Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ራእይ 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)


ሴቲቱና ዘንዶው

1 ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ፤ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የዐሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የተቀዳጀች አንዲት ሴት ነበረች።

2 እርስዋም ፀንሳ ነበር፤ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጭንቃ ጮኸች።

3 ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ ይኸውም ታላቅ ቀይ ዘንዶነው፤ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶችም ነበሩት፤ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፤

4 ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ።

5 አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።

6 ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሓ ሸሸች።

7 በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፤

8 አልቻላቸውምም፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም።

9 ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።

10 ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ፤ እንዲህ ሲል “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኀይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፤ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸውየወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።

11 እነርሱም በበጉ ደም በምስክራቸውም ቃል ድል ነሡት፤ ነፍሳቸውንም እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም።

12 ስለዚህ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ! ደስይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፤ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።”

13 ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት።

14 ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኵሌታ ወደ ምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሓ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት።

15 እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውሃ ከአፉ በስተ ኋላዋ አፈሰሰ።

16 ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፤ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው።

17 ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፤

18 በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos