትረፈረፈ ብልጽግና ይሰጥሃል።
እግዚአብሔር ለምድርህ በወቅቱ ዝናብን ለመስጠትና የእጅህን ሥራ ሁሉ ለመባረክ፣ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ አንተም ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከአንዳቸውም አትበደርም።
እግዚአብሔርም ራስ እንጂ ጅራት አያደርግህም። ዛሬ የምሰጥህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በጥንቃቄ ብትጠብቅ፣ መቼውንም ቢሆን በላይ እንጂ ፈጽሞ በታች አትሆንም።
ሌሎችን አማልክት በመከተል እነርሱን በማገልገል ዛሬ ከምሰጥህ ትእዛዞች ቀኝም ግራም አትበል።
ነገር ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ባትታዘዝ በዛሬዋ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙንና ሥርዐቱን ሁሉ በጥንቃቄ ባትከተላቸው፣ እነዚህ ርግማኖች ሁሉ ይደርሱብሃል፤ ያጥለቀልቁሃልም፦
በከተማ ትረገማለህ፤ በዕርሻም ትረገማለህ።
እንቅብህና ቡሖ ዕቃህ የተረገሙ ይሆናሉ።
የማሕፀንህ ፍሬ፣ የዕርሻህ ሰብል፣ የመንጋህ ጥጆች፣ የበግና የፍየል ግልገሎችህ ይረገማሉ።
ስትገባ ትረገማለህ፤ ስትወጣም ትረገማለህ።
አምላክህን እግዚአብሔርን ብትታዘዝ፣ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ያንተ ይሆናሉ፤ አይለዩህምም።
እግዚአብሔርም መጥቶ በዚያ ቆመ፤ ቀደም ሲል እንዳደረገው ሁሉ “ሳሙኤል! ሳሙኤል!” ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም፣ “ባሪያህ ይሰማልና ተናገር” አለ።
ልጄ ሆይ፤ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በልብህ ብታኖር፣
ጥበብ ልብህ ውስጥ ትገባለችና፤ ዕውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለች፤
የመለየት ችሎታ ይጋርድሃል፤ ማስተዋልም ይጠብቅሃል።
ጥበብ ንግግራቸው ጠማማ ከሆነ ሰዎች፣ ከክፉዎችም መንገድ ታድንሃለች፤
እነዚህም በጨለማ መንገድ ለመሄድ፣ ቀናውን ጐዳና የሚተዉ ናቸው፤
ክፉ በመሥራት ደስ የሚላቸው፣ በክፋት ጐዳና ሐሤት የሚያደርጉ፣
መንገዳቸው ጠማማ፣ በአካሄዳቸው ጠመዝማዞች ናቸው።
ከአመንዝራ ሴትም ትጠብቅሃለች፤ በአንደበቷም ከምታታልል ባዕድ ታድንሃለች፤
ይህችም የልጅነት ባሏን የተወች፣ በአምላኳ ፊት የገባችውን ኪዳን ያቃለለች ናት።
ቤቷ ወደ ሞት ያደርሳል፤ መንገዷም ወደ መናፍስተ ሙታን ያመራል።
ወደ እርሷ የሚገባ ማንም አይመለስም፤ የሕይወትንም መንገድ አያገኝም።
ጆሮህን ወደ ጥበብ ብታቀና፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ብትመልስ፣
አንተም በደጋግ ሰዎች ጐዳና ትሄዳለህ፤ የጻድቃንንም መንገድ ይዘህ ትጓዛለህ።
ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ።
ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከርሷ ይነቀላሉ።
እንዲሁም የመለየት ጥበብን ብትማጠን፣ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ማስተዋልን ብትጣራ፣
እርሷንም እንደ ብር ብትፈልጋት፣ እንደ ተሸሸገ ሀብት አጥብቀህ ብትሻት፣
በዚያ ጊዜ ፈሪሀ እግዚአብሔርን ትረዳለህ፤ አምላክንም ማወቅ ታገኛለህ።
የክብር አባት የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ይበልጥ እንድታውቁት፣ የጥበብና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ ያለ ማቋረጥ እለምናለሁ።
እንዲሁም በርሱ የተጠራችሁለት ተስፋ፣ ይህም በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩ
የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል።
እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል። መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል።
በውስጡ ካለው ከራሱ መንፈስ በቀር ከሰው መካከል የአንድን ሰው ሐሳብ የሚያውቅ ማን አለ? እንደዚሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር፣ የእግዚአብሔርን ሐሳብ የሚያውቅ ማንም የለም።
ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤
ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።
“ብትወድዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ።
እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋራ ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤
እርሱም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም። እናንተ ግን፣ ዐብሯችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስለሚሆን ታውቁታላችሁ።
ሰው ባያስተውለውም፣ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ይናገራል፤
ሰዎች ዐልጋቸው ላይ ተኝተው ሳሉ፣ ከባድ እንቅልፍ ሲወድቅባቸው፣ በሕልም፣ በሌሊትም ራእይ ይናገራል።
እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ቀርባችሁ ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ።
እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፤ በፍጹም ልባችሁም ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ፤
ዕውሮችን በማያወቁት መንገድ እመራቸዋለሁ፤ ባልተለመደ ጐዳና እወስዳቸዋለሁ። ጨለማውን በፊታቸው ብርሃን አደርጋለሁ፤ ጐርባጣውን ስፍራ አስተካክላለሁ። ይህን አደርጋለሁ፤ አልተዋቸውም።
እርሱም አለ፤ “የአምላካችሁን እግዚአብሔር ድምፅ በጥንቃቄ ብትሰሙ፣ በፊቱም ትክክል የሆነውን ብትፈጽሙ፣ ትእዛዞቹን ልብ ብትሉና ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቁ፣ በግብጻውያን ላይ ያመጣሁባቸውን ማንኛውንም ዐይነት በሽታ በእናንተ ላይ አላመጣም፤ ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝና።”
ሙሴ እስራኤልን ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ እስራኤል ሆይ፤ በዛሬዋ ዕለት በጆሯችሁ የምነግራችሁን ሥርዐትና ሕግ ስሙ፤ አጥኗቸው፤ በጥንቃቄም ጠብቋቸው።
በስሜ የተጠራው ሕዝቤ ራሱን አዋርዶ ቢጸልይ፣ ፊቴን ቢፈልግና ከክፉ መንገዱ ቢመለስ፣ ከሰማይ እሰማዋለሁ፤ ኀጢአቱን ይቅር እላለሁ፤ ምድሩንም እፈውሳለሁ።
የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስንም መልሶ ያለመልማል፤ የእግዚአብሔር ሥርዐት የታመነ ነው፤ አላዋቂውን ጥበበኛ ያደርጋል።
የእግዚአብሔር ሕግጋት ትክክል ናቸው፤ ልብን ደስ ያሰኛሉ። የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፤ ዐይንን ያበራል።
ስለዚህ እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤
እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በርሱ ላይ ጣሉት።
ወደ እኔ የሚመጣ፣ ቃሌንም ሰምቶ የሚፈጽም ሁሉ ማንን እንደሚመስል ላሳያችሁ፤
ቤት ለመሥራት አጥልቆ የቈፈረና በዐለት ላይ መሠረቱን የመሠረተ ሰው ይመስላል፤ ጐርፍ በመጣ ጊዜ የውሃው ሙላት ያን ቤት ገፋው፤ በሚገባ ስለ ታነጸም ሊያነቃንቀው አልቻለም።
የተቤዠህ፣ የእስራኤል ቅዱስ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ።
ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።
ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ፣ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንምና፤ ይህም እግዚአብሔር በነጻ የሰጠንን እናውቅ ዘንድ ነው።
እኛ የምንናገረው ይህን ነው፤ ከሰው ጥበብ በተማርነው ቃል ሳይሆን፣ ከመንፈስ በተማርነው ቃል እንናገራለን፤ መንፈሳዊ እውነትንም የምንገልጸው በመንፈሳዊ ቃል ነው።
ልጄ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፤ በዘለፋውም አትመረር፤
አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የሚወድደውን ይገሥጻልና።
የእስራኤል ቅዱስ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ትበረታላችሁ፤ እናንተ ግን ይህን አላደረጋችሁም፤
በጥሩ መሬት ላይ የተዘራው ዘር ግን ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውለውን ሰው ይመስላል፤ በርግጥም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ።”
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ አንተን ከልብ እሻለሁ፤ ውሃ በሌለበት፣ በደረቅና በተራቈተ ምድር፣ ነፍሴ አንተን ተጠማች፤ ሥጋዬም አንተን ናፈቀች።
በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋራ ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቁ።
ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።
እግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት፤ እርሱም ዘንበል አለልኝ፤ ጩኸቴንም ሰማ።
ጽድቅህን በልቤ አልሸሸግሁም፤ ታማኝነትህንና ማዳንህን እናገራለሁ፤ ምሕረትህንና እውነትህን፣ ከታላቅ ጉባኤ አልደበቅሁም።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህን አትንፈገኝ፤ ቸርነትህና እውነትህ ዘወትር ይጠብቁኝ፤
ስፍር ቍጥር የሌለው ክፋት ከብቦኛልና፤ የኀጢአቴ ብዛት ስለ ያዘኝ ማየት ተስኖኛል፤ ከራሴ ጠጕር ይልቅ በዝቷል፤ ልቤም ከድቶኛል።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ታድነኝ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን።
ነፍሴን ለመንጠቅ የሚፈልጉ ይፈሩ፤ ይዋረዱም፤ ጕዳቴንም የሚሹ፣ ተዋርደው በመጡበት ይመለሱ።
በእኔ ላይ፣ “ዕሠይ! ዕሠይ!” የሚሉ፣ በራሳቸው ዕፍረት ይደንግጡ።
አንተን የሚፈልጉ ሁሉ ግን፣ ሐሤት ያድርጉ፤ በአንተም ደስ ይበላቸው፤ ዘወትር የአንተን ማዳን የሚወድዱ፣ “እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ይበል!” ይበሉ።
እኔ ግን ችግረኛና ድኻ ነኝ፤ ጌታ ግን ያስብልኛል። አንተ ረዳቴና ታዳጊዬም ነህና፤ አምላኬ ሆይ፤ አትዘግይ።
ከሚውጥ ጕድጓድ፣ ከሚያዘቅጥ ማጥ አወጣኝ፤ እግሮቼን በዐለት ላይ አቆመ፤ አካሄዴንም አጸና።
ልጄ ሆይ፤ የአባትህን ትእዛዝ አክብር፤ የእናትህንም ትምህርት አትተው።
ምን ጊዜም በልብህ አኑራቸው፤ በዐንገትህም ዙሪያ እሰራቸው።
በምትሄድበት ሁሉ ይመሩሃል፤ በምትተኛበት ጊዜ ይጠብቁሃል፤ በምትነቃበት ጊዜም ያነጋግሩሃል።
የእግዚአብሔር ድምፅ በውሆች ላይ ነው፤ የክብር አምላክ አንጐደጐደ፤ እግዚአብሔር በታላላቅ ውሆች ላይ አንጐደጐደ።
የእግዚአብሔር ድምፅ ኀያል ነው፤ የእግዚአብሔር ድምፅ ግርማዊ ነው።
ደግሞም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሠኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት።
እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት።
ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው። ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤ ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።
በእግዚአብሔር ዕውቀት ላይ በትዕቢት የሚነሣውን ክርክርና ከንቱ ሐሳብ ሁሉ እናፈርሳለን፤ አእምሮንም ሁሉ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን።
እናንተ ግን ከርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በውስጣችሁ ይኖራልና ማንም እንዲያስተምራችሁ አያስፈልግም፤ ነገር ግን የርሱ ቅባት ስለ ሁሉም ነገር፣ እውነተኛ የሆነውን እና ሐሰት ያልሆነው እናንተን እንደሚያስተምር፣ እናንተንም እንዳስተማራችሁ በርሱ ኑሩ።
አሁንም በፍጹም ብትታዘዙኝና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ከአሕዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ፤ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆንም፣
መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
የራሱ የሆኑትንም ሁሉ ካወጣ በኋላ ፊት ፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል።
ከዚያም ኢየሱስ፣ ቀደም ሲል ዮሐንስ ያጠምቅበት ወደ ነበረበት፣ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ተመለሰ፤ በዚያም ሰነበተ፤
ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጡ። እነርሱም፣ “ዮሐንስ አንድም ታምራዊ ምልክት አላደረገም፤ ነገር ግን ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ” አሉ።
በዚያም ስፍራ ብዙዎች በኢየሱስ አመኑ።
እንግዳ የሆነውን ግን ድምፁን ስለማያውቁ ከርሱ ይሸሻሉ እንጂ ፈጽሞ አይከተሉትም።”
በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ ማንኛውንም ነገር እንደ ፈቃዱ ብንለምን እርሱ ይሰማናል።
የምንለምነውን ሁሉ እንደሚሰማን ካወቅን፣ የለመንነውንም ነገር እንደ ተቀበልን እናውቃለን።
መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል፤
ጽድቅህን እንደ ብርሃን፣ ፍትሕህን እንደ ቀትር ፀሓይ ያበራዋል።
በእግዚአብሔር ፊት ጸጥ በል፤ በትዕግሥትም ተጠባበቀው፤ መንገዱ በተቃናለት፣ ክፋትንም በሚሸርብ ሰው ልብህ አይሸበር።
የጠቢባንን ቃል ልብ ብለህ ስማ፤ ልብህም ወደ ትምህርቴ ያዘንብል፤
በልብህ ስትጠብቃቸው፣ ሁሉም በከንፈሮችህ ላይ የተዘጋጁ ሲሆኑ ደስ ይላልና።
እግዚአብሔር ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ፀሓይ ባቃጠለው ምድር ፍላጎትህን ያሟላል፤ ዐጥንትህን ያበረታል፤ በውሃ እንደ ረካ የአትክልት ቦታ፣ እንደማይቋርጥም ምንጭ ትሆናለህ።
ብፁዕ ነው፣ በክፉዎች ምክር የማይሄድ፣ በኀጢአተኞች መንገድ የማይቆም፣ በፌዘኞችም ወንበር የማይቀመጥ፤
ነገር ግን ደስ የሚሠኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል።
“መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ እነርሱም ያውቁኛል፤
ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው ነው። ሕይወቴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ።
እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎችን የሚጠቅም ቃል እንጂ የማይረባ ቃል ከአፋችሁ አይውጣ።
በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።
ለቤዛ ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ አታሳዝኑ።
ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፣ እግዚአብሔር፣ በሚቃጠል ቍርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል።
እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአንደበቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣል።
እርሱ ለቅኖች ትክክለኛ ጥበብ ያከማቻል፤ ያለ ነቀፋ ለሚሄዱትም ጋሻ ይሆናቸዋል፤
“እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ።
ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤
“ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ።
ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”
የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
ከሦስት ቀንም በኋላ፣ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያደምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው በቤተ መቅደስ ውስጥ አገኙት፤
የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ይደነቁ ነበር።
ራሳችሁን እንደ ባሪያ አድርጋችሁ ስታቀርቡ፣ ለምትታዘዙት ለርሱ፣ ይኸውም ወደ ሞት ለሚወስደው ለኀጢአት ወይም ወደ ጽድቅ ለሚያደርሰው ለመታዘዝ ባሮች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን?
ከሰማይ የሆነችው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ በኋላም ሰላም ወዳድ፣ ታጋሽ፣ ዕሺ ባይ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬ የሞላባት፣ አድልዎና ግብዝነት የሌለባት ናት።
እግዚአብሔር ሆይ፤ የሥርዐትህን መንገድ አስተምረኝ፤ እኔም እስከ መጨረሻው እጠብቀዋለሁ።
ሕግህን እንድጠብቅ፣ በፍጹም ልቤም እንድታዘዘው፣ ማስተዋልን ስጠኝ።
እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ያግዘናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅም፤ መንፈስ ግን በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ይማልድልናል።
በልዑል መጠጊያ የሚኖር፣ በሁሉን ቻይ አምላክ ጥላ ሥር ያድራል።
ክፉ ነገር አያገኝህም፤ መቅሠፍትም ወደ ድንኳንህ አይገባም፤
በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ፣ እግርህም ከድንጋይ ጋራ እንዳይሰናከል፤
በእጆቻቸው ያነሡህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዝልሃል።
በአንበሳና በእፉኝት ላይ ትጫማለህ፤ ደቦሉን አንበሳና ዘንዶውን ትረግጣለህ።
“ወድዶኛልና እታደገዋለሁ፤ ስሜን ዐውቋልና እከልለዋለሁ።
ይጠራኛል፤ እመልስለታለሁ፤ በመከራው ጊዜ ከርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ፤ አከብረዋለሁ።
ረዥም ዕድሜን አጠግበዋለሁ፤ ማዳኔንም አሳየዋለሁ።”
እግዚአብሔርን፣ “መጠጊያዬ፣ ምሽጌ፣ የምታመንብህ አምላኬ” እለዋለሁ።
እኛም ሁላችን ባልተሸፈነ ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያንጸባረቅን፣ የርሱን መልክ እንድንመስል ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን፤ ይህም የሚሆነው መንፈስ ከሆነ ጌታ ነው።