ዕብራውያን 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምትኵረት የሚያሻው ጕዳይ 1 ስለዚህ ከሰማነው ነገር ስተን እንዳንወድቅ፣ ለሰማነው ነገር አብልጠን ልንጠነቀቅ ይገባናል። 2 ምክንያቱም በመላእክት በኩል የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነና ማንኛውም መተላለፍና አለመታዘዝ ተገቢውን ቅጣት ከተቀበለ፣ 3 እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ ድነት ቸል ብንል እንዴት ልናመልጥ እንችላለን? ይህ ድነት በመጀመሪያ በጌታ ተነገረ፤ ከርሱ የሰሙትም ለእኛ አረጋገጡልን። 4 እግዚአብሔርም በምልክት፣ በድንቅና በልዩ ልዩ ታምራት እንዲሁም እንደ ፈቃዱ በታደሉት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ስለዚሁ ነገር መስክሯል። ኢየሱስ ወንድሞቹን መሰለ 5 ይህን የምንናገርለትን መጪውን ዓለም ለመላእክት አላስገዛም። 6 ነገር ግን አንዱ በሌላ ስፍራ እንዲህ ብሎ መስክሯል፤ “በሐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጠነቀቅለትም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው? 7 ከመላእክት በጥቂት አሳነስኸው፤ ክብርንና ግርማን አጐናጸፍኸው፤ 8 ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት።” እግዚአብሔር ሁሉን ከበታቹ ሲያስገዛለት፣ ያላስገዛለት ምንም ነገር የለም፤ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ተገዝቶለት አናይም። 9 ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላእክት ጥቂት እንዲያንስ ተደርጎ የነበረው ኢየሱስ፣ የሞትን መከራ በመቀበሉ አሁን የክብርና የምስጋና ዘውድ ተጭኖለት እናየዋለን። 10 ሁሉ ነገር ለርሱና በርሱ የሚኖር እግዚአብሔር፣ ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ለማምጣት፣ የድነታቸውን መሥራች በመከራ ፍጹም ሊያደርገው የተገባ ነበር። 11 ሰዎችን የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሰዎች ከአንድ ቤተ ሰብ ናቸው፤ ስለዚህ ኢየሱስ ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም። 12 እንዲህም ይላል፤ “ስምህን ለወንድሞቼ ዐውጃለሁ፤ በጉባኤም መካከል አወድስሃለሁ።” 13 እንዲሁም፣ “እኔ በርሱ እታመናለሁ።” ደግሞም እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች።” 14 ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ፣ እርሱ ራሱ ደግሞ ያንኑ ተካፈለ፤ ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያብሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው፤ 15 እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት ባርነት የታሰሩትን ነጻ እንዲያወጣ ነው። 16 እርሱ የመጣው መላእክትን ለመርዳት ሳይሆን፣ የአብርሃምን ዘር ለመርዳት እንደ ሆነ ግልጽ ነው። 17 ስለዚህ በሁሉም ነገር ወንድሞቹን መምሰል ተገባው፤ ይህንም ያደረገው መሓሪና ታማኝ ሊቀ ካህናት ሆኖ፣ እግዚአብሔርን ለማገልገልና ለሕዝቡ የኀጢአትን ስርየት ለማስገኘት ነው። 18 እርሱ ራሱ በተፈተነ ጊዜ መከራን ስለ ተቀበለ፣ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.