Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሶፎንያስ 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የእስራኤል ክፋት

1 ለዓመፀኛዪቱና ለረከሰች፥ ለጨቋኞች ከተማ ወዮላት!

2 ማንንም አታዳምጥም፥ እርምት አትቀበልም፥ በጌታ አልታመነችም፥ ወደ አምላክዋም አልቀረበችም።

3 በውስጧ የሚኖሩ ባለ ሥልጣኖቿ የሚያገሡ አንበሶች ናቸው፥ ፈራጆችዋም ለጠዋት ምንም የማያስቀሩ የማታ ተኩላዎች ናቸው።

4 ነቢዮችዋ ስዶችና ከሐዲ ሰዎች ናቸው፥ ካህናቶቿ መቅደሱን አርክሰዋል፥ በሕግም ላይ አምፀዋል።

5 በውስጧ ያለው ጌታ ጻድቅ ነው፥ ስሕተት አያደርግም፥ ማለዳ ማለዳ ፍርዱን ለብርሃን ይሰጣል፥ አያቋርጥምም፤ ዓመፀኛው ግን እፍረትን አያውቅም።

6 መንግሥታትን አጥፍቻለሁ፥ ግንቦቻቸው ሁሉ ፈርሰዋል፥ መንገዶቻቸውን ማንም የማይተላለፍባቸው ባዶ ሆነዋል፥ ከተሞቻቸውም አንድም ሰው እንዳይገኝባቸው፥ ማንም የማይኖርባቸው ሆነዋል።

7 እኔም አልኩ “በእርግጥ ትፈሪኛለሽ፥ እርማትንም ትቀበያለሽ፤ መኖሪያዋ አይጠፋም፥ ያቀድኩትም አይደርስም።” እነርሱ ግን በማለዳ ተነሥተው ድርጊታቸውን ሁሉ አረከሱ።


የመንግሥታት መቀጣትና መመለስ

8 ስለዚህ “ጠብቁኝ” ይላል ጌታ፤ ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ፥ ፍርዴ ሕዝቦችን ለመሰብሰብ፥ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነው፥ ይህም መዓቴንና የቁጣዬን ትኩሳት ሁሉ ለማፍሰስ ነው፤ በቅንዓቴ እሳት ምድርም ሁሉ ትበላለችና።

9 በዚያን ጊዜም ሁሉም የጌታን ሥም እንዲጠሩና በአንድ ትከሻ እንዲያገለግሉት፥ ለሕዝቦች ንጹሕን አንደበት እመልስላቸዋለሁ።

10 ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚያመልኩኝ፥ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ፥ ቁርባኔን ያመጡልኛል።

11 በዚያ ቀን በእኔ ላይ አምፀሽ በሠራሽው ሥራ ሁሉ አታፍሪም፤ በኩራትሽ የተደሰቱትን ከመካከልሽ አወጣለሁና፥ አንቺም በቅዱስ ተራራዬ ላይ ዳግመኛ አትታበዪም።

12 በመካከልሽ ትሑትና ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሕዝብን አስቀራለሁ፤ በጌታም ስም ይታመናሉ።

13 የእስራኤል ትሩፍ ኃጢአትን አይሠሩም፥ ሐሰትንም አይናገሩም፥ በአፋቸውም ውስጥ አታላይ ምላስ አይገኝም፤ እነርሱም ይሰማራሉ፥ ይተኛሉ፥ የሚያስፈራቸውም የለም።


የደስታ መዝሙር

14 የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ዘምሪ፤ እስራኤል ሆይ፥ እልል በሉ፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ በፍጹም ልብሽ ሐሴት አድርጊ ደስም ይበልሽ።

15 ጌታ ቅጣትሽን አስወግዷል፥ ጠላትሽንም አጥፍቷል፤ የእስራኤል ንጉሥ ጌታ በመካከልሽ አለ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አትፈሪም።

16 በዚያን ቀን ኢየሩሳሌም እንዲህ ይባልላታል፦ “ጽዮን ሆይ፥ አትፍሪ፥ እጆችሽም አይዛሉ።

17 ጌታ አምላክሽ በመካከልሽ ኃያል ታዳጊ ነው፤ በአንቺም በፍጹም በደስታ ደስ ይለዋል፥ በፍቅሩም ያርፋል፥ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል።”

18 ከበዓሉ ርቀው የሚያዝኑትን፥ ከአንቺም የሆኑትን እሰበስባለሁ፤ ስድብ እንደ ሸክም ከብዶባቸው ነበር።

19 እነሆ በዚያ ዘመን፥ ያስጨነቁሽን ሁሉ እቀጣለሁ፤ አንካሳይቱንም አድናለሁ፥ የተጣለችውንም እሰበስባታለሁ፤ ባፈሩባትም ምድር ሁሉ ላይ ለምስጋናና ለከበረ ስም አደርጋቸዋለሁ።

20 በዚያ ዘመን እሰበስባችኋለሁ፥ በሰበሰብኳችሁም ጊዜ፤ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር ሕዝቦች ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል ጌታ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos