ዮሐንስ 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጌታችንን ሽቱ ስለ ቀባችው ሴት 1 ፋሲካ ከሚውልበት ከስድስተኛው ቀን አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው አልዓዛር ወደ ነበረበት ወደ ቢታንያ መጣ። 2 በዚያም ምሳ አደረጉለት፤ ማርታም ታሳልፍላቸው ነበር፤ አብረውት ምሳ ከበሉትም አንዱ አልዓዛር ነበር። 3 ማርያም ግን ዋጋዉ የከበረና የበዛ አንድ ነጥር የጥሩ ናርዶስ ሽቱ ወሰደችና የጌታችን ኢየሱስን እግር ቀባችው፤ በፀጕሯም አሸችው፤ የዚያ ሽቱ መዓዛም ቤቱን መላው። 4 ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የነበረ ያሲዘው ዘንድ ያለው የስምዖን ልጅ አስቆሮታዊው ይሁዳ ግን እንዲህ አለ። 5 “ለነዳያን ይሰጥ ዘንድ ይህን ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ለምን አልሸጡትም?” 6 ይህንም ያለ፥ ድሆች አሳዝነውት አይደለም፤ ሌባ ነበርና፥ ሙዳየ ምጽዋቱንም ሲጠብቅ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ነበርና ስለዚህ ነው እንጂ። 7 ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለ፥ “ለምቀበርበት ቀን ትጠብቀው ዘንድ ተዉአት። 8 ድሆች ግን ዘወትር አብረዋችሁ አሉ፤ ዘወትርም ታገኙአቸዋላችሁ፤ በወደዳችሁም ጊዜ መልካም ታደርጉላቸዋላችሁ፤ እኔን ግን ዘወትር የምታገኙኝ አይደለም።” 9 ከአይሁድም ብዙ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ በዚያ እንዳለ በዐወቁ ጊዜ ወደ እርሱ መጡ፤ የመጡትም ጌታችን ኢየሱስን ለማየት ብቻ አልነበረም፤ ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ለይቶ ያስነሣዉን አልዓዛርንም ያዩ ዘንድ ነበር እንጂ። 10 የካህናት አለቆችም አልዓዛርን ሊገድሉት ተማከሩ። 11 ከአይሁድ ብዙዎች ስለ እርሱ እየሄዱ በጌታችን በኢየሱስ ያምኑ ነበርና። ወደ ኢየሩሳሌም ስለ መግባቱ 12 በማግሥቱም ለበዓል መጥተው የነበሩ ብዙ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመጣ በሰሙ ጊዜ፥ 13 የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው “ሆሣዕና በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ፥ የእስራኤልም ንጉሥ ቡሩክ ነው” እያሉ ወጥተው ተቀበሉት። 14 ጌታችን ኢየሱስም የአህያ ውርንጫ አግኝቶ በእርስዋ ላይ ተቀመጠ። 15 “የጽዮን ልጅ ሆይ፥ አትፍሪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ ይመጣል” ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ 16 ደቀ መዛሙርቱም አስቀድመው ይህን ነገር አላወቁም፤ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ከከበረ በኋላ በዚያ ጊዜ ይህ ነገር ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ፥ ይህንም እንደ አደረጉለት ትዝ አላቸው። 17 ከዚያም አብረውት የነበሩት ሕዝብ አልዓዛርን ከመቃብር እንደ ጠራው፥ ከሙታንም እንደ አስነሣው መሰከሩለት። 18 ስለዚህም ነገር ሕዝቡ ሁሉ ሊቀበሉት ወጡ፤ ይህን ተአምራት እንደ አደረገ ሰምተዋልና። 19 ፈሪሳውያንም እርስ በርሳቸው፥ “የምታገኙት ምንም ጥቅም እንደሌለ ታያላችሁን? እነሆ፥ ዓለም ሁሉ ተከትሎታል” ተባባሉ። ለበዓል ስለ መጡ ሰዎች 20 ከጽርዕ ሰዎችም ይሰግዱ ዘንድ ለበዓል የወጡ ነበሩ። 21 እነርሱም ከገሊላ፥ የቤተ ሳይዳ ሰው ወደ ሆነው ወደ ፊልጶስ ሄደው፥ “አቤቱ፥ ጌታ ኢየሱስን ልናየው እንወድዳለን” ብለው ለመኑት። 22 ፊልጶስም ሄዶ ለእንድርያስ ነገረው፤ እንድርያስና ፊልጶስም ሄደው ለጌታችን ለኢየሱስ ነገሩት። 23 ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁን የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ጊዜው ደረሰ። 24 እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት በምድር ላይ ካልወደቀችና ካልሞተች ብቻዋን ትኖራለች፤ ከሞተች ግን ብዙ ፍሬን ታፈራለች። 25 ነፍሱን የሚወዳት ይጥላታል፤ በዚህ ዓለም ነፍሱን የሚጥላትም ለዘለዓለም ሕይወት ይጠብቃታል። 26 እኔን የሚያገለግለኝ ካለ ይከተለኝ፤ የሚያገለግለኝ እኔ ባለሁበት በዚያ ይኖራልና፤ እኔን የሚያገለግለኝንም አብ ያከብረዋል። 27 “አሁንስ ነፍሴ ታወከች፤ ግን ምን እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚች ሰዓት ነፍሴን አድናት፤ ነገር ግን ስለዚህ ነገር ለዚች ሰዓት ደርሻለሁ። 28 አባት ሆይ፥ ልጅህን አክብረው።” ከሰማይም፥ “አከበርሁህ፤ ደግሞም እንደገና አከብርሃለሁ፤” የሚል ቃል መጣ። 29 በዚያ ቆመው ይሰሙ የነበሩ ሕዝብ ግን “ነጐድጓድ ነው” አሉ፤ “መልአክ ተናገረው” ያሉም አሉ። 30 ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ይህ ቃል የመጣ ስለ እናንተ ነው እንጂ ስለ እኔ አይደለም። 31 አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደረሰ፤ ከእንግዲህስ ወዲህ የዚህን ዓለም ገዥ ወደ ውጭ አስወጥተው ይሰዱታል። 32 እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ካልሁ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።” 33 ይህንም ያለ በምን ዐይነት ሞት ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲያመለክታቸው ነው። 34 ሕዝቡም፥ “እኛስ ክርስቶስ ለዘለዓለም እንዲኖር በኦሪት ሰምተን ነበር፤ እንግዲህ እንዴት አንተ ‘የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ይል ዘንድ አለው’ ትለናለህ? እንግዲህ ይህ የሰው ልጅ ማን ነው?” ብለው መለሱለት። 35 ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፥ “ ገና ለጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው፤ በጨለማ የሚመላለስ የሚሄድበትን አያውቅምና ጨለማ እንዳያገኛችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ 36 የብርሃን ልጆች ትሆኑ ዘንድ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን እመኑ” ጌታችን ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ሄደ፤ ተሰወራቸውም። 37 ይህንም ያህል ተአምራት በፊታቸው ሲያደርግ አላመኑበትም። 38 “አቤቱ፥ ምስክርነታችንን ማን ያምነናል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ?” ያለው የነቢዩ የኢሳይያስ ቃል ይደርስ ዘንድ። 39 ስለዚህም ማመን ተሳናቸው፤ ኢሳይያስ ዳግመኛ እንዲህ ብሎአልና። 40 “በዐይናቸው አይተው፥ በልባቸውም አስተውለው እንዳይመለሱና እንዳልፈውሳቸው ዐይኖቻቸው ታወሩ፤ ልባቸውም ደነደነ።” 41 ኢሳይያስ ጌትነቱን አይቶአልና፥ ይህን ተናገረ፤ ስለ እርሱም መሰከረ። 42 ከሕዝቡ አለቆችም ያመኑበት ብዙዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ከምኵራብ አስወጥተው እንዳይሰዱአቸው በፈሪሳውያን ምክንያት አልመሰከሩለትም። 43 ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የሰውን ክብር ወደዋልና። 44 ጌታችን ኢየሱስም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፥ “በእኔ የሚያምን በላከኝም ነው እንጂ በእኔ ብቻ የሚያምን አይደለም። 45 እኔን ያየ የላከኝን አየ። 46 በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን እኔ ወደ ዓለም መጣሁ። 47 ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቀውን እኔ የምፈርድበት አይደለሁም፤ ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድበት አልመጣሁምና። 48 የሚክደኝን፥ ቃሌንም የማይቀበለውን ግን የሚፈርድበት አለ፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻዪቱ ቀን ይፈርድበታል። 49 የተናገርሁት ከእኔ የሆነ አይደለምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እንድናገር፥ እንዲህም እንድል እርሱ ትእዛዝን ሰጠኝ። 50 ትእዛዙም የዘለዓለም ሕይወት እንደ ሆነ አውቃለሁ፤ እኔም የምናገረውን አብ እንዳለኝ እንዲሁ እናገራለሁ።” |