ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ ከሆነ ሕይወት የተዋጃችሁት በሚጠፋ ነገር፣ በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤
ነገር ግን እናንተ የተዋጃችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው።
ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።
የገባውም የፍየልንና የጥጃዎችን ደም ይዞ አይደለም፤ ነገር ግን የዘላለም ቤዛነት ሊያስገኝ የራሱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ።
ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ እኛም በብርሃን ብንመላለስ፣ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፤ የልጁም የኢየሱስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል።
ነገር ግን እርሱ ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ በርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን፤ በርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።
“እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ የኀጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ በኩል መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤
በርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ ሕግ በኩል ማግኘት ያልተቻለውን ጽድቅ ያገኛል።
የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና። ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል።
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ በኢየሱስ ደም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት ድፍረት አግኝተናል፤
ፍጹም ሊያደርጋቸው ቢችል ኖሮ፣ መሥዋዕት ማቅረቡን ይተዉት አልነበረምን? ደግሞም ለአምልኮ የሚቀርቡት ሰዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለሚነጹ፣ በኅሊናቸው ኀጢአተኝነት ባልተሰማቸውም ነበር።
ይኸውም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል በከፈተልን አዲስና ሕያው መንገድ ነው።
በእግዚአብሔር ቤት ላይ የተሾመ ታላቅ ሊቀ ካህናት ስላለን፣
ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን፣ ሰውነታችንንም በንጹሕ ውሃ ታጥበን፣ በእውነተኛ ልብና በሙሉ እምነት ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ።
በእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት፣ በርሱም ዘንድ ማዳን አለና፣ እስራኤል ሆይ፤ በእግዚአብሔር ተስፋ አድርግ።
እርሱም እስራኤልን፣ ከኀጢአቱ ሁሉ ያድነዋል።
እኛ ስላደረግነው አንዳች ነገር ሳይሆን፣ ከዕቅዱና ከጸጋው የተነሣ ያዳነን፣ ወደ ቅዱስ ሕይወትም የጠራን እርሱ ነው። ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፤
እንዲህ ቢሆን ኖሮ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ መከራን መቀበል ባስፈለገው ነበር። አሁን ግን በዘመናት መጨረሻ ራሱን መሥዋዕት በማድረግ ኀጢአትን ለማስወገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገልጧል።
እግዚአብሔር ፍቅሩን በመካከላችን የገለጠው እንዲህ ነው፤ እኛ በርሱ አማካይነት በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከ።
ነገር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ፣
በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው።
ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም፤
ነገር ግን ክርስቶስ በውስጣችሁ ካለ፣ ሰውነታችሁ ከኀጢአት የተነሣ የሞተ ቢሆንም፣ መንፈሳችሁ ከጽድቅ የተነሣ ሕያው ነው።
ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የርሱ መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፣ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው፣ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ ሟች ለሆነው ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣል።
ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ ግዴታ አለብን፤ ይሁን እንጂ እንደ ሥጋ እንድንኖር ለሥጋ አይደለም።
እንደ ሥጋ ብትኖሩ ትሞታላችሁና፤ ክፉ የሆነውን የሥጋ ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን፣ በሕይወት ትኖራላችሁ።
በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና።
እንደ ገና የፍርሀት ባሪያ የሚያደርጋችሁን መንፈስ ሳይሆን፣ “አባ፣ አባት” ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብላችኋልና፤
የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋራ ሆኖ ይመሰክርልናል።
ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ የክብሩ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ በርግጥ የመከራው ተካፋዮች ብንሆን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች፣ ከክርስቶስ ጋራ ዐብረን ወራሾች ነን።
የአሁኑ ዘመን ሥቃያችን ወደ ፊት ሊገለጥ ካለው፣ ለእኛ ከተጠበቀልን ክብር ጋራ ሲነጻጸር ምንም እንዳይደለ እቈጥራለሁ።
ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በናፍቆት ይጠባበቃል።
ምክንያቱም የሕይወት መንፈስ ሕግ በክርስቶስ ኢየሱስ ከኀጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቷችኋል።
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው።
መድቀቁና መሠቃየቱ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር፤ እግዚአብሔር ነፍሱን የኀጢአት መሥዋዕት ቢያደርገውም እንኳ፣ ዘሩን ያያል፤ ዕድሜውም ይረዝማል፤ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል።
እኛ ግን አገራችን በሰማይ ነው፤ ከዚያ የሚመጣውንም አዳኝ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በናፍቆት እንጠባበቃለን፤
እርሱም ሁሉን ለራሱ ባስገዛበት ኀይል፣ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።
እናንተም በበደላችሁና የሥጋችሁን ኀጢአታዊ ባሕርይ ባለመገረዝ ሙታን ነበራችሁ፣ እግዚአብሔር ግን ከክርስቶስ ጋራ ሕያዋን አደረጋችሁ፤ በደላችንንም ሁሉ ይቅር አለን፤
ኀጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፤ በደሌንም አልሸሸግሁም፤ ደግሞም “መተላለፌን ለእግዚአብሔር እናዘዛለሁ” አልሁ፤ አንተም የኀጢአቴን በደል፣ ይቅር አልህ። ሴላ
ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም እንዲሰረይላችሁ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።
በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፤ ነፍሴ በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች፤ ሙሽራ ራሱን እንደሚያሳምር፣ ሙሽራዪቱም በዕንቈቿ እንደምታጌጥ፣ የድነትን ልብስ አልብሶኛል፤ የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛል።
እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ፤ እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣ መተላለፌን ደምስስ።
አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።
ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድ።
የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፤ በእሽታ መንፈስም ደግፈህ ያዘኝ።
እኔም ለሕግ ተላላፊዎች መንገድህን አስተምራለሁ፤ ኀጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ።
የድነቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ደም ከማፍሰስ አድነኝ፤ አንደበቴም ስለ ጽድቅህ በእልልታ ይዘምራል።
ጌታ ሆይ ከንፈሮቼን ክፈት፤ አፌም ምስጋናህን ያውጃል።
መሥዋዕትን ብትወድድ ኖሮ ባቀረብሁልህ ነበር፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም ደስ አያሰኝህም።
እግዚአብሔር የሚቀበለው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም።
በበጎ ፈቃድህ ጽዮንን አበልጽጋት፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥሮች ሥራ።
የጽድቅ መሥዋዕት፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ያን ጊዜ ደስ ያሰኙሃል፤ ኰርማዎች በመሠዊያህ ላይ የሚሠዉትም ያን ጊዜ ነው።
በደሌን ፈጽሞ ዕጠብልኝ፤ ከኀጢአቴም አንጻኝ።
ስለዚህ ድርሻውን ከታላላቆች ጋራ እሰጠዋለሁ፤ ምርኮውን ከኀያላን ጋራ ይካፈላል፤ እስከ ሞት ድረስ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠቱ፣ ከክፉ አድራጊዎችም ጋራ በመቈጠሩ፣ የብዙዎችን ኀጢአት ተሸከመ፤ ስለ ዐመፀኞችም ማለደ።
ነገር ግን የተወሰነው ዘመን በደረሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን፣ ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤
ይህም የሆነው የልጅነትን መብት እናገኝ ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ለመዋጀት ነው።
እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቷልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤
እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ የተቀደሰ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ገንዘቡ ያደረገው ሕዝብ ናችሁ።
አሁን ግን፣ ያዕቆብ ሆይ የፈጠረህ፣ እስራኤል ሆይ! የሠራህ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ ነህ፤