ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጦቢት 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ከዚህም በኋላ ሩፋኤል ጦብያን አለው፥ “አንተ ወንድሜ አባትህን እንዴት እንደ ተውኸው አታውቅምን? 2 ና ከሚስትህ ቀድመን ሄደን ቤቱን እናዘጋጅ። 3 የዚህንም ዓሣ ሐሞት ያዝ፤” ያም ከእነርሱ ጋር የተከተለው ብላቴና ከእነርሱ ጋር ሄደ። 4 ሐና ግን በጎዳና ተቀምጣ ልጅዋን ታይ ዘንድ ትመለከት ነበር። 5 ሲመጣም አየችው፤ ሄዳም አባቱን፥ “እነሆ፥ ልጅህ መጣ፤ ከእርሱም ጋር የሄደው ያ ሰው መጣ” አለችው። የጦቢት ዐይን እንደ በራ 6 ሩፋኤልም አለው፥ “ያባትህ ዐይኖች እንዲበሩ አውቃለሁ፤ 7 አንተ ግን ያን ሐሞት ያባትህን ዐይን ኳለው፤ በተኳለም ጊዜ ዐይኖቹን ያሻል፤ ብልዙም ከዐይኑ ይወጣል፤ በደኅናም ያያል።” 8 ሐናም ሮጣ የልጅዋን አንገት አቅፋ፥ “ልጄ ሆይ፥ ካየሁህ እንግዲህ ልሙት” አለችው፤ ሁለቱም አለቀሱ። 9 ጦቢትም ወደ ደጅ ወጣ፤ ተሰነካከለም፤ ልጁም ሮጦ አባቱን አነሣው። 10 የአባቱንም ዐይኖች በዚያ ሐሞት ኳለና፥ “አባቴ ሆይ፥ እንደምትድን ታመን” አለው። 11 በኳለውም ጊዜ ዐይኖቹን አሸ። 12 ብልዙም ከዐይኑ ብሌን ተገፈፈ፤ ልጁንም አየው፤ አንገቱንም አቅፎ አለቀሰ። 13 እንዲህም አለ፥ “ጌታ ሆይ፥ የተመሰገንህ ነህ፤ ስምህም ለዘለዓለሙ ይመስገን፤ ቅዱሳን መላእክትህም ሁሉ ቡሩካን ናቸው፤ ገርፈህ ይቅር ብለኸኛልና። 14 እነሆም፥ ልጄ ጦብያን አየሁት፤” ከዚህም በኋላ ልጁ ደስ እያለው ገባ፤ ለአባቱም በሜዶን የተደረገለትን ታላላቅ ነገር ሁሉ ነገረው። 15 ጦቢትም ደስ እያለው ወጥቶ ምራቱን ተቀበላት፤ እግዚአብሔርንም በነነዌ አደባባይ አመሰገነው፤ ሲሄድም ያዩት ሰዎች፥ “እንዴት አየ?” ብለው አደነቁት። 16 ጦቢት ግን በፊታቸው እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ እግዚአብሔር ይቅር ብሎታልና። ጦቢትም ወደ ምራቱ ወደ ሣራ በደረሰ ጊዜ፥ “ልጄ! እንኳን በደኅና ገባሽ!” ብሎ መረቃት፤ ወደ እኛ ያመጣሽ እግዚአብሔርም ይመስገን፤ አባትሽንና እናትሽንም ይባርክ” አላት። በነነዌም ለሚኖሩ ለወንድሞቹ ሁሉ ታላቅ ደስታ ሆነ። 17 አኪአክሮስም መጣ፤ የወንድሙ ልጅ ነሳቦስም መጣ። 18 ሰባት ቀንም በደስታ የሰርግ በዐል አደረጉ። |