ዮሐንስ 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)አይሁድ ጌታን እንደ ገረፉትና እንደ ተዘባበቱበት 1 ከዚህም በኋላ ጲላጦስ ጌታችን ኢየሱስን ይዞ ገረፈው። 2 ጭፍሮችም የእሾህ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ ደፉበት፤ የቀይ ሐር መጐናጸፊያም አለበሱት። 3 ወደ እርሱም እየመጡ፥ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን” ይሉት ነበር፤ በጥፊም ይመቱት ነበር። 4 ጲላጦስም እንደገና ወደ ውጭ ወጣና፥ “እነሆ፥ በእርሱ ላይ አንዲት በደል ስንኳን ያገኘሁበት እንደሌለ ታውቁ ዘንድ ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ” አላቸው። 5 ጌታችን ኢየሱስም የእሾህ አክሊል ደፍቶ፥ የቀይ ሐር መጐናጸፊያም ለብሶ ወደ ውጭ ወጣ፤ ጲላጦስም፥ “እነሆ፥ ሰውዬው” አላቸው። 6 ሊቃነ ካህናትና ሎሌዎቻቸውም ባዩት ጊዜ፥ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮሁ፤ ጲላጦስም፥ “እናንተ ራሳችሁ ውሰዱና ስቀሉት፤ እኔስ በእርሱ ላይ በደል አላገኘሁበትም” አላቸው። 7 አይሁድም መልሰው፥ “እኛ ሕግ አለን፤ እንደ ሕጋችንም ሊሞት ይገባል፤ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአልና” አሉት። 8 ጲላጦስም ይህን ነገር ሰምቶ እጅግ ፈራ። ጲላጦስ ዳግመኛ እንደ መረመረው 9 ደግሞም ወደ ፍርድ አደባባይ ገባና ጌታችን ኢየሱስን፥ “አንተ ከወዴት ነህ?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም። 10 ጲላጦስም፥ “ለእኔም አትነግረኝምን? ልሰቅልህ ሥልጣን እንደ አለኝ፥ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ፥ አታውቅምን?” አለው። 11 ጌታችን ኢየሱስም፥ “ከሰማይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ አንዳች ሥልጣን የለህም፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው ታላቅ ኀጢኣት አለበት” አለው። 12 ስለዚህም ጲላጦስ ሊፈታው ወድዶ ነበር፤ አይሁድ ግን፥ “ይህን ከፈታኸው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሰው ሁሉ በቄሣር ላይ የሚያምፅ ነውና” ብለው ጮሁ። ጲላጦስ ወደ ሊቶስጥሮስ እንደ አወጣው 13 ጲላጦስም ይህን ሰምቶ ጌታችን ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፤ በዕብራይስጥም ገበታ ተብሎ በሚጠራው “ጸፍጸፍ” በሚሉት ቦታ ላይ በወንበር ተቀመጠ። 14 የፋሲካም የመዘጋጀት ቀን ነበር፤ ጊዜዉም ስድስት ሰዓት ያህል ነበር፤ ጲላጦስም አይሁድን፥ “እነሆ፥ ንጉሣችሁ” አላቸው፤ 15 እነርሱ ግን፥ “አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮሁ። ጲላጦስም፥ “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” አላቸው፤ ሊቃነ ካህናቱም፥ “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው መለሱ። ጌታችን ስለ መሰቀሉ 16 ከዚህ በኋላ ሊሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ጌታችን ኢየሱስንም ተቀብለው ወሰዱት። 17 መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ወጣ። 18 በዚያም ሰቀሉት፤ ከእርሱም ጋር አንዱን በቀኝ፥ አንዱንም በግራ አድርገው ሌሎች ሁለት ወንበዴዎችን ሰቀሉ፤ ኢየሱስንም በመካከላቸው ሰቀሉ። 19 ጲላጦስም ጽሕፈት ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረ፤ ጽሕፈቱም፥ “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ነበር። 20 ከአይሁድም ይህቺን ጽሕፈት ያነበብዋት ብዙዎች ነበሩ፤ ጌታችን ኢየሱስን የሰቀሉበት ቦታ ለከተማ ቅርብ ነበርና፤ ጽሕፈቱም የተጻፈው በዕብራይስጥ፥ በሮማይስጥና በግሪክ ነበር። 21 ሊቃነ ካህናትም ጲላጦስን አሉት፥ “እርሱ ራሱ ‘እኔ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ’ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ።” 22 ጲላጦስም፥ “የጻፍሁትን ጻፍሁ” ብሎ መለሰላቸው። ልብሱን እንደ ተካፈሉ 23 ጭፍሮችም ጌታችን ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ከጭፍሮቹ ለእያንዳንዱ አራት ክፍል አድርገው መደቡት፤ ቀሚሱንም ወሰዱ፤ ቀሚሱም ከላይ ጀምሮ የተሠራ ሥረወጥ እንጂ የተሰፋ አልነበረም። 24 እርስ በርሳቸውም፥ “ዕጣ እንጣጣልና ለደረሰ ይድረሰው እንጂ አንቅደደው ተባባሉ፤” ይህም “ልብሶችን ለራሳቸው ተካፈሉ፤ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” ያለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው፤ ጭፍሮችም እንዲሁ አደረጉ። ጌታ እናቱን ለደቀ መዝሙሩ አደራ ስለ መስጠቱ 25 በጌታችን በኢየሱስ መስቀል አጠገብም እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊት ማርያምም ቆመው ነበር። 26 ጌታችን ኢየሱስም እናቱንና የሚወደውን ደቀ መዝሙሩን ቆመው ባያቸው ጊዜ እናቱን፥ “አንች ሆይ፥ እነሆ፥ ልጅሽ” አላት። 27 ከዚህም በኋላ ደቀ መዝሙሩን፥ “እናትህ እነኋት” አለው፤ ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ተቀብሎ ወደ ቤቱ ወሰዳት። ስለ ጌታችን ሞት 28 ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ሁሉ እንደ ተፈጸመ ባየ ጊዜ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ “ተጠማሁ” አለ። 29 በዚያም ሆምጣጤ የመላበት ማሰሮ ነበር፤ እነርሱም ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው በስምዛ ዘንግ ከአፉ አገናኝተው ጨመቁት። 30 ጌታችን ኢየሱስም ሆምጣጤውን ቀምሶ፥ “ሁሉ ተፈጸመ” አለ፤ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን ሰጠ። ከመስቀል ስለ መውረዱ 31 አይሁድ ግን የመዘጋጀት ቀን ነበርና፥ የዚያች ሰንበትም ቀን ታላቅ ናትና “ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ አይደር” አሉ፤ ጭን ጭናቸውንም ሰብረው ያወርዷቸው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት። 32 ጭፍሮችም መጥተው ከእርሱ ጋር የተሰቀሉትን የአንደኛውንና የሁለተኛውን ጭኖች ሰበሩ። 33 ወደ ጌታችን ኢየሱስም ሄደው ፈጽሞ እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ጭኑን አልሰበሩም። 34 ነገር ግን ከጭፍሮቹ አንዱ የቀኝ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ያንጊዜም ከእርሱ ደምና ውኃ ወጣ። 35 ያየውም መሰከረ፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ እርሱም እናንተ ልታምኑ እውነት እንደሚናገር ያውቃል። 36 ይህ ሁሉ የሆነው “ከእርሱ ዐፅሙን አትስበሩ” ያለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። 37 ሌላዉም መጽሐፍ ደግሞ“ የወጉትን ያዩታል” ይላል። ወደ መቃብር ስለ መውረዱ 38 ከዚህም በኋላ አይሁድን ስለፈራ በስውር የጌታችን የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረው የአርማትያስ ሰው ዮሴፍ የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ይወስድ ዘንድ ጲላጦስን ለመነው፤ ጲላጦስም ፈቀደለት። እርሱም ሄዶ የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ወሰደ። 39 ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሄዶ የነበረው ኒቆዲሞስም መጣ፤ ቀብተውም የሚቀብሩበትን መቶ ወቄት የከርቤና የሬት ቅልቅል ሽቶ አመጣ። 40 እንደ አይሁድ አገናነዝ ሥርዐትም የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ወስደው ከሽቱ ጋር በበፍታ ገነዙት። 41 በዚያም በተሰቀለበት ቦታ የአትክልት ስፍራ ነበር፤ በዚያ የአትክልት ስፍራ ውስጥም በውስጡ ሰው ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር። 42 ጌታችን ኢየሱስንም በዚያ ቀበሩት፤ ለአይሁድ የመሰናዳት ቀን ነበርና፤ መቃብሩም ለሰቀሉበት ቦታ ቅርብ ነበር። |