ሶፎንያስ 3:15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔር ፍርድሽን አስወግዶአል፥ ጠላትሽንም ጥሎአል፣ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር በመካከልሽ አለ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አታዪም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔር ቅጣትሽን አስወግዶታል፤ ጠላቶችሽን ከአንቺ መልሷል፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ነው፤ ከእንግዲህ ወዲያ አንዳች ክፉ ነገር አትፈሪም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታ ቅጣትሽን አስወግዷል፥ ጠላትሽንም አጥፍቷል፤ የእስራኤል ንጉሥ ጌታ በመካከልሽ አለ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አትፈሪም። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ያስተላለፈውን የቅጣት ፍርድ አንሥቶላችኋል፤ ጠላቶቻችሁንም አስወግዶላችኋል፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ነው፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጥፋት ይደርስብናል ብላችሁ አትፈሩም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔር ፍርድሽን አስወግዶአል፥ ጠላትሽንም ጥሎአል፥ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር በመካከልሽ አለ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አታዪም። |
ሞት ሰዎችን ዋጠ፤ በረታም፤ እንደ ገናም ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፤ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር በአፉ ተናግሮአልና።
አምላካችን እግዚአብሔር ታላቅ ነውና ቸል አይለንም፤ እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው፤ እግዚአብሔር አምላካችን ነው። እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው፤ እርሱ እግዚአብሔር ያድነናል።
በእግዚአብሔር የተሰበሰቡም ይመለሳሉ፤ በደስታም ተመልሰው ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘለዓለም ደስታም በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታንም ያገኛሉ፤ መከራ፥ ኀዘንና ትካዜም ይጠፋሉ።
ለወገኑ የሚፈርድ አምላክሽ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ፥ የሚያንገደግድሽን ጽዋ የቍጣዬንም ጽዋ ከእጅሽ ወስጃለሁ፤ ደግመሽም ከእንግዲህ ወዲህ አትጠጪውም።
እንግዲህ በምድርሽ ውስጥ ግፍ፥ በዳርቻሽም ውስጥ ጕስቍልናና ቅጥቃጤ አይሰማም፤ ቅጥሮችሽ ድኅነት ይባላሉ፤ በሮችሽም በጥርብ ድንጋይ ይሠራሉ።
እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤትን አደርጋለሁ፤ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ በውስጥዋ አይሰማም።
እነሆ እግዚአብሔር በጽዮን የለምን? ወይስ ንጉሥዋ በእርስዋ ዘንድ የለምን? የሚል የወገኔ ሴት ልጅ ጩኸት ድምፅ ከሩቅ ሀገር ተሰማ። በተቀረፁ ምስሎቻቸውና በባዕድ ከንቱነትስ ያስቈጡኝ ስለ ምንድን ነው?
“እግዚአብሔርም በዚያ ሳለ፥ አንተ፥ እነዚህ ሁለቱ ሕዝቦች፥ እነዚህም ሁለቱ ሀገሮች ለእኔ ይሆናሉ፤ እኔም እወርሳቸዋለሁ ብለሃልና፤
ዳግመኛም የአሕዛብን ስድብ አላሰማብሽም፤ ዳግመኛም የአሕዛብን ውርደት አትሸከሚም፤ ዳግመኛም ሕዝብሽን አታሰናክዪም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”
ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልመልስም፤ መዓቴን በእስራኤል ቤት ላይ አፍስሻለሁና፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
ዙሪያዋም ዐሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ከዚያም ቀን ጀምሮ የከተማዪቱ ስም፦ ‘እግዚአብሔር በዚያ አለ’ ተብሎ ይጠራል።”
“እኔም በተቀደሰ ተራራዬ በጽዮን የምቀመጥ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ ያን ጊዜም ኢየሩሳሌም የተቀደሰች ከተማ ትሆናለች፥ እንግዶችም ከእንግዲህ ወዲህ አያልፉባትም።
በምድራቸውም እተክላቸዋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ከሰጠኋቸው ከምድራቸው አይነቀሉም” ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር አምላክ።
የሰውንም ደም ስላፈሰስህ፥ በምድሪቱና በከተማይቱም በእርስዋም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፥ በሊባኖስ ላይ የሠራኸው ግፍ ይከድንሃል፣ የአራዊትም አደጋ ያስፈራራሃል።
የሰውን ደም ስላፈሰስህ፥ በምድሪቱና በከተማይቱም በእርስዋም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፥ አንተ ብዙዎችን አሕዛብን በዝብዘሃልና ከአሕዛብ የቀሩት ሁሉ ይበዘብዙሃል።
አምላክሽ እግዚአብሔር በመካከልሽ ታዳጊ ኃያል ነው፣ በደስታ በአንቺ ደስ ይለዋል፥ በፍቅሩም ያርፋል፥ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል ይባላል።
እግዚአብሔር በውስጥዋ ጻድቅ ነው፣ ክፋትን አያደርግም፣ ፍርዱን በየማለዳው ወደ ብርሃን ያወጣል፥ ሳያወጣውም አይቀርም፣ ዓመፀኛው ግን እፍረትን አያውቅም።
በዚያም ቀን ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ ከባድ ድንጋይ አደርጋታለሁ፣ የሚሸከሙአት ሁሉ እጅግ ይቈስላሉ፣ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በላይዋ ላይ ይከማቻሉ።
አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፣ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፣ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፣ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫንይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።
ናትናኤልም፥ “በየት ታውቀኛለህ?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ገና ፊልጶስ ሳይጠራህ በበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ አይችሃለሁ” አለው።
እኔ ከራሴ አንዳች አደርግ ዘንድ አልችልም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ እንጂ፤ ፍርዴም እውነት ነው፤ የላከኝን ፈቃድ እንጂ የእኔን ፈቃድ አልሻምና።
ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ፤ እንዲህ ሲል “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኀይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፤ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸውየወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።