መዝሙር 149 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሃሌ ሉያ። 1 እግዚአብሔርን አዲስ ምስጋናን አመስግኑት፤ ምስጋናውም በጻድቃኑ ጉባኤ ነው። 2 እስራኤል በፈጣሪው ደስ ይለዋል፥ የጽዮንም ልጆች በንጉሣቸው ሐሤትን ያደርጋሉ። 3 ስሙን በደስታ ያመሰግናሉ፥ በከበሮና በበገና ይዘምሩለታል። 4 እግዚአብሔር በሕዝቡ ደስ ብሎታልና፥ የዋሃንንም በማዳኑ ከፍ ከፍ ያደርጋልና። 5 ጻድቃን በክብሩ ይመካሉ፤ በመኝታቸውም ላይ ሐሤትን ያደርጋሉ። 6 እግዚአብሔርን በጕሮሮአቸው ያመሰግኑታል፤ ሁለት አፍ ያለውም ሰይፍ በእጁ ነው፥ 7 በአሕዛብ ላይ በቀልን ያደርግ ዘንድ፥ ሕዝቡንም ይዘልፋቸው ዘንድ፤ 8 ንጉሦቻቸውንም በእግር ብረት፥ አለቆቻቸውንም በሰንሰለት ያስራቸው ዘንድ፤ 9 የተጻፈውን ፍርድ በእነርሱ ላይ ያደርግ ዘንድ። ይህች ክብር ለጻድቃኑ ሁሉ ናት። |