ለሩፋኤል የታሰበ የአገልግሎት ዋጋ1 ከዚህም በኋላ ጦቢት ጦብያን ጠርቶ፥“ ልጄ ሆይ፥ ከአንተ ጋራ የሄደ የዚህን ሰው ደመወዙን እይለት፤ ዳግመኛም ትጨምርለት ዘንድ ይገባል” አለው። 2 ጦብያም አባቱን እንዲህ አለው፥ “ያመጣሁትን የገንዘቤን እኩሌታ ስንኳ ብሰጠው የሚጐዳኝ የለም። 3 ወደ አንተ በደኅና መልሶኛልና፥ ሚስቴንም ፈውሷታልና፤ ብሩንም አምጥቶልኛልና፤ እንዲሁም አንተን ፈውሶሃልና።” 4 አባቱም፥ “እውነት ተናገርህ” አለው። 5 ያንም መልአክ ጠርቶ እንዲህ አለው፥ “ከእናንተ ጋር ካመጣችሁት ሁሉ እኩሌታውን ይዘህ በደኅና ሂድ።” 6 ሩፋኤልም ያንጊዜ ሁለቱን ሁሉ ጠራቸው፤ ገለል አድርጎም እንዲህ አላቸው፥ “እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ ለእርሱም ተገዙ፤ ለስሙም ምስጋና አቅርቡ፤ ስላደረገላችሁም በጎ ነገር ሁሉ በሰው ሁሉ ፊት እመኑበት፤ እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ ስሙንም አመስግኑ፤ የእግዚአብሔርንም ሥራ በክብር ተናገሩ፤ ተአምራቱንም ግለጡ፤ እርሱንም ከማመስገን ቸል አትበሉ። 7 የመንግሥትን ምሥጢር ሊሰውሩት፥ የእግዚአብሔርን ሥራ ግን በክብር ሊገልጡት ይገባልና፤ መከራም እንዳታገኛችሁ በጎ ሥራን ሥሯት። 8 ጸሎት ከጾም፥ ከምጽዋትና ከጽድቅ ጋር መልካም ነው። ከብዙ የዓመፅ ገንዘብ ጥቂት የእውነት ገንዘብ ይሻላል፤ ወርቅንም ከማድለብ ምጽዋት መስጠት ይሻላል። 9 ምጽዋት ከሞት ታድናለች፤ ከኀጢአትም ሁሉ ታነጻለችና፥ ጽድቅንና ምጽዋትን የሚያደርጉም ሁሉ ለራሳቸው ሕይወትን ይሞላሉ። 10 የሚበድሉ ግን ሕይወታቸውን ይጠሏታል። 11 “እነሆ፥ ነገሩን ሁሉ ከእናንተ አልሰውርም፤ የመንግሥትን ምሥጢር ሊሰውሩት የእግዚአብሔርን ሥራ ግን በክብር ሊገልጡት መልካም እንደ ሆነ እነግራችኋለሁ። 12 እነሆ፥ አንተና ምራትህ ሣራ በጸለያችሁ ጊዜ የልመናችሁን መታሰቢያ እኔ በቅዱሱ ፊት አቀረብሁ፤ አንተም ሬሳ በቀበርህ ጊዜ ያንጊዜ እኔ ካንተ ጋራ ነበርሁ። 13 ቸል ባላልህ ጊዜ፥ ምሳህንም ትተህ በተነሣህ ጊዜ፥ ሬሳንም ትቀብር ዘንድ በሄድህ ጊዜ፥ በጎ ሥራን መሥራትንም ባልዘነጋህ ጊዜ እኔ ከአንተ ጋር ነበርሁ። 14 አሁንም፦ ጌታ እግዚአብሔር አንተን አድንህ ዘንድ፥ ምራትህ ሣራንም ከኀዘኗ አረጋጋት ዘንድ ላከኝ። 15 የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ፥ በገናናውና በቅዱሱ ጌትነት ፊት ከሚያቀርቡ ሰባቱ ቅዱሳን መላእክት አንዱ መልአክ እኔ ሩፋኤል ነኝ” አላቸው። 16 ይህንም ሰምተው ሁለቱ ደነገጡ፤ ፈርተዋልምና በግምባራቸው ወደቁ። 17 መልአኩም እንዲህ አላቸው፥ “አትፍሩ፤ ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔርን ፍሩት፥ እግዚአብሔርንም ፈጽማችሁ አመስግኑት፤ 18 ምስጋና ለእኔ አይገባኝምና፥ ነገር ግን የአምላካችሁ ፈቃድ አመጣኝ፤ ስለዚህም በዘመናት ሁሉ ለዘለዓለሙ እግዚአብሔርን አመስግኑት። 19 እኔም ተገለጥሁላችሁ፤ ነገር ግን እይታን አያችሁ እንጂ ከእናንተ ጋር አልበላሁም፤ አልጠጣሁምም። 20 አሁንም በእግዚአብሔር እመኑ፥ ወደ ላከኝም ወደ ላይ እወጣለሁና ይህን ሁሉ በመጽሐፍ ጻፉት” አለ። 21 ያን ጊዜም ተነሥቶ ሄደ፤ ከዚያ በኋላም አላዩትም። 22 የእግዚአብሔርም መልአክ ስለ ተገለጸላቸው፥ ገናናና ድንቅ በሚሆን በእግዚአብሔር ሥራ ሁሉ አመኑ። |